በ1990ዎቹ በቦስኒያ ንጹኃንን በጥይት ለመምታት ገንዘብ ከፍለዋል በተባሉ ጣልያናዊያን ቱሪስቶች ላይ ምርመራ ተከፈተ

የቦስኒያ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, AP Photo/Jerome Delay

እአአ በ1990ዎቹ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ወደ ቦስኒያ እና ኸርሰግቪና በመሄድ ንጹኃን ላይ ጥይት ይተኩሱ የነበሩ ጣልያናዊያን ቱሪስቶችን በተመለከተ ምርመራ ተጀመረ።

የሚላን ዐቃቤ ሕግ ምርመራ የከፈተው ቱሪስቶች ገንዘብ ከፍለው ንጹኃን ላይ ይተኩሱ እንደነበር ክሶች ከቀረቡ በኋላ ነው።

"sniper safaris" በሚል ጣልያናዊያን ቱሪስቶች ወደ ቦስኒያ እና ኸርሰግቪና ይሄዱ እንደነበር ጋዜጠኛ እና ደራሲ ኢዝኖ ጋቫዜኒ ይፋ አድርጓል።

"ቱጃሮች ሰዎችን እያደኑ ይተኩሱባቸው ነበር። አቅመ ደካማ የሆኑ ንጹኃንን ለመግደል ገንዘብ ከፍለዋል" ብሏል።

ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናትን ለመግደል የወጣው የክፍያ መጠን የተለያየ ነበር።

አራት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ከ11,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ዩጎዝላቪያ በጦርነት ስትበታተን ከተማዋን የሰርብ ኃይሎች ከብበዋት ነበር። በወቅቱ "የሰዎች አደን" ይካሄድ እንደነበር ከዚህ ቀደምም ክሶች ተሰምተዋል።

የቦስኒያ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, CHRISTOPHE SIMON/AFP

ጋዜጠኛ እና ደራሲው ያሰባበሰው ማስረጃ የቦስኒያ የደኅንነት ባለሥልጣን ምስክርነት ያካተተ ነው።

ዐቃቤ ሕግ አሌሳንድሮ ጎቢስ ምርመራ እያደረጉ ሲሆን፤ የግድያ ክስ እንደሚመሠረት ተገልጿል።

የቦስኒያው የደኅንነት ባለሥልጣን እንዳሉት፤ በ1993 መጨረሻ አካባቢ በቱሪስቶች ስለተፈጸመው ግድያ መረጃ አግኝተዋል። መረጃውንም በ1994 ለጣልያን የደኅንነት ባለሥልጣናት አስረክበዋል።

የጣልያን ደኅንነት ባለሥልጣናት ከሁለት ወራት በኋላ የሰጡት ምላሽ፤ ቱሪስቶቹ ከሰሜን ጣልያን ተነስተው በድንበር ከተማ ቲሬሴ አቋርጠው ወደ ሳራጄቮ ተራራማ አካባቢዎች ይጓዙ እንደነበር አመልክተዋል።

ይሄንን የቱሪስቶች ጉዞ ማስቆማቸውንም የጣልያን ደኅንነት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የቦስኒያ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL EVSTAFIEV/AFP

እአአ በ2022 "Sarajevo Safari" የተባለ ዘጋቢ ፊልም ስለ ድርጊቱ ዝርዝር መረጃ ካወጣ በኋላ ጋዜጠኛ እና ደራሲው ኢዝኖ ጋቫዜኒ ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።

ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት ስለ ጉዳዩ ቢሰማም ዘጋቢ ፊልሙ እስከሚወጣ ድረስ ተጨባጭ ማስረጃ አላገኘም ነበር።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ እንደተጠቀሰው ግድያውን የፈጸሙ ቱሪስቶች ከጣልያን በተጨማሪ ከአሜሪካ እና ከሩስያም ተጉዘዋል። ስለ ድርጊቱ በቦስኒያ ምርመራ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም መቋረጡ ተገልጿል።

ኢዝኖ ጋቫዜኒ ያገኘውን ባለ 17 ገጽ ማስረጃ ለዐቃቤ ሕግ አስረክቧል።

ከጣልያኑ 'ላ ሪፐብሊካ' ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ "በድርጊቱ ብዙዎች ተሳትፈዋል። ቢያንስ መቶ ሰዎች ይሆናሉ። አሁን ባለው ተመን እስከ 88,000 ፓውንድ እየከፈሉ ግድያውን ፈጽመዋል" ብሏል።

በ1992 ሩስያዊው ፖለቲከኛ እና ጸሐፊ ኤድዋርድ ሊሞኖቭ፤ የቦስኒያ እና ኸርሰግቪና መዲና በሆነችው ሳራጄቮ ግዙፍ የማሽን ጥይት ሲተኩስ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል።

ሰርቢያዊው የቦስኒያ መሪ ራዶቫን ከርዲክ ለፖለቲከኛው ሰርቢያን ሲያስጎበኝ የሚያሳይ ምሥልም ተገኝቷል።

ኤድዋርድ ሊሞኖቭ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በዘር ጭፍጨፋ ተፈርዶበታል።

የጣሊያን ዐቃቤ ሕግ የዐይን እማኞችን እንደለየ እና ምስክርነታቸውን ተጠቅሞ በግድያው የተሳተፉትን እንደሚለይ አስታውቋል።

በሳራጄቮ በ1990ዎቹ ተሰማርተው የነበሩ የእንግሊዝ ወታደሮች ስለ ግድያው "ሰምተው እንደማያውቁ" ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አንድ የእንግሊዝ ወታደር "ከጭምጭምታ ባለፈ እውነታ የለውም" ሲል ክሱን አጣጥሏል።