የአማራ ክልልን “ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ወታደራዊው ኦፕሬሽን እንደሚቀጥል” ተገለጸ

ጎንደር

የፎቶው ባለመብት, gove. comm./fb

የምስሉ መግለጫ, ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል ከተባሉት ከተሞች መካከል አንዷ ጎንደር

በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም የሚከታተለው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በክልሉ ተገኝቷል ያለውን ሰላም እና መረጋጋት ለማጠናከር የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እንዳለው በክልሉ ውስጥ “በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዙር ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በተወሰዱ እርምጃዎች አብዛኞቹ የአማራ ክልል ዞኖች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል” ብሏል።

ጨምሮም “የተጀመረውን ሰላም እና መረጋገት ይበልጥ ለማጽናት እና አስተማማኝ ለማድረግ፣ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕዙ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷል” ሲል በክልሉ ውስጥ የሚካሄደው ዘመቻ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ ሲካሄድ የነበረው እና ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት በአብዛኛው መረጋጋት ማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል።

ምንም እንኳን ሁኔታዎች ቢረጋጉም የሰሞኑ ግጭቶች እንዲሁም የጸጥታውን እጦት ተከትሎ የቆሙ የሰብዓዊ እርዳታዎች መቆም የዜጎችን ችግር ሊያባብስ እንደሚችልም ነው ተቋሙ ነሐሴ 16/ 2015 ባወጣው ሪፖርት የገለጸው።

በፈታኝ ሁኔታዎችም ውስጥ ቢሆን አጋር የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች በአማራ ክልል ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ እየሰሩ ይገኛሉም ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በትልልቅ ከተሞች ሲካሄዱ የነበሩ ግጭቶች ቆመው ከተሞቹ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የገቡ ሲሆን፣ ግጭቶች እና ጥቃቶች ከከተሞች ባሻገር በሚገኙ የክልሉ አካባቢዎች እየተካሄዱ መሆናቸው እየተዘገበ ነው።

የተለያዩ ወገኖች በአማራ ክልል የተከሰተው አሳሳቢ የፀጥታ መደፍረስ እና ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ እየጠየቁ ሲሆን፣ መንግሥትም ለዚሁ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጾ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 17/2015 ዓ.ም. እንዳስታወቀው እየተወሰደ ባለው እርምጃ፣ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በገቡ አካባቢዎች “የድርጊቱ ዋና ዋና ተዋናዮች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ” እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ማንነትን የለየ የጅምላ አስር እየተካሄደ መሆኑን የመብት ተሟጋቾች እና ቤተሰቦች እየተናገሩ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤት አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

ሰፊ የእርሻ ሥራ በሚከናወንበት የክረምት ወቅት በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የግብርና ተግባራ መስተጓጎል የገጠመው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዕዙ አመልክቷል።

በዚህም ከአንዳንድ ቦታዎች በስተቀር “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም አርሶ አደሮች ወደ መኸር አዝመራ ሥራ እየተመለሱ ናቸው” በማለት የግብርና ግብአቶችም እየተጓጓዙ መሆናቸውን ገልጿል።

ለወራት ሲካሄድ የቆየን ተቃውሞ እና ግጭትን ተከትሎ በአማራ ክልል ባለፈው ሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በስፋት የተከሰተው ግጭት ክልሉን አለመረጋጋት ውስጥ መክተቱ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በመደበኛው ሕግ የማስከበር ሥነ ሥርዓት ለመቆጣጠር ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

በመጀመሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ፣ ቀጥሎም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ያፀደቁት ለስድስት ወራት የሚቆይ በክልሉ እና እንደአስፈላጊነቱ በቀሪው የአገሪቱ ከፍሎች ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. ተደንግጓል።

ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ የፌደራሉ የፀጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ የተሰማሩ ሲሆን፣ በዚህም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱ ውጊያዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ዕዙ፣ የሆስፒታል ምንጮች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።