ነፍጥ አንስተው እየተዋጉ ያሉ በሙሉ ለሰላም እና ዕርቅ ቅድሚያ እንዲሰጡ ፓትርያርኩ ጥሪ አቀረቡ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ

የፎቶው ባለመብት, EOTC

በኢትዮጵያ ነፍጥ አንስተው እየተዋጉ ያሉ በሙሉ የጦር መሳሪያቸውን አውርደው ለሰላም እና ዕርቅ ቅድሚያ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ።

ፓትርያርኩ የሰላም ጥሪውን ያቀረቡት በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ዛሬ አርብ ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

“በአራቱም ማዕዘናት ነፍጥ ያነሳችሁ በሙሉ ያነገባችሁትን ገዳይ መሣርያ አውርዳችሁ ለሰላም እና ለዕርቅ ቅድሚያ በመስጠት ለአንዲት አገራችሁ ሕልውና ተገዢዎች እንድትሆኑ” ሲሉ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ መንግሥትም ባስተላለፉት መልዕክት ልበ ሰፊ በመሆን ሁሉንም አካላት ለውይይት እንዲሰሰብም ለምነዋል።

ፓትርያርኩ “በዘመናችን የሰላምን እና የነጻነትን ትርጉም ባለመረዳት” ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እየተላለቁ እና ሕዝቦቿም በሰላም መኖር እንዳይችሉ ሆነዋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት መቋጨቱን ተከትሎ የተስፋ ጭላንጭል መታየቱን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እያገረሸ ያለው ጦርነት “አስደንጋጭ እና አሳዛኝ” ክስተት ነው ብለዋል።

“በመርከቡ ላይ ማዕበል ቢነሣ ይህ የካፒቴኑ ጉዳይ፤ ይህ የመንገደኛው ነው አይባልም። በታሪክ አጋጣሚም ኢትዮጵያ በምትባል መርከብ ላይ ስለተሳፈርን ራሳችን ገዳይ፣ ራሳችን ሟች ሁነን አብረን መዋጋት እንጂ አብረን መኖር ያቃተን ሕዝብ በመሆን፤ አገራችንን የዓለም መሳለቂያ ያደረግንበት ይህ ማዕበል የሁላችንም ዕዳ ነውና መፍትሔውን በጽኑ መፈለግ ይገባናል” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ጦርነት እና ረሃብ እየተፈራረቀባት በርካቶች መድቀቃቸው እና ለመከራ መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪም በርካታ ዘግናኝ ክስተቶች መስተናገዳቸውን ገልጸዋል።

“የሰውነት ክብር ወድቆ ሰው ቁልቁል ሲሰቀል፣ በሕይወት ሳለም በእሳት ሲቃጠል፣ በነፍሰጡር እናቶች ላይ በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ ግፍ ሲፈጸም ማየቱ” ልብን የሚሰብር መሆኑ እና ሐዘናቸውም ጥልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በርካቶች ጥላሸት የተቀባቡበት የቃላት ውርወራ እንዲሁም የደም አፋሳሽ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን በመጥቀስ ይህም ትምህርት ሊሆንም ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ሽማግሌዎችም ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልዕክትም የአስታራቂ ሚና እንዲጫወቱ እና ለሰላም ጠበቃ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።

“በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያላችሁ ሽማግሌዎች፣ ሽምግልናችሁ ለዚህ ቀን ካልሆነ ለመቼም አይሆንምና በአገሩም ሽማግሌ የለም ወይ? መባሉ በሰማይም በምድርም ያስወቅሳል” ብለዋል።

በተጨማሪም በውጭ አገር ለሚኖሩም ኢትዮጵያውያን በርካቶች “በእሳት ሲጠበሱ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ስላልሆነ” ሰላም እንዲሰፍን እንዲሰሩም አሳስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች እንዳደረጉት ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ነው ፓትርያርኩ ጥሪ ያቀረቡት።

የቤተ ክርስቲያኗ አመራሮችም ከዚህ ቀደም መፍትሔ መሆን ሲገባ የችግሩ አካል ሆነዋል መባላችውን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ አስታራቂ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

2015 ዓ.ም. ሊጠናቀቅ በቀሩት ጥቂት ቀናት አሁን ያለው ችግር ወደሚቀጥለው ዘመን እንዳይሻገር “ቀጣዩን አዲስ ዓመት በሰላም ለመቀበል እንችል ዘንድ ከጉልበት ሳይሆን ከልብ ሽብረክ በማለት እርቅ ይውረድ፣ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ፣ ሰላም ይታወጅ ምድሪቱንም እናሳርፋት!” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

በአማራ ክልል ከሰሞኑ ያገረሸው ግጭት የተጀመረው ታጣቂዎች በመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ “ዘግናኝ የሚባል ጥቃት መክፈታቸውን” ተከትሎ እንደሆነ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ከሰሞኑ ማነገራቸው ተዘግቧል።

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት መባባስ ተከትሎ በክልሉ በዋነኝነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነ እና እነዚህም እስሮች አብዛኛዎቹ የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።