ዛሬ ረፋድ በመቀለ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች ተበተኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዛሬ ጳጉሜን 2/2015 ዓ.ም. ንጋት በትግራይ መዲና መቀለ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጠራ ሰልፍ በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ተበተነ።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች “የአስተዳደር አቅም ማነስ” አለ በሚል እና የትግራይ ሕዝብ ስቃይ አላበቃም በማለት የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተው ነበር።
ዛሬ ጠዋት ሮማናት ተብሎ በሚጠራው አዳባባይ ለመሰባሰብ የሞከሩ ወጣቶች ለአጭር ግዜ የተበተኑ ሲሆን ወጣቶች ዳግም ተደራጅተው ለተቃውሞ ለመሰባሰብ ያደረጉት ጥረት በጸጥታ ኃይሎች እንዲበተን ተደርጓል።
ለሦስት ቀናት የተጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በመቀለ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል።
በርካታ የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች በተሸከርካሪ እና በእግር ሆነው በተከማዋ እየተዘዋወሩም ነበር።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሌሎች ማኅብረሰብ አንቂዎች በፖሊስ ታስረው ነበር። የሰልፉ ተሳታፊ ለመሆን አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችም ለእስር ተዳርገዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጅ ከሆኑት መካከል አንዱ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ “ዛሬ ጠዋት የተቃውሞ ሰልፉ በተጠራበት ቦታ ለሰላማዊ ተቃውሞ ብንገኝም በቦታው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ተሰማርቶ ጠበቀን። ወደ አካባቢው የመጣውን በሙሉ ወደ እስር ቤት እየላኩ ነው” ብለዋል።
ቀደም ሲል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውድቅ አድርጎት ነበር።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን የተቃውሞ ስልፍ የማድረጊያ "ትክክለኛው ጊዜ አይደለም" ይላል። አስተዳደሩ ይህ ጊዜ ሁለት ዓመት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ለተጎዱ ምግብን እና መድሃኒት መቅረብ ያለበት ግዜ ነው ብሏል።
ትናንት የግዚያዊ አስተዳደሩ መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ እንዲሰረዝ የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ በመቀለ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ነው ብለው ነበር።
በትግራይ የሚገኙ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ የሚጀመር እና ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ በትግራይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ የሚጠይቀው ሰልፍ እንዳይደረግ ፖሊስ ሰዎችን በኃይል በትኗል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የጠሩት ሰልፍ የታገደበት ዋነኛ ምክንያት በመቀሌ ያለው የጸጥታ ችግር መሆኑን አቶ ጌታቸው የገለጹ ሲሆን፣ ከዚያ ባሻገር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሕጋዊ መሠረት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል።
ይህን በተመለከተ አቶ ጌታቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ “ሰላማዊ ሰልፍ መፍቀድ ወይም መከልከል የሚባል ነገር እንደሌለ ከፓርቲዎቹ አመራሮች ጋር ተስማምተናል። ሆኖም የሰልፉን ቦታ መወሰን የፓርቲዎች ኃላፊነት አይደለም” ብለዋል።
“ሕጋዊ መሠረታቸውን በተመለከተ ሙግት ውስጥ ላለመግባት ተውነው እንጂ፣ እነዚህ ፓርቲዎች እኮ አሁን ባለው ምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት የቤት ውስጥ ስብሰባ ከመጥራት በስተቀር በአደባባይ ሰልፍ የመጥራት መብትም የላቸውም" ብለዋል።












