ገለልተኛ መርማሪዎች ወደ አማራ ክልል እንዲገቡ መንግሥት እንዲፈቅድ አምነስቲ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአማራ ክልል ከተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት መደረጋቸውን ተከትሎ ገለልተኛ መርማሪዎች ወደስፍራዎቹ እንዲገቡ መንግሥት ፍቃድ እንዲሰጥ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ጠየቀ።
በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው አምነስቲ ትናንት ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
በዚህ ሳምንት በክልሉ በተፈጸመ የአየር ጥቃት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን በርካታ ሚዲያዎች መዘገባቸውንም ድርጅቱ ጠቅሷል።
በፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች መገደላቸውንና ከ50 በላይ ሰዎችም እንደቆሰሉ የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጥቃቶቹን በተመለከተ አንዳንዶች የደረሰው በከባድ መሳሪያ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተፈጸመ መሆኑን ነው ለቢቢሲ የገለጹት።
አምነስቲ በፍኖተ ሰላም፣ በባህር ዳር እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች የጅምላ ግድያዎች እና ሞቶች መፈጸማቸውን መረጃዎች እንደደረሱት ጠቅሶ ተጨማሪ ምርመራ ሊደረግባቸው እንደሚገባም ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች የሚያጣራው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን፣ ሌሎች ገለልተኛ የምርመራ አካላት እና ነጻ ሚዲያዎች እነዚህን ውንጀላዎች በጥልቀት ለመርመር ይቻል ዘንድ ያልተገደበ ፍቃድ እንዲሰጣቸው የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ተናግረዋል።
"መንግሥት እና የጸጥታ ኃይሎች የሰዎችን ሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስጠበቅ አለባቸው" ሲል ቲገሬ መናገራቸውም በመግለጫው ሰፍሯል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት መባባስ ተከትሎ በክልሉ በዋነኝነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ በቁጥጥር ሥር የማዋል፣ የሰዓት ገደብ እላፊ የመጣል፣ የመዘዋወር ነጻነትን የመከልከል እንዲሁም መሰባሰብን የሚከለክል ሰፊ ሥልጣንን የሚሰጥ እንደሆነም አምነስቲ ገልጿል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የፌደራል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መደበኛ ባልሆኑ የማቆያ ማዕከላት ማሰራቸውን ማስታወቁንም በአምነስቲ መግለጫ ተካቷል።
በአዲስ አበባ በእስር ላይ የሚኙ ግለሰቦች ጠበቆች እና የቤተሰብ አባላት ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን እና የሕግ አማካሪ የማግኘት መብት መነፈጋቸውንም መናገራቸውን አምነስቲ በመግለጫው አስፍሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነና እነዚህም እስሮች አብዛኛዎቹ የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መምሪያ ዕዙ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።
በተጨማሪም ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ ያለው የኢንተርኔት መቋረጥ የነዋሪውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብት የሚጋፋ መሆኑንም ነው የጠቀሰው።
በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በርካቶች ለጅምላ እስራት፣ ክስ ሳይመሰረትባቸውና ፍርድ ቤት ሳይቆዩ ለረጅም ጊዜ እንዲታሰሩ እንዲሁም በኮሚዩኒኬሽን ላይ ሕገወጥ እገዳዎች እንዲፈጸሙ ማድረጉንም አምነስቲ ጠቅሷል።
የፋኖ ሚሊሻ እና የአማራ ልዩ ኃይል ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር አጋር በመሆን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት እስከተፈረመበት ድረስ ለሁለት ዓመት ያህል ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተዋግተዋል።
ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ሚሊሻ ከፌደራል ኃይሎች ጋር በመተባበር በምዕራብ ትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑንም አምነስቲ እና ሂውማን ራይትሰ ዋች ያወጡትም ሪፖርት በዚህ መግለጫ ተጠቅሷል።
በአማራ ክልል ልዩ ኃይል መልሶ ከማደራጀት ጋር ተያይዞ የተነሳው ውጥረት አገርሽቶ ወደ ግጭት ያመራ ሲሆን እነዚህም ግጭቶች ተባብሰው ከሰሞኑ በተለያዩ የአማራ አካቢዎች ውጊያዎች ተደርገዋል።
በአማራ ክልል ከሰሞኑ ያገረሸው ግጭት የተጀመረው ታጣቂዎች በመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ “ዘግናኝ የሚባል ጥቃት መክፈታቸውን” ተከትሎ እንደሆነ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ከሰሞኑ መናገራቸው ተዘግቧል።
በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸው ተገልጿል።
በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።












