የአማራ ክልል በአምስት ዓመት ውስጥ ስድስተኛውን ርዕሰ መስተዳድር ሾመ

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Media Corporation

ለስድስት ወራት በሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት በዶክተር ይልቃል ከፋለ ምትክ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ነሐሴ 19/ 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ላይ ነው አዲስ ርዕሰ መስተዳድር እንደሾመ የተዘገበው።

በክልሉ በአምስት ዓመት ውስጥ ስድስተኛ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አረጋ በክልሉ በሥራ ፈጠራ እና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊነትም ሲያገለግሉ ነበር።

ክልሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው በምትካቸው አቶ አረጋ ከበደን አዲስ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ምክር ቤቱ መሾሙ ያሳወቀው።

መስከረም 20/2014 ዓ.ም የአማራን ክልል እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት ዶክተር ይልቃል የመልቀቂያ ጥያቄያቸው በምክር ቤቱም ተቀባይነት አግኝቷል።

ለ23 ወራት ክልሉን በመምራት ያገለገሉት ዶክተር ይልቃል ለፓርቲያቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገቡ ስምንት ወራት እንደሆናቸው ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቅሰዋል።

ሆኖም ወቅታዊ ሁኔታዎች ለመቆየት እንዳስገደዳቸው ጠቁመው “በቀውስ ወቅት ወደ ሥልጣን መጥቶ በቀውስ ወቅት ኃላፊነትን መልቀቅ ህመሙን የማውቀው እኔ ብሆንም የምችለውን ሁሉ ግን ሰጥቻለሁ፤ ጥያቄዬንም ፓርቲዬ ተቀብሎኛል” ብለዋል።

“ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠኝን ኃላፊነት በገባኝ እና በምችለው ልክ ተወጥቻለሁ” ያሉት ዶክተር ይልቃል ላለፉት ሁለት ዓመታት ማኅበራዊ፣ ቤተሰባዊ እና የጤና ችግሮቻቸውን ተቋቁመው ማገልገላቸውን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ መምከሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ መንግሥታዊ ሥርዓት መቅደምም እንዳለበት ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል።

“ከመንግሥት ውጭ የታጠቀ ኃይል መኖር መጨረሻው እንደ የመን እና ሶማሊያ መሆን ነው። ከሌሎች መማር ካልቻልን ከማን ልንማር እንችላለን” በማለት ተናግረዋል።

ምክር ቤት የክልሉን የጸጥታ ችግር ከገመገመም በኋላ ፈጻሚ አካሉን አደረጃጀት መቀየር እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱም ተነግሯል።

አዳዲስ ሹመቶች

የአማራ ክልል ምክር ቤት ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የተለያዩ ሹመቶችንም በማጽደቅ አስቸኳይ ጉባኤውን አጠናቋል።

በዚህም መሠረት ሹመታቸው የጸደቀላቸው

  • አቶ አብዱ ሁሴን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
  • ዶክተር አህመዲን መሐመድ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እንዲሁም የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር ድረስ ሳህሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ
  • አቶ ደሳለኝ ጣሰው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር ጋሻው አወቀ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ
  • አቶ ብርሃኑ ጎሽም የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር መንገሻ ፈንታው የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር ስቡህ ገበያው የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊ
  • አቶ ክብረት አህመድ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ
  • አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ
  • ዶክተር ደመቀ ቦሩ የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ

አዲስ ከተሾሙት ኃላፊዎች ውጪ ያሉ ሌሎቹ የክልሉ ተቋማት ኃላፊዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ ስለመወሰኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በክልሉም ወጥ የሆነ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷልም ተብሏል።

ክልሉ የገጠሙት ተግዳሮቶች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሕዝቡን የሚያስከፉ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተናገሩት ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል፣ አመራሩን ማውረድ እንዲሁም ፓርቲው በምርጫ እንዲቀጣ ማድረግ እንጂ “ኃይል በፍጹም አማራጭ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ውስብስብ እንደሆነም ጠቅሰው ወጥ ዓላማ፣ የጋራ ራዕይ፣ በቂ የትግል ስልት እና የሌሎችን አሰላለፍ ያልተረዳ በመሆኑ ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲወሰን ጥሪ ያቀረበውም ግጭቱ በጥቂት ቀናት ብቻ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ተከትሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

የአማራ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ባለፉት ዓመታት በርካታ ርዕሰ መስተዳደሮች የተፈራረቁበት መሆኑ ይታወቃል።

እነዚህም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ናቸው።

ዶክተር ይልቃል የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርነት የተረከቡት በአሁኑ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ከሆኑት አቶ አገኘሁ ተሻገር ነበር።

በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለሌላ ኃላፊነት መታጨታቸውን ተከትሎ ለአማራ ክልል ምክር ቤት መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ ነበር አቶ አገኘሁ የተሾሙት።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ ተፈፀመ በተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች የአዴፓ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ከተገደሉ አንድ ወር በኋላ አቶ ተመስገን ክልሉን እንዲመሩ መደረጋቸው ይታወሳል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ላቀ አያሌው ክልሉን በጊዜያዊነት ለጥቂት ጊዜ መርተው ነበር።

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲደረጉ የነበሩ ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ ከአማራ ክልል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የቀረበለትን ጥያቄ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

በክልሉ በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ አስፈላጊ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተደረገው ውጊያ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ሲካሄድ የነበረው እና ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት በአብዛኛው መረጋጋት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል።