መከራቸው የበዛው ቦስኒያ የሚገኙ ስደተኞች

ስደተኞች በመጠለያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቦስኒያ ክረምት ገብቷል። በድንበር በኩል አቋርጠው ወደ ክሮሺያ ለመግባት ያሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም እጅግ የሚበርደውን ክረምት በቦስኒያ ለማሳለፍ ተገደዋል።

ለአብዛኛዎቹ ስደተኞች ምሽት ላይ በተለይ ከዜሮ በታች የሚሆነውን ቅዝቃዜ መቋቋም የማይታሰብ ነው። ሁኔታው ለህይወታቸውም አስጊ የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገልጿል።

'ቢራ' በሚባለው አካባቢ የዓለማቀፉ ስደተኞች ድርጅት ማዕከል የከፈተ ቢሆንም በርካታ ስደተኞች መጠለያ ፍለጋ እዚህም እዚያም ሲንጎራደዱ መመልከት የተለመደ ነገር ሆኗል።

ከዚህ በፊት የማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ፋብሪካ የነበረው አዳራሽ በአሁኑ ሰአት እስከ 2000 በሚደርሱ ስደተኞች ተጨናንቋል። ማዕከሉ መተኛ ክፍሎች፣ የጤና አገልግሎት፣ መታጠቢያዎች ያሉት ሲሆን ትኩስ ምግቦችንም ያቀርባል።

ነገር ግን የስደተኞቹ ቁጥር ከአቅም በላይ በመሆኑ በርካታ ስደተኞች ወደ ማዕከሉ መግባት አይችሉም። የማዕከሉ ሃላፊ የሆነችው አሚራ ሀድዚሜሜዶቪችም ሁኔታው በጣም የሚያሳዝን መሆኑን ትገልጻለች።

'' በጣም መጥፎ ስሜት ውስጥ ነው የሚከተው። አንድን ሰው ልረዳህ አልችልም ብሎ በእንደዚህ አይነት ብርድ ውስጥ ውጪ እንዲያድር ማድረግ በጣም ከባድ ነው'' ብላለች።

ምንም እንኳን የሀገሪቱ መንግሥት አዲስ ስደተኞች እንዳይገቡ ቢከለክልም እስከ 2000 የሚደርሱ ስደተኞች አሁንም ከበረዶ ጋር እየታገሉ በመንገዶች ግራና ቀኝ ይታያሉ።

የስደተኞች መጠለያው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአውሮፓ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ዱንጃ ሚጃቶቪች የስደተኞች መጠለያውን ከጎበኙ በኋላ ሁኔታው ''ኢሰብአዊና ተቀባይነት የሌለው ነው'' ብለዋል።

''ስደተኞች ከበረዶና ጭቃ ጋር ተቀላቅለው ማየት ያሳምማል፤ በቂ የሆነ ውሀ አቅርቦት እንኳን የላቸውም፤ የስደተኞች ማቆያው ከነጭራሹ ሊከፈት አይገባም ነበር'' ብለዋል በሰጡት መግለጫ።

አክለውም ስደተኞቹን ወደተሻለ ቦታ ማዘዋወርና ተገቢውን ሰብአዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።