በደብረ ታቦር ለቀናት በተካሄደ ግጭት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሆስፒታል ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Debre Tabor Communication
በአማራ ክልል፣ ደብረ ታቦር ከተማ ካለፍነው ቅዳሜ ነሐሴ 20/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ ውጊያ በደብረ ታቦር ሰላማዊ ዜጎች እንደተገደሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ገለጹ።
እስከ ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ዓ. ም. ረፋድ ድረስ በቀጠለው ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት እና ለጉዳት መዳረጋቸው እንዲሁም ደብረ ታቦር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላይ ጉዳት መድረሱም ተገልጿል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ፣ ግጭቱ ቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ ለቀናት መካሄዱን ገልጸው፤ በዚህም ቢያንስ 10 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በደብረ ታቦር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰሩ ሐኪም በበኩላቸው፣ በከተማዋ የተረጋጋ ሁኔታ ባለመኖሩ በግጭቱ በሰዎች ላይ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት በአሐዝ ማስቀመጥ እንደማይችሉ ገልጸው፣ ሰላማዊ ሰዎች ግን መጎዳታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በክልሉ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደብረ ታቦር “አሁን ላይ ስንት ሰው ተጎዳ፣ ስንት ሰው ሞተ የሚለውን በቁጥር ማስቀመጥ ከባድ ነው” ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሐኪሙ “እኛ ሆስፒታል ያሉ አስታማሚ እና የጥበቃ ሠራተኞችም ተመተዋል” ብለዋል።
“ወላድ ሊጠይቅ የመጣ ሰው እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ነው የተመታው። ቀዶ ሕክምና ተሠርቶለታል። የጥበቃ ሠራተኞች ቀላል ጉዳት ነው የደረሰባቸው” ሲሉም ሐኪሙ አክለዋል።
በተጨማሪም “የሆስፒታሉ በር ላይ የነበሩ አምስት አስታማሚዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሆስፒታሉ አካባቢ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 27 ወጣቶች ቆስለዋል” ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸወ ሰዎች በውጊያው ምክንያት ሕክምና ሳያገኙ እንደቆዩም ገልጸዋል።
“እስካሁን ሆስፒታል አልገቡም ነበር። አሁን ውጊያው ከከተማ ወጣ ስላለ ሆስፒታል ገብተው እርዳታ መስጠት ጀምረናል” ሲሉ ሐኪሙ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ሐኪሙ ጨምረውም በሆስፒታሉ ላይ ጉዳት በመድረሱ የሕክምና አገልግሎት መስተጓጎሉን እና ባለሙያዎችም ሥራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
“የሆስፒታሉ ክፍሎች መስተዋት ተሰባብሯል፣ መብራት መጠቀም አንችልም፣ የሕክምና ማሽኖች ያሉበት ቦታ በተኩሱ ጉዳት ደርሶበት የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች በመጠኑ ተጎድተዋል” ሲሉ ሐኪሙ የደረሰውን ጉዳት ገልጸዋል።
“የተተኮሰባቸው ክፍሎች ላይ አልጋዎች ተሰባብረዋል። ቀጥታ ተኩስ የነበረው ወደ ሆስፒታሉ ስለሆነ የተጎዱ ሰዎችም ይሁን ሌሎች ሕሙማንም መታከም አልቻሉም። ወላድም ብትመጣ የሚከታተል የለም፣ ቀዶ ሕክምና የሚሠራም የለም” ሲሉም አክለዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ቢያንስ 10 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ከቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ እስከዛሬ [ነሐሴ ሰኞ 22/2015 ዓ. ም.] ደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ ውጊያ ታካሂዷል። መከላከያ ከባድ መሣሪያ ይጠቀም ስለነበር ቤቶች ላይም ሆስፒታል ላይም አርፏል። እኔ በማውቀው 10 ሰዎች ሞተዋል፣ ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል” ሲሉ ነዋሪው ገልጸዋል።
“መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎችም ሞተዋል። [ሰኞ ነሐሴ 22/2015 ዓ. ም.] ከአራት ሰዓት በኋላ ግጭቱ ቆሞ አስክሬን ሲነሳ ነበር። አሁን ውጊያ የለም የተኩስ ድምጽም አይሰማም። መከላከያ ቤት ለቤት እየዞረ እየፈተሸ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ቢቢሲ የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎችን እና የሆስፒታል ሐኪሙን ያነጋገረው ሰኞ ከሰዓት በኋላ ነበር።
ቢቢሲ በደብረ ታቦር ከተማ ስለተከሰተው ግጭት ከአስቸኳይ ጊዜ አስፈፃሚው ዕዝ፣ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ጋብ ብሎ የነበረው በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት መልሶ ማገርሸቱ የተነገ ሲሆን፣ ከደብረ ታቦር በተጨማሪ በደብረ ማርቆስ እና በፍኖተ ሰላም ባለፉት ቀናት ግጭቶች ማጋጠማቸው ተነግሯል።
በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለሳምንታት በክልሉ የተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ባለው ውጊያ የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱ፣ የአካል ጉዳት መድረሱ እንዲሁም ንብረት መውደሙ እየተዘገበ ይገኛል።
ሆኖም በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ነሐሴ 21/2015 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ ክልሉ “ከነበረበት የፀጥታ ችግር እየተላቀቀ” እንደሆና “ወደተሟላ ሰላም ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤታማ” መሆኑን ገልጿል።
በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተለው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ተገኝቷል ያለውን ሰላም እና መረጋጋት ለማጠናከር “የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል” መግለጹ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በክልሉ ውስጥ “በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በተወሰዱ እርምጃዎች አብዛኞቹ የአማራ ክልል ዞኖች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል” ብሏል።
ጨምሮም “የተጀመረውን ሰላም እና መረጋገት ይበልጥ ለማጽናት እና አስተማማኝ ለማድረግ፣ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕዙ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል” ሲል በክልሉ ውስጥ የሚካሄደው ዘመቻ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ሲካሄድ የነበረው እና ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት በአብዛኛው መረጋጋት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ባለፈው ሳምንት ማስታወቁም አይዘነጋም።
ሆኖም ግን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደነበሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ መረጃዎች የጠቆሙ ሲሆን የቢቢሲም ምንጮችም በደብረ ታቦር ውጊያ ለቀናት መካሄዱን ገልጸዋል።
ለሳምንታት በግጭት ውስጥ የቆየው የአማራ ክልል ክልል ምክር ቤት በዶ/ር ይልቃል ከፋለ ምትክ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ነሐሴ 19/2015 ዓ. ም. መሾሙ አይዘነጋም።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ ከአማራ ክልል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።
በውጊያው የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት መቀጠፉ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸው፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸው ተገልጿል።












