የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ እስራኤል በጋዛ ‘የዘር ጭፍጨፋ’ እየፈጸመች ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን እስራኤል በጋዛ ‘የዘር ጭፍጨፋ’ እየፈጸመች ነው አሉ።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በአደባባይ እስራኤል ላይ የሰላ ትችት ያሰሙት ልዑል አልጋ ወራሹ የእስራኤልን ድርጊት ኮንነዋል።
የሙስሊምና አረብ አገራት መሪዎች ጉባዔ ላይ እስራኤል በሊባኖስና በኢራን የፈጸመችውንም ጥቃት አውግዘዋል።
በሪያድና ቴህራን መካከል ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ መሆኑን በሚጠቁም ሁኔታ ኢራን ላይ እስራኤል የምታደርሰውን ጥቃት በተመለከተም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ሌሎችም በጉባዔው የታደሙ መሪዎች እስራኤል ከዌስት ባንክና ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቃ እንድትወጣ ጠይቀዋል።
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሀን አል-ሱአድ የጋዛ ጦርነት እስካሁን ያልቆመው “በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውድቀት ምክንያት ነው” ብለዋል።
እስራኤል በቀጠናው ረሃብ አስከትላለች ሲሉም ኮንነዋል።
“የእስራኤልን ጥቃት ለማስቆምና ግጭቱን ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተስኖታል” ሲሉም አክለዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ታግተዋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ በከፈተችው ጥቃት ከ43,400 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት ከተገደሉት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑን ሴቶችና ሕጻናት ናቸው ብሏል።
የሙስሊምና አረብ አገራት ጉባዔ ተሳታፊዎች እስራኤል በተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞችና በጋዛ መሠረተ ልማት እያደረሰች ያለውን “ተከታታይ ጥቃት” አውግዘዋል።
ባለፈው ወር በፍልስጤም የሚሠራውን የተባበሩት መንግሥታት ክንፍ እስራኤል ለማገድ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል።
ተቋሙ ከሐማስ ጋር “አብሯል” በሚል በእስራኤልና በይዞታ ሥር ባለው ምሥራቅ እየሩሳሌም እንዳይሠራ ነው ውሳኔው የተላለፈው።
አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ብዙ አገራት ውሳኔውን ኮንነዋል። እርዳታ ወደ ጋዛ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር ቅርበት እንዳላቸው የሚያውቁት የገልፍ አገራት ከነሱ ጋርም ያላቸውን ቅርበት ተጠቅመው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ግጭቱን ለማስቆም ጫና እንዲያሳድሩ ይሻሉ።
ከጆ ባይደን አንጻር ለሳዑዲ የሚቀርቡት ትራምፕ ቢሆኑም በመካከለኛው ምሥራቅ ያላቸው የቀደመ ታሪክ ድብልቅ ነው።
እየሩሳሌምን የእስራኤል መዲና በማለትና የጎላን ሀይትስን በግዳጅ በያዝ ዕውቅና በመስጠት ሙስሊሙን አገራት ሲያስቆጡ እስራኤልን አስደስተዋል።
እአአ በ2020 ‘አብርሃም አኮርድስ’ በሚል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ባሕሬንና ሞሮኮ ከእስራኤልና ሱዳን ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙት እንዲፈጥሩ አስችለዋል።












