ፍልስጤሞች ከሳዑዲ-እስራኤል ታሪካዊ ስምምነት የሚፈልጉት ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
እስራኤል በዙሪያዋ ከሚገኙ አረብ አገራት ጋር ግንኙነቷን እያደሰች ነው።
ይህ በትራምፕ ዘመን የተጀመረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ በአውሮፓውያኑ 2020 ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ከባህሬንና ከሞሮኮ ጋር ስምምነትን አሳክታለች።
ሱዳንም ቢሆን ይህንኑ መስመር እንድትከተል ተበረታታ ነበር፤ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ከማምራቷ በፊት።
ከየትኛውም የመካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገሮች ውስጥ በእስራኤል በጉጉት የምትጠብቀው አገር ግን ሳዑዲ አረቢያ ናት።
ሳዑዲ ለእስራኤል እውቅና ከሰጠች መላው የአረቡና የሙስሊሙ ዓለም ለእስራኤል እውቅና እንደሰጠ የሚያስቆጥር ነው ይላሉ ተንታኞች።
ቤኒያሚን ኔታንያሁም ይህን ተስፋ ለሕዝባቸው ጠቆም አድርገዋል።
አሜሪካ ውስጥ ውስጡን እያሸማገለችው በሚገኘው በዚህ ስምምነት ፍልስጤሞች ምን እንደሚፈልጉ ይፋ አድርገዋል።
ኦማን ላይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ባርባራ ሊፍ ጋር የተገናኙት ከፍተኛ የፍልስጤም ባለሥልጣናት በትንሹ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል።
- በእስራኤል ሙሉ ቁጥጥር ሥር ከሚገኘው ዌስት ባንክ ከፊሉ ወደ ፍልስጤም አስተዳደር እንዲመለስ።
- በዌስት ባንክ እስራኤል የምታደርገው የሰፈራ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም።
- ሳዑዲ አረቢያ ለፍልስጤም በየዓመቱ የምታደርገው እርዳታ እንዲቀጥል። የሳዑዲ እርዳታ ከ2016 ጀምሮ እየቀነሰ መጥቶ ከሦስት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ መቆሙ ይታወሳል።
- አሜሪካ በፍልስጤም ቆንጽላዋን አሁን በእስራኤል ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ምሥራቅ እየሩሳሌም እንድትከፍት (ይህ ቆንጽላ በዶናልድ ትራምፕ ትእዛዝ እንዲዘጋ መደረጉ ይታወሳል።)
- አሜሪካ ስታሸማግለው የቆየችው የፍልስጤም-እስራኤል ድርድር ጆን ኬሪ እአአ 2014 ላይ ካቆሙበት እንዲቀጥል የሚሉ ናቸው።
ሳዑዲ ለፍልስጤም እስራኤል ችግር መፍትሄ ያለቸውን ዕቅድ በፈረንጆቹ 2002 ላይ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
ይህም ሁሉንም የአረቡ ዓለም የሚያካትት ዕቅድ ነው ተብሎ ይታመናል።
በዚህ ዕቅድ መሠረት እስራኤል ከአረቡ ዓለም ሙሉ እውቅና እንድታገኝ በምላሹ አሁን በኃይል ከያዘቻቸው የዌስት ባንክ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለ’ቃ እንድትወጣ፣ እና ዌስትባንክና ጋዛን ያካተተና ዋና ከተማውን ምሥራቅ እየሩሳሌም ያደረገ የፍልስጤም አገር እንዲመሠረት የሚል ነበር።
አሜሪካ አሁን ሳዑዲና እስራኤልን ማደራደር የያዘችው በቁም ነገር ነው።
ጆ ባይደን ከዓመት በኋላ ለምርጫ ሲቀርቡ ለዲሞክራቶች አንድ ትልቅ የብሥራት ዜና ይዘው የመቅረብ ፍላጎት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳዑዲ፣ እስራኤል አገር ሆና ከተመሠረተችበት ከ1940ዎቹ መጨረሻ ወዲህ አንድም ጊዜ እውቅና ሰጥታት አታውቅም።
የአረቡና የሙስሊሙ ዓለም መሪ ተደርጋ የምትወሰደው ሳዑዲ ታዲያ ለእስራኤል እውቅና እንድትሰጥ ማድረግ ለጆ ባይደን ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው የሚሆንላቸው።
ሳዑዲ ለእስራኤል ዕውቅና ለመስጠት ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎችም አሉ። ከእነዚህ ዋና ዋናዎቹ ፍልስጤሞችን የሚመለከቱ አይደሉም። የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ያስቀመጠቻቸው ናቸው።
አንዱና ዋንኛው እጅግ የተራቀቁ አሜሪካ ሠራሽ የጦር መሣሪያዎችን ከአሜሪካ መግዛት እንድትችል እንዲፈቀድላት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ለሰላማዊ ልማት የሚውል የኑክሊየር ፕሮግራም ለመጀመር በአገሯ ዩራኒየም ማበልጸግ እንድትችል ነው።
የሳዑዲው ልዑልና መሪ መሐመድ ቢን ሰልማን ለእስራኤል ዕውቅና የሰጡት እንዲሁ በዋዛ እንዳልሆነ ጸረ እስራኤል ለሆነው ሕዝባቸውና ለመላው የአረቡ ዓለም ማሳመን አለባቸው።
በአረቡ ዓለም ለእስራኤል ዕውቅና መስጠት ፍጹም ፍልስጤም ወንድሞችን መካድ ተደርጎ ነው የሚታየው።
መካከለኛው ምሥራቅ አብዛኛው ሕዝብ ለፍልስጤሞች ስስ ልብ ነው ያለው።
የፍልስጤሞችን ስቃይ የራሱ ስቃይ አድርጎ ነው የሚመለከተው።
በዚህ ሁኔታ ለእሰራኤል ዕውቅና መስጠት ዋጋ እንደሚያስከፍል ቢን ሰልማን ጠንቅቀው ይረዳሉ።
ለዚህም ነው አጋጣሚው ከተገኘ አይቀር ሁለት ትልልቅ ቅድመ ሁኔታዎችን በአገራቸው ስም ያስቀመጡት።
የጦር መሣሪያ ግዥዉና የኒክሊየር ግንባታ ይሁንታን ደግሞ አሜሪካ ለሳዑዲ ለመስጠት ይተናነቃታል። የአሜሪካ ሴኔት ይህን ጥያቄ በይሁንታ ይመለከተዋል ተብሎ አይጠበቅም።
ሳዑዲ በአሜሪካ ፖለቲከኞች ዘንድ በሰብአዊ ጥሰት የምትነሳና የምትወሳ፣ ማንኛውም ወደ ሳዑዲ የሚደርስ የጦር መሣሪያ በአሸባሪዎች እጅ ሊወድቅ እንደሚችል የሚገመት፣ በየመን ጦርነትና እልቂት እጇ እንዳለበት የሚታመን ነው።
ሌላው ተንታኞች እያነሱት ያለው መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ እሰራኤል ይመለከታል።
ይህ አሜሪካ የምታሸማግለው ስምምነት ፍሬ እያፈራ ቢሄድ እንኳ በእስራኤል አሁን ያለው አክራሪ ቀኝ ዘመም መንግሥት ይህን የስምምነት ቅድመ ሁኔታ እንዴት ሊቀበለው ይችላል የሚለው ነው።












