አቶ ጌታቸው ረዳ በመግለጫቸው ያነሷቸው አምስት አንኳር ነጥቦች

የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ

የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ እሮብ ጳጉሜ 1 2015 ዓ.ም. በመቀለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው በዚህ መግለጫቸው የይገባኛል ጥያቄ ስለሚነሳባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በትግራይ ስላለው የጸጥታ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

ጊዜያዊ አስተዳዳሪው በትናንቱ መግለጫቸው ከነሷቸው ነጥቦች መካከል አምሰቱ አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

የይገባኛል ጥያቄ ስለሚነሳባቸው ስፍራዎች እና የተፈናቃዮች ጉዳይ

ግዚያዊ አስተዳዳሪው አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የኤርትራ ሠራዊትን እና የአማራ ክልል ኃይሎችን ከትግራይ አስወጥቶ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

“ከፌዴራል መንግሥት ጋር ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ መተማመን ባይኖርም ከጊዜ ወደ ጊዜ መተማመኑን እያጠናከርን የተገኘው ሰላም የተሻለ ደረጃ ላይ የሚደርስበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንሰራለን። ሰላማችን ሳይደፈርስ፡ ግዛታችንና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት መመለስ አለብን በሚል ጠንካራ አቋም እየተንቀሳቀስን ነው” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ወቅታዊ ሁኔታውን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በትግራይ በኩል ያሉ ግዛቶችን በኃይል እናስመልስ የሚሉ ወገኖች አሉ ብለዋል።

“በኃይል ማስመለስ ይቻላል። ነገር ግን የፕሪቶሪያው ስምምነት ከእነ ብዙ ችግሮቹና እጥረቶቹ ከተቀበልን በኋላ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በፌደራል መንግሥት ዘንድ የስምምነቱ አፍራሽ ተደርገን እንዳንቆጠር መጠንቀቅ ያስፈልገናል” ብለዋል።

በትግራይ በኩል ምዕራብ ትግራይ እንዲሁም በአማራ በኩል ወልቃይት ጠገዴ የሚባለው አካባቢ በሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ቦታ ነው።

አካባቢው ከሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት በፊት በትግራይ ክልል ስር ይገኝ የነበረ ሲሆን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአማራ ኃይሎች ስር ይገኛል።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አካባቢውን ተቆጣጥረው የሚገኙ የአማራ ኃይሎች የትግራይ ተወላጆችን በኃይል እያፈናቀሉ ነው የሚል ሪፖርቶችን ሲያወጡ ቆይተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንቱ መግለጫቸው “ከሁሉ በላይ ሰላማችንን በማያቃውስ መንገድ የጀመርነውን ግንኙነት እያሳደግን ማስቀጠል ይኖርብናል” ብለዋል።

የሰብዓዊ ጥቃት የፈፀሙ አካላት ተጠያቂነት

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም በደል ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዚህ በፊት ገልጾ ነበር።

አቶ ጌታቸውም በትግራይ በተለይ ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን የፈጸሙት “በኢትዮጵያ መንግሥት የተጋበዙ የውጭ ኃይሎች ናቸው” ብለዋል።

እነዚህን በደሎች የፈጸሙትን ለፍርድ ለማቅረብ በማስረጃዎች የተደገፉ የፍትሕ ሂደቶች ሊኖሩ ይገባል ብለን እናምናለን ሲሉም አክለዋል።

“ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጉዳዩን በተደጋጋሚ ያነሳ ሲሆን የፌዴራል መንግሥቱም በዚህ ላይ የተለየ አቋም የለውም” ብለዋል።

“መታወቅ ያለበት እየሰራን ያለነው እኮ ወንጀል ፈፅመዋል ከምንላቸው ጋር ነው፡ ስለዚህ ተጠያቂነት እስካልተረጋገጠ ድረስ ከእነሱ ጋር አንሰራም ማለት ደግሞ አንችልም" ብለዋል።

መንግሥት የማያውቃቸው እስር ቤቶች

አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግሥት ያማያውቃቸው እስር ቤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

"የትግራይ ፍትህ ቢሮ ባደረገው ጥናት መሰረት ትግራይ ውስጥ መንግሥት የማያውቃቸው እስር ቤቶች አሉ።”

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰብዓዊ መብት ረገጣ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መጀመራቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው የመንግሥት ኣካላት ነን በሚል ሽፋን ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ሰዎችን እያፈኑ ገንዘብ የመቀበል የወንጀል ድርጊት በክልሉ እየፈጸሙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይህንን የወንጀል ድርጊት ለማጣራት ጊዜ ወስዶብናል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ “ከነገ ጀምሮ ለፍርድ ማቅረብ እንጀምራለን" ብለዋል።

የክልሉ ግዚያዊ አስተዳዳሪ እንዲሁም የክልሉን የፖሊስ ኃይል፣ የግለሰቦች አገልጋይ እንዳይሆን ከላይ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ መልሶ የማደራጀት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በክልሉ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር የፖለቲካ ድክመት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ውድቀት የሚመኙ የተደራጁ ግለሰቦች መኖራቸውን አስቀምጠዋል።

ከትግራይ-ባህር ዳር፤ ደሴና ሰመራ የጦር መሳሪያ የሚያዘዋውሩ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው በትግራይ የሌብነት ወንጀል እጅግ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል።

የእርዳታ እህል ዘርፈዋል የተባሉ ከ480 በላይ ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍን በተመለከተ

በትግራይ የሚገኙ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ጳጉሜ 2 2015 ዓ.ም. የሚጀመር እና ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው ነበር።

ይኹን እንጂ ይህ በትግራይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ የሚጠይቀው ሰልፍ እንዳይደረግ ፖሊስ ሰዎችን በኃይል በትኗል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የጠሩት ሰልፍ የታገደበት ዋነኛ ምክንያት በመቀሌ ያለው የጸጥታ ችግር መሆኑን አቶ ጌታቸው የገለጹ ሲሆን፣ ከዚያ ባሻገር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሕጋዊ መሠረት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል።

ይህን በተመለከተ አቶ ጌታቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ “ሰላማዊ ሰልፍ መፍቀድ ወይም መከልከል የሚባል ነገር እንደሌለ ከፓርቲዎቹ አመራሮች ጋር ተስማምተናል። ሆኖም የሰልፉን ቦታ መወሰን የፓርቲዎች ኃላፊነት አይደለም” ብለዋል።

“ሕጋዊ መሠረታቸውን በተመለከተ ሙግት ውስጥ ላለመግባት ተውነው እንጂ፣ እነዚህ ፓርቲዎች እኮ አሁን ባለው ምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት የቤት ውስጥ ስብሰባ ከመጥራት በስተቀር በአደባባይ ሰልፍ የመጥራት መብትም የላቸውም" ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በመቀለ ከተማ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ሲናገሩ፤ “ከአጎራባች አካባቢዎች የገባ ከፍተኛ የፈንጂ ክምችት አለ፤ ወረቀቶች በመበተን የተሳተፉ ግለሰቦች ተይዘዋል፤ ከፖሊስ ጋር ከተነጋግረን በኋላ የተፈቱ አሉ። ደግሞ የሦስት ቀን ሰልፍ የሚባል ነገር የለም፤ አመፅ ካልሆነ በስተቀር” ብለዋል።

"እድሉን ተጠቅመው ትግራይን ወደ ትርምስ ለመመለስ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ፤ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉን። የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አይደሉም” በማለት ለሁለት ሰዓታት በፈጀው መግለጫቸው ላይ አስረድተዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቀባይነት

አቶ ጌታቸው በመግለጫው የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የክልሉ ዞኖችንና ወረዳዎችን አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማስፋት አለመቻሉን አስረድተዋል።

አቶ ጌታቸው ግዜያዊ አስተዳደሩ ተቀባይነት እንዳይኖረው ጥረት የሚያደርጉ አመራሮች መኖራቸውን አክለው ተናግረዋል።

ወረዳዎች እና በታችኛው እርከን ያሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል እንዳይሆኑ የተደራጀ ንቅናቄ እንዳለም በግልጽ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው የሚመሩት ግዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል መንግሥቱ ያለው ባለው ግንኙነት እንቅፋት እየሆነበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው የፌደራሉ መንግሥቱ “መቀለን ጨምሮ በዞን እና በወረዳ መዋቅሩን ካልዘረጋ እና በብዙ መልኩ መስራት ካልቻለ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በተሟላ መልኩ ግንኙነት ማስቀጠል አይቻለኝም እያለ ነው” ብለዋል።

“የሆኖ ሆኖ… ዞን እና ወረዳዎች የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ማስተዳደር የለበትን የሚል እንቅስቃሴ በማንኛውም መልኩ መቆም አለበት" በማለት ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥት ለትግራይ የአንድ ዓመት በጀት ብቻ መድቦ በመጀመሪያ ዙር 3 ቢሊየን ብር መቀበሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

"ከዚህም ለሲቪል ሠራተኛው የከፈልነው የአራት ወር ደሞዝ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ሙሉ በሙሉ ለሲቪል ሰራተኛው ሳናወጣ ከ270 ሺህ በላይ ወታደሮችን ምግብ ማቅረብ ስለነበረብን ነው" ብለዋል።