ምርጫ ቦርድ በእስር ስላሉ የኦነግ አመራሮች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Social Media
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ ያሉ ሰባት የኦነግ አመራሮችን ሁኔታ በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጣራት አድርጎ ከሆነ እንዲያሳውቀው በደብዳቤ ጠየቀ።
ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ ያሉ ሰባት የፓርቲው አመራሮች ሕይወት የሚያሰጋ መሆኑን ከኦነግ አቤቱታ እንደደረሰው በመጥቀስ ነው ደብዳቤውን ግንቦት 19/ 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ተቋም ኮሚቴ የጻፈው።
ኦነግ ሚያዝያ 6/ 2016 ዓ.ም ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ “አመራሮቹ በፍርድ ቤት ነጻ የተለቀቁ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ከእስር ያልተፈቱ መሆኑን፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከአገሪቱ ሕጎች በተጻረረ መልኩ በቁጥጥር ስር” ያቆያቸው መሆኑን በመጥቀስ ቦርዱ የአመራሮቹን እስር ሁኔታ መፍትሄ እንዲሰጣቸው መጠየቁን ደብዳቤው አመላክቷል።
ሰባቱ የታሰሩ የኦነግ አመራሮች አቶ አብዲ ረጋሳ፣ አቶ ሚካኤል ቦራን፣ አቶ ኬነሳ አያና፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ ዶ/ር ገዳ ገቢሳ፣ አቶ ዳዊት አብደታ እና አቶ ግርማ ጥሩነህ እንደሆኑም በምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ጌጤ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ አመላክቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ለሚ ገመቹ ፓርቲያቸው የጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተ ሲናገሩ፣ የኦነግ አመራሮች በአሁኑ ወቅት ያሉበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለተለያዩ አካላት ሲገልፁ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደምም ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ለምርጫ ቦርድ የፓርቲው አመራሮች “በእንግልት ለተለያዩ በሽታዎች ተጋልጠው በቡራዩ ከተማ በእስር ላይ ይገኛሉ በማለት ድርጅቱ ይመለከታቸዋል ላለው አካል ሁሉ ቅሬታውን እያቀረበ ነው” ብለዋል።
አቶ ለሚ በእስር ላይ የሚገኙት የድርጅቱ አመራሮች “በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። በተለይ ደግሞ አቶ ኬኔሳ እና አቶ ገዳ ገቢሳ የጤንነት ሁኔታቸው በጣም የሚያሳስብ ነው፤ ክፉኛ ተጎድተዋል” ብለዋል።
ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ለሦስት ዓመት ታስረው የሚገኙ የኦሮሞ ተቃዋሚ አመራሮች እንዲፈቱ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዋች ሐምሌ 17/ 2016 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ጠይቆ ነበር።
ተቋሙ ሰባቱ የኦሮሞ ተቃዋሚ አመራሮች በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለዘፈቀደ እስር የተዳረጉት በፖለቲካ ሚናቸው ነው ብሏል።
ሌላኛው ከእነዚህ አመራሮች ጋር ታስረው የነበሩት የፓርቲው የፖለቲካ ኦፊሰር በቴ ኡርጌሳ ከጤና ጋር በተያያዘ ከእስር ቢለቀቁም ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም. በመቂ ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው መገኘታቸው ይታወሳል።
ምርጫ ቦርድ ከኦነግ ፓርቲ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች እንደቀረቡለት ገልጾ ጥር 22/ 2016 ዓ.ም ለቋሚ ኮሚቴው በጻፈው ደብዳቤ፣ ሰባቱ የኦነግ ፓርቲ አመራሮች “እስር ቤት እንደሚቀያየርባቸው፤ የታሰሩበት ቦታ በግልጽ እንደማይታወቅ፤ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ እና የአያያዝ ሁኔታቸውም አሳሳቢ እንደሆነ” አቤቱታዎች እንደደረሱት ገልጾ መጠየቁን በዚሁ ደብዳቤ አስታውሷል።
ቦርዱ ያደረገው ክትትል በሙሉ ፍሬ ማፍራት አለመቻሉን እና በፓርቲው በተደጋጋሚ እየቀረበ ባለው አቤቱታ ላይ የተደረገ ማጣራት ስለመኖሩም መልስ አላገኘሁም ብሏል።
ስለሆነም በፓርቲው ቅሬታ ላይ የተደረገ ማንኛውም ማጣራት ካለ ቋሚ ኮሚቴው መልስ እንዲሰጠው ጠይቋል።
የኦነግ አመራሮቹ አብዲ ረጋሳ፣ ዳዊት አብደታ፣ ላሚ በግና፣ ሚካኤል ቦራን፣ ኬነሳ አያና፣ እና ጋዳ ኦልጂራ ሪፖርቱ በወጣበት ወቅት ለሶስት ዓመታት ያህል እንዲሁም ጋዳ ጋቢሳን ለሁለት ዓመት በእስር እንዳቆያቸው የገለጸው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ባለስልጣናቱ ከዚህ ተጻርረው በእስር አቆይተዋቸዋል ብሏል።
ባለስልጣናቱ አመራሮቹን ያለምንም ክስ ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ እንዳቆይዋቸው ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት አላቀረቡም ሲልም ተቋሙ ወቅሷል።
የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር "የፖሊስ ኃላፊዎች የኦሮሞ ተቃዋሚ አመራሮች ላይ ክስ ሳይመሰረትባቸው በጭካኔ ረዘም ላለ ጊዜ በእስር ላይ በማቆየት በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ላይ ይሳለቃሉ" ሲሉም ወርፈዋቸዋል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት ፓለቲከኞቹን በአስቸኳይ በመፍታት እስር የፖለቲካ ጭቆና መጠቀሚያ እንዳይሆን ማረጋገጥ አለበት።" ብለው ነበር።
እንደ ተቋሙ ከሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ባለስልጣናት የታሳሪዎቹን መብት በተደጋጋሚ በመጣስ፣ በግዳጅ በመሰወር፣ የታሰሩበት እንዳይታወቅ በማድረግ እንዲሁም ከጠበቆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለሳምንታት ወይም ለወራት እንዳይገናኙ አድርጓቸዋል።
አንዳንዴም እስከ ስምንት ወር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይገናኙ የቆዩ እንዳለ ጠቅሶ በተደጋጋሚም በጊዜያዊ መጠለያዎች እና በእስር ቤቶች በማዛወር ቤተሰቦቻቸው እንዳያገኟቸው እንቅፋት መሆናቸው ተገልጿል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የኦነግ የስራ አስፈጻሚ የሆነውን አብዲ ረጋሳን በቁጥጥር ስር ያዋሉት በቡራዩ ፖሊስ ገድሏል በሚል ጥርጣሬ በየካቲት 2012 ዓ.ም ነበር።
አብዲ ወደ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ከመዛወሩ በፊት ስድስት ኪሎ ሰፈር በሚገኝ የመንግሥት መስሪያ ቤት ታስሮ ነበር። ለሁለት ወራትም የት እንደነበር ለጠበቃው እና ለቤተሰቦቹ ሳይገለጽ መቆየቱ በተቋሙ ሪፖርት ተጠቅሷል።
ከዚያ በኋላ የኦሮሚያ ፖሊስ የልዩ ኃይሉ ካምፕ በሚገኝበት ገላንን ጨምሮ በስምንት እስር ቤቶች እንዳዘዋወረው በሪፖርቱ ሰፍሯል።
በዚህም ወቅት ለስምንት ወራት ያህል ያለበት ሳይታወቅ ደብዛው ጠፍቶ እንደነበርም ተገልጿል።
ላሚ በግና፣ ዳዊት አብደታ፣ ኬነሳ አያና እና ሚካኤል ቦረና በቁጥጥር ስር የዋሉት ታዋቂው የኦሮምኛ ዘፋኝ እና ተሟጋች ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ፣ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. ላይ ነው።
ሪፖርቱ አክሎም እነዚህንም የፖለቲካ አመራሮች በተመሳሳይ መልኩ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት ሲያዛውራቸው የቆየ መሆኑን ጠቅሶ፣ በአንድ ወቅት ከአዋሽ መልካሳ ወጣ ብሎ በሚገኝ የቀድሞ የዶሮ እርባታ ስፍራ ላይ ታስረው እንደነበር በዚህም ወቅት ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቆቻቸው አያውቁም ነበር ብሏል።
አንደኛው ግለሰብ ወንድሙ ከታሰረ በኋላ አስራ አራት ጊዜ መዘዋወሩን መናገሩን ተቋሙ በሪፖርቱ አስፍሯል።












