በምርጫ ወቅት እጩ ተወዳዳሪዎች የሚገደሉባት ከተማ

ሲንቲያ ሁዋሬዝ የምርጫ ፉክክር ያስነሳው ነውጥ የልጅነት ጓደኛዋን ነጥቋታል።
የምስሉ መግለጫ, ሲንቲያ ሁዋሬዝ የምርጫ ፉክክር ያስነሳው ነውጥ የልጅነት ጓደኛዋን ነጥቋታል

የሜክሲኮዋ ጉሬሮ ከተማ ለምርጫ ተወዳዳሪዎች አስፈሪ ናት።

በሜክሲኮ ታሪክ ከፍተኛ ነውጥ የታየበት የምርጫ ፉክክር ተካሂዷል።

ሲንቲያ ሁዋሬዝ የምርጫ ፉክክር ያስነሳው ነውጥ የልጅነት ጓደኛዋን ነጥቋታል።

ሞይሲ “ሞይ” ሁዋሬዝ አቤርካ ታዋቂ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች መብት ንቅናቄ መሪ ነበር።

የተቃዋሚው ፒአርዲ እጩ ሳለ በታጠቁ ቡድኖች ታፍኖ በጥይት ተገድሏል። አስክሬኑ የተገኘው የጅምላ መቃብር ውስጥ ከ16 ሰዎች ጋር ነበር።

“ከጓደኛዬ ሞይ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ አብረን በትግል አሳልፈናል። ይህ የምርጫ ቅስቀሳ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የከፋው ነበር” ትላለች ሲንቲያ።

በምርጫ ውድድሩ ጓደኛዋን ተክታ እጩ ሆናለች።

የጓደኛዋ ግድያ ምርመራ ውጤት ሳያስገኝ እሱን ተክታ እጩ መሆን የሚያስከትለው አደጋ ይገባታል።

ግን ለመታገል ቆርጣ ተነስታለች።

“ፈርቻለሁ። እንዴት ላርፈራ እችላለሁ። አንድ ቀን ከቤት ወጥቼ ላልመለስ እንደምችል እፈራለሁ። ግን ድምጼን ማሰማት የምችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ ነው” ትላለች።

ድምጽ መስጫ ቀን ሲቃረብ የሚደርሰው ጥቃትም ተባብሶ ቀጥሏል።

አካፑልኮ ከተማ ውስጥ ቢያንስ 12 ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል።

ስድስት አስክሬኖች ገበያ አቅራቢያ ተጥለው ነበር የተገኙት።

ኢንተግሪላ የተባለው አማካሪ ተቋም በቅርቡ በሠራው ጥናት፣ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ነውጥ ያለውን አስጊ አካሄድ ጠቁሟል።

ካለፈው ዓመት ሰኔ ምርጫ አንስቶ ወደ 200 የሚጠጉ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ፖለቲከኞችና እጩ ተወዳዳሪዎች እንደተገደሉ ወይም የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸው መዝግቧል።

በጉሬሮ ከተማ ደግሞ 50 ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የቀድሞው የአካፑልኮ ከንቲባ ከኤቮዲዮ ቬልዛኩዝ መላው የፖለቲካ ሕይወቱ ያለፈው በስጋት ነበር።
የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የአካፑልኮ ከንቲባ ከኤቮዲዮ ቬልዛኩዝ መላው የፖለቲካ ሕይወቱ ያለፈው በስጋት ነበር።

ገዢው ፓርቲ ያቀረባቸው እጩዎችም የጥቃት ሰለባ ሆነዋል።

በአካፑልኮ ግዛት የገዢው ፓርቲ ሞሬና እጩ ተወዳዳሪ የሆነው ሪካርዶ ታጃ ከጠባቂው ጋር እራት እየበላ ሳለ ሬስቶራንት ውስጥ ተኩስ ተከፍቶበት ተገድሏል።

በሜክሲኮ አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ፖለቲካዊ ነውጥ በማስነሳት ይታወቃሉ።

ድምጽ ሰጪዎች ለሕዝቡ አገልግሎት ከሚሰጡ እጩ ተወዳዳሪዎች ይልቅ በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች የሚደገፉ እጩዎችን መምረጥ ግዴታቸው ይሆናል።

ሲንትያ ከቀድሞው የአካፑልኮ ከንቲባ ከኤቮዲዮ ቬልዛኩዝ ጋር ስለ ጉዳዩ አውርታለች።

መላው የፖለቲካ ሕይወቱ ያለፈው በስጋት ነበር።

ለምክር ቤት እየተወዳደረ ሳለ ቤቱ ታጣቂዎች ሄደው አስፈራርተውታል። ከምርጫ ውድድሩ ጥሎ ወጥቷል።

“ኋላ ላይ ከሚፀፅተኝ ደኅንነቴ ይሻለኛል። ተጨማሪ የሞት ቁጥር መሆን አልሻም” ብሏል።

ለፌደራል መንግሥት ስላለው የፀጥታ ስጋት ቢገልጽም ምላሽ አላገኘም።

ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርገው የአገሪቱን ፖሊሲ ነው። ሕዝብ እየተፈጠረ ባለው ፖለቲካዊ ነውጥ የሚያድርበትን ስጋትም ሳይጠቅስ አያልፍም።

ሴናተር ፌሊክስ ሳልጋዶ ሜክዶኒዮ ከምርጫ ውድድር የወጣው የመድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ክስ ቀርቦበት ነው።
የምስሉ መግለጫ, ሴናተር ፌሊክስ ሳልጋዶ ሜክዶኒዮ ከምርጫ ውድድር የወጣው የመድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ክስ ቀርቦበት ነው።

ሴናተር ፌሊክስ ሳልጋዶ ሜክዶኒዮ ከምርጫ ውድድር የወጣው የመድፈርና ወሲባዊ ጥቃት ክስ ቀርቦበት ነው።

የቀረበበትን ክስ ያጣጣለ ሲሆን ኋላ ላይ የቀረበበትም ክስ ውድቅ ተደርጓል።

ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶር ለሴናተሩ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

60 በመቶ የሚሆኑ ሜክሲኳውያን ከተሞቻቸው ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንደሆነ አይሰማቸውም።

ሴናተሩ ካለፉት ዓመታት ለውጥ እንዳለ ያምናል።

“እንተቃቀፍ አንገዳደል” የሚል አባባል አለው።

ከምርጫ በፊት የሚደርሰውን ጥቃት አምኖ “ቀስ በቀስ ወደ አጠቃላይ ሰላም እናመራለን” ብሏል።

በአካባቢው አውሎ ነፋስ ተነስቶ በርካቶች ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። በዚህ ላይ የፖለቲካ ቀውስ ተጨምሮበት የእለት ከእለት ኑሮን ፈታኝ አድርጎታል።

መርሴደስ ሳንቼዝ ብዙ ነገር ነው ያጣችው።

መርሴደስ ሳንቼዝ ብዙ ነገር ነው ያጣችው።
የምስሉ መግለጫ, መርሴደስ ሳንቼዝ ብዙ ነገር ነው ያጣችው።

በመሬን መንሸራተት ምክንያት ወንድሟና እናቷን አጥታለች።

መንግሥት የምግብ ድጋፍን ጨምሮ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እርዳታ ማድረጉን ትናገራለች።

በየቤቱ ወደ 3 ሺህ ዶላር ገደማ ድጎማ ተሰጥቷቸዋል።

ከተፈጥሯዊው አደጋ ማገገም ሲጀምሩ ግን የፖለቲካ እንዲሁም ፖለቲካዊ ያልሆነም ግድያ ከተማዋን ይንጣት ጀመር።

ከምትኖርበት ቤት አቅራቢያ የታክሲ ሾፌር በቅርቡ ተገድሏል። መርሴደስ ሁሌም ስጋት ውስጥ ነን ትላለች።

“ከቤታችን ያለ ፍርሃት ወደ ውጪ መውጣት እንኳን አልቻልንም። ምንም ችግር ውስጥ አልገባም ያለ ሰው ሳይቀር በተሳሳተ ሰዓት የተሳሳተ ቦታ ሊገኝ ይችላል። ሁሌም አስጊ ነው።”