ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ የነበረው ጋሪ ሊኒከር ወደ ቢቢሲ ሥራው ሊመለስ ነው

ሊኒከር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሊንከር ጋር አብረው የሚሰሩት እንደ አይን ራይት፣ አለን ሺረር እና ሚካህ ሪቻርድስ ያሉ ተንታኞች ለባልደረባቸው ድጋፍቸውን ለመግለጽ ከቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራሞች ቀርተዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ በቢቢሲ ታግዶ የነበረው እውቁ እግር ኳስ ተንታኝ ጋሪ ሊኒከር ወደ ሥራው ሊመለስ ነው።

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪ ከጋሪ ሊኒከር ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ተንታኙ በመጪው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ወደ ሥራው እንደሚመለስ ይፋ አድርገዋል።

ጋሪ ሊኒከር ከሥራው እራሱን እንዲያገል በቢቢሲ ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ጉዳዩ የበርካቶች መነጋገሪ ከመሆኑም በላይ፣ የቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆች እና ተንታኞች ለጋሪ ሊኒከር ድጋፋቸውን ለመግለጽ ከቢቢሲ ሥራዎች እራሳቸውን አግልለው ነበር።

በዚህም ምክንያት በርካታ የቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራሞች እንዲታጠፉ፣ ርዝመታቸው እንዲቀነስ አልያም ደግሞ ያለ ተንታኞች እንዲቀርቡ ተደርጎ ነበር።

የጋሪ ሊኒከር ውዝግብ

እውቁ የስፖርት ተንታኝ ጋሪ ሊኒከር ከቢቢሲ የታገደው በትዊተር ገጹ በስደተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው አስተያየት ከሰጠ በኋላ ነው።

በአንድ ወቅት ስደተኞችን በግል መኖሪያው አስጠግቶ ሲያኖር የነበረው እና የስደተኞች መብት ተቋርቋሪ የሆነው ጋሪ ሊኒከር የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የስደተኞች ፖሊስን አጥብቆ ተችቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም በእንግሊዝ ቻናል በኩል ወደ አገር ግዛቷ ስደተኞችን ወደ ትውልድ አገራቸው አልያም ወደ ሦስተኛ አገር እመልሳለሁ ማለቷን ነው ሊኒከር አጥብቆ የተቸው።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከ45 ሺህ በላይ ስደተኞች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር መግባታቸውን፤ ስደተኞችን በሆቴሎች ለማቆየት በቀን 7 ሚሊዮን ፓወንድ ወጪ እያደረገ መሆኑን ገልጾ ከአሁን በኋላ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን አልታገስም ብሏል።

“በእዚህ ሕገ-ወጥ መንገድ የሚመጣ ስደተኛ ታስሮ ወደ ትውልድ አገሩ ወይም ወደ ሦስተኛ አገር [ሩዋንዳ] ይላካል” ብሏል የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ።

ሊኒከር ግን የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ስደተኞችን አልቀበልም በሚል ባወጣው መግለጫ ላይ የተጠቀመው ቋንቋ እአአ በ1930ዎቹ ከነበረው ናዚ ጀርመን ጋር አያይዞ አስተያየቱን ሰጥቷል።

በዚህም የስፖርት ተንታኙ የዩናይትድ ኪንግደም ገዢ ፓርቲ ከሆነ የወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የሰላ ትችት ሲቀርብበት የቆየ ሲሆን፣ ቢቢሲም ከቀናት በፊት ሊኒከር የሰጠው አስተያየት የቢቢሲን የገለልተኛነት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚጥስ ነው በማለት ከቢቢሲ ፕሮግራሞች እራሱን እንዲያገል ጠይቆት ነበር።

የቢቢሲ ውሳኔም ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ከሊኒከር ጋር አብረው የሚሰሩት እንደ ኢያን ራይት እና አለን ሺረር ያሉ እውቅ የስፖርት ተንታኞች ለባልደረባቸው ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በቢቢሲ የስፖርት ፕሮግራሞች ላይ ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ይህን ተከትሎም የስፖርት መረሃ ግብሮች ላይ ያልተጠበቁ ለውጦች መጥተዋል። ቅዳሜ እና እሁድ የነበሩት ፕሮግራሞች እንዲያጥሩ ወይም ያለ ተንታኝ እንዲቀርቡ ሆነዋል።

ቅዳሜ ምሽት የተላለፈው ‘ማች ኦፍ ዘ ደይ’ ፕሮግራም ላይ ተንታኞች አልቀረቡም። በእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይም አስተያየት የሚሰጥ ባለሙያ ባለመኖሩ ከስታዲየም በሚወጣ ድምጽ ተሸፍኖ ነበር።

የቢቢሲ ዳይሬክተር ጀነራል ቲም ዴቪ
የምስሉ መግለጫ, የቢቢሲ ዳይሬክተር ጀነራል ቲም ዴቪ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቀኑ ለቢቢሲ “አስቸጋሪ ነበር” ያሉ ሲሆን፤ ሊኒከርን ወደ ቢቢሲ ስቱዲዮ ተመልሶ ተመልካቾች ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ፕሮግራሞችን እንዲያገኙ ማስቻል ቀዳሚ ዓላማቸው አንደሆነ ገልጸዋል።

ዛሬ ሰኞ ንጋት ውይይት አድርገው ወደፊት ምን መሆን እንዳለበት ከጋሪ ሊኒከር እና የሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተስማምተናል ብለዋል።

“ጋሪ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ወደ ስቱዲዮ ስለሚመለስ ደስተኛ ነኝ። ጋሪ አስደናቂ ችሎታ ያለው የስፖርት ተንታኝ እና ውድ የቢቢሲ አካል ነው። ደርጅቱም ለእርሱ ምን ያክል ውድ እንደሆነ አውቃለሁ” ብለዋል ቲም ዴቪ።

ዋና ዳይሬክተር ጨምረው እንደገለጹት ከዜና እና ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት በሌላቸው ቋሚ ቅጥረኛ ባልሆኑ ባልደረቦች ላይ የቢቢሲ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን በገለልተኛ አካል ምርመራ ይደረጋል ብሏል።

ቢቢሲ ቀደም ሲል የእግር ኳስ ተንታኙ ከሥራው እንዲሰናበት የጠየቀው የተቋሙን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ተላልፏል በማለት ቢሆንም፣ ዋና ዳይሬክተሩም ሆኑ ተቋሙ ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ አይደሉም የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ሲሰጡ ቆይተዋል።

ለጋሪ ሊኒከር ድጋፋቸውን የገለጹ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ቲም ዴቪ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጨምር ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ መከራከሪያቸው ቲም ዴቪ የቢቢሲ ኃላፊነታቸውን ከመረከባቸው በፊት ሥልጣን ላይ ያለው የወግ አጥባቂ ፓርቲ አመራር ነበሩ የሚል ነው።

ዋና ዳይሬክተሩ ግን የጋሪ ሊኒከር ጉዳይ ለቢቢሲ ፈታኝ መሆኑን አምነው ሥልጣናቸውን ግን እንደማይለቁ ተናግረዋል።

ከቲም ዴቪ በተጨማሪ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አጋር ናቸው የተባሉት የቢቢሲ ቦርድ ሰብሳቢ ሪቻርድ ሻርፕ በተመሳሳይ ሥራቸውን እንዲለቁ እየተጠየቁ ነው።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ለወግ አጥባቂ ፓርቲ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው እና ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንስ የ800 ሺህ ፓዎንድ ብድር አሰጥተዋል መባሉት ተከትሎ በሚዲያ አዘጋጋብ ገለልተኛ ሊሆኑ ስለማይችሉ ከሥራቸው ይልቀቁ እየተባለ ነው።