“ከሕዝቡ እየተነጠለ ያለው ኃይል ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ደርሷል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ ኃይሎች ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ” ላይ ደርሰዋል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የተናገሩት የአገር መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርቶ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ዘመቻ እያካሄደ ባለበት ጊዜ ነው።
ካለፈው ሚያዚያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲበተኑ እና ኢመደበኛ ታጣቂዎች ትጥቅ እንደሚፈቱ ከተነገረ በኋላ በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች ከመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲያካሂዱ ነበር።
በአማራ ክልል ያለው ሁኔታም እየተባባሰ ሄዶ ከክልሉ መስተዳደር አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ ገብነት ጠይቋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ የፌደራሉን ሠራዊት በክልሉ ውስጥ ማሰማራቱ ይታወቃል።
ባለፉት ሳምንታት የክልሉን ዋና ከተማን ባሕር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እና አካባቢዎች ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭቶች ሲካሄዱ ሰንብተዋል። ሠራዊቱ ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጥሮ መረጋጋት ማስፈኑ የተገለጸ ቢሆንም አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሠራዊቱ እየወሰደ ባለው እርምጃ “ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑን እና “በአማራ ክልል የሕዝቡን የመብት ጥያቄ ካባ በማድረግ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት የተንቀሳቀሰው ኃይል ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ ውጤት ተመዝግቧል” ሲሉ ተናግረዋል።
ኤታማዦር ሹሙ ለመከላከያ ሠራዊቱ የመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ” ያሏቸው ኃይሎች በአሁኑ ወቅት ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
“ሠራዊቱ በአማራ ክልል ሰሞኑን የተከሰተውን እና ሸኔ ቀደም ሲል የፈጠረውን ችግር ለማስተካከል እየሠራ ነው” ሲሉ የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ በሁለቱም ኃይሎች የተፈጠረው ችግር ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ መድረሱን እና እየሰሩ ያሉት “የመለቃቀም ሥራ ነው” ብለዋል።
በአማራ ክልል ታጣቂዎች የክልሉን ፀጥታ ማወካቸውን እና “በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል በዘረፋ ተግባር ላይ የተሰማራና መንገዶችን በመዝጋት የሕዝቡን ሰላም የሚያውክ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱም ይህንን ችግር ለማስወገድ የመከላከያ ሠራዊቱ ተከታታይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመልክተው “አሁን ከሕዝቡ እየተነጠለ ያለውን ይህን ኃይል አቅሙን በማዳከም ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ተችሏል” ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ለወራት ሲካሄድ የቆየን ተቃውሞ እና ግጭትን ተከትሎ በአማራ ክልል ባለፈው ሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በስፋት የተከሰተው ግጭት ክልሉን አለመረጋጋት ውስጥ መክተቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ግጭቶች አስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ በአብዛኛው የክልሉ ክፍሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ውስጥ ከገቡ ወዲህ ከሐምሌ ወር ወዲህ ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውን የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያሰባሰበውን መረጃ ጠቅሶ አመልክቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ማክሰኞ ነሐሴ 23/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጨምሮም በኢትዮጵያ የመብቶች ጥሰት ተበራክተዋል ያለ ሲሆን በተለይ ደግሞ በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች እያሽቆለቆሉ መምጣታቸው አሳሳቢ ነው ብሏል።
በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ስለደረሰው ሰብአዊ ጉዳት መጠን በመንግሥት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ከመድረሱ በተጨማሪ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የጅምላ አስሮች መካሄዳቸውን የመብት ተሟጋቾች እና የታሳሪ ቤተሰቦች አመልክተዋል።












