ዓይነ ስውራን ማንበብ እንዲችሉ የሚያደርገው ፈር ቀዳጅ ግኝት

የ70 ዓመቷ ሺላ ኧርቪን
የምስሉ መግለጫ, ሺላ ኧርቪን ዕይታቸውን የለወጠውን ቴክኖሎጂ አድርገው

በተወሰኑ ዓይነ ስውራን ላይ ከዓይን ብሌናቸው ጀርባ በተገጠመላቸው መሳሪያ አማካኝነት ለማንበብ በመቻላቸው በሕወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ ተመዝግቧል።

ለንደን በሚገኘው የሙርፊልድስ ዓይን ሆስፒታል ውስጥ በአምስት ታማሚዎች ላይ ይህን ማይክሮ ቺፕን የገጠሙት የቀዶ ሕክምና ሐኪም የዓለም አቀፉ ሙከራው ውጤት "አስደናቂ" መሆኑን ተናግረዋል።

በዓይነ ስውርነት የተመዘገቡት የ70 ዓመቷ ሺላ ኧርቪን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማንበብ እና የቃላት ሰንጠረዥ መሥራት መቻላቸውን "ተአምር" በማለት "ድንቅ ነገር ነው፣ ደስታን የሚሰጥ ነው" በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ይህ አዲሱ ቴክኖሎጂ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ወደ 350 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን እንደሚያጠቃ የሚገመተው ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ዓይነ ስውርነት ለገጠማቸው ሰዎች ተስፋ ይሰጣል።

እንዲህ ባለው የዓይነ ስውርነት ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከዓይናቸው ጀርባ ያለው ትንሽዬው የሬቲና ክፍል ቀስ በቀስ ይጎዳል፣ በዚህም ምክንያት የዓይን ብዥታ ወይም የዕይታ መዛባት ይገጥማቸዋል። የቀለም ዓይነት እና ጥቃቅን ዝርዝሮችን መለየት ብዙውን ጊዜ አይችሉም።

ይህ አዲሱ ዘዴ ትንሽዬ 2 ሚሊ ሜትር መጠን ያላት ውፍረቷም የሰው ፀጉር ያህል የምትቀጥን ፎቶቮልታይክ የተባለች ማይክሮ ቺፕ ከዓይን የጀርባ ክፍል ባለው ሬቲና ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ የሚሆን ነው።

ለዚህም ችግሩ ያለባቸው ሰዎች አብሮ የተሠራ የቪዲዮ ካሜራ ያለው መነጽር ያደርጋሉ። ካሜራውም ምሥስሎችን በኢንፍራሬድ ጨረር አማካኝነት በዓይን ውስጠኛ ክፍል ወደ ተቀመጠው ቺፕ እና በኪስ ወደሚያዘው ትንሽዬ የምሥል ማቀናበሪያ በመላክ ምሥሉ ግልጽ እና ጥራት ያለው እንዲሆን ይደረጋል።

ከዚያም ምሥሎቹ እንደገና በተገጠመው ትንሽዬ ቺፕ እና በኦፕቲክ ነርቭ በኩል ወደ ግለሰቡ አንጎል ይላካሉ፣ ይህም እንደገና የተወሰነ ዕይታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ይህንን አዲስ ቴክኖሎጂ በቀዳሚነት እንዲጠቀሙ የተደረጉት ዓይነ ስውራን በመሳሪያዎቹ አማካኝነት የሚደርሳቸውን ምሥሎች እንዴት መረዳት እንዳለባቸው በመማር ለወራት ቆይተዋል።

ምሥስሎች

በዩናይትድ ኪንግደም የሚካሄደውን ይህንን ሙከራ የመሩት በለንደን የሙርፊልድስ የዓይን ሆስፒታል የዓይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ማሂ ሙቂት ግኝቱ "ፈር ቀዳጅ እና ሕይወትን የሚለውጥ ቴክኖሎጂ" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ይህ ለዓይነ ስውራን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ እንደ ማንበብ፣ መጻፍ ያሉ ትርጉም ያላቸውን ነገሮች ለመከወን ዕይታን በመስጠት በኩል የታየ የመጀመሪያው ስኬት ነው።

"ይህም ጉልህ ለውጥ ይመስለኛል" ብለዋል።

በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲስን መጽሔት ላይ ለታተመው ምርምር በአምስት የአውሮፓ አገራት ውስጥ 38 የዓይነ ስውርንት ችግር ያለባቸው ሰዎች በካሊፎርኒያ ባዮቴክ ሳይንስ ኮርፖሬሽን በተሠራው ሙከራ ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ ሙከራ ውስጥ ከተሳተፉት 32 ዓይነ ስውራን መካከል 27ቱ ተፈጥሯውን ማዕከላዊ ዕይታ በመጠቀም እንደገና ማንበብ ችለዋል። ከአንድ ዓመት በኋላም የዕይታቸው መጠን እየሰፋ የሚያነቧቸው ፊደላት እና የመስመሮች ብዛት እየተሻሻለ መጥቷል።

በሺላ ላይ የታየው መሻሻል ደግሞ የበለጠ አስደናቂ ነው። ያለዚህ ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ማንበብ አይችሉም።

ሺላን በሙርፊልድስ ሆስፒታል የዓይን ጤና መመርመሪያ ሰሌዳ ላይ በተደረገላት ፈተና ወቅት ሲያነቡ አንዱንም አልተሳሳቱም፤ በዚህም በእጅጉ ደስተኛ ሆነው ታይተዋል።

ሺላ በዓይናችን ውስጥ ባለው ሬቲና በተባለው ክፍል ውስጥ ያሉ ህዋሳቶቻቸው በመዳከማቸው ምክንያት ከ30 ዓመታት በፊት ነበር ማዕከላዊ ዕይታቸውን ማጣት የጀመሩት።

ሺላ ኧርቪን
የምስሉ መግለጫ, ሺላ ኧርቪን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሺላ በጣም የተገደበ ዕይታ ስለነበራቸው እና ሙሉ በሙሉ ስለደበዘዘ የዓይነ ስውራንን በትር ይጠቀማሉ። ከቤት ውጪ ሲሆኑም ጎላ ጎላ ያሉትን የመንገድ ምልክቶች እንኳን ማንበብ አይችሉም ነበር። በዚህም ምክንያት መንጃ ፈቃዳቸውን ለመመለስ በመገደዳቸው አዝነው ማልቀሳቸውን ተናግረዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት አካባቢ የተገጠመላቸውን ይህ ዕይታን የሚመልሰውን ቴክኖሎጂ ካገኙ በኋላ፣ የሙርፊልድስ የሕክምና ቡድን እንደተሰማው ሁሉ እያዩት ባለው ለውጥ ተደስተዋል።

"አሁን መልዕክቶችን እና መጽሐፍትን ማንበብ እንዲሁም የቃላት ሰንጠረዥ መሥራትን" ይላሉ።

እንደገና አነባለሁ ብለው አስበው ታውቁ እንደሆነ ሺላ በተጠየቁበት ጊዜ "ፈጽሞ!" ሲሉ መልሰዋል።

"የሚደንቅ ነገር ነው። እኔ አሁን አንድ ደስተኛ ሴት ነኝ" በማለት "ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተራመደ ነው፣ እኔም የዚሁ አካል መሆኔ ያስደስተኛል" ሲሉ ሕክምናው የፈጠረላቸውን ስሜት ገልጸዋል።

ሺላ ከቤት ውጪ ሲሆኑ መሳሪያውን አይጠቀሙም። በከፊል ይህ የሆነበት ምክንያት አጠቃቀሙ ከፍተኛ ትኩረትን ስለሚፈልግ ለማንበብ ጭንቅላታቸው በጣም ተረጋግቶ መቀመጥ ስላለበት ነው።

እንዲሁም እሳቸው በመሳሪያው ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን ስላለፈለጉ ጭምርም ነው።

ይልቁንም በየቀኑ ተቀምጠው ልዩ መነጽራቸውን ከማጥለቃቸው በፊት የዕለት ከዕለት የቤት ውስጥ የሥራቸውን በፍጥነት እንደሚያከናውኑ ይናገራሉ።

ይህ አሁን ሙከራው በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀው የዓይነ ስውራን የዕይታ መርጃ በስፋት አገልግሎት ላይ እንዲውል ገና ፈቃድ ስላልተሰጠው ከሙከራ ባሻገር ለገበያ አልቀረበም። በተጨማሪም ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣም እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ነገር ግን ሙከራውን የመሩት የዓይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ማሂ ሙቂት እንደሚሉት "በጥቂት ዓመታት ውስጥ" በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አማካኝነት ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተስፋ አላቸው።