የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር በመተማመኛ ድምፅ እጦት ከሥልጣን ተነሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሷ ባይሩ በምክር ቤት የመተማኛ ድምፅ ከተሸነፉ በኋላ ፈንሳይ ወደ አዲስ የፖለቲካ ቀውስ ገብታለች።
364 ለ194 ድምፅ የተሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማክሰኞ የመንግሥታቸውን የሥራ መልቀቂያ ለፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ደግሞ አዲስ ተተኪ ይመርጣሉ።
የማክሮ ፅህፈት ቤት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚቀጥሉት ቀናት ይታወቃል ብሏል።
የማክሮን ቀንደኛ ተቀናቃኝ የሆነው ግራ ዘመም አንቦውድ ፓርቲ ፕሬዝዳንቱም እንዲለቁ ግፊት እያደረገ ነው።
ፈረንሳይ በሁለት ዓመታት ውስጥ አምስተኛዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሾም ጫፍ ላይ ስትሆን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹም ሽረት የፕሬዝዳንት ማክሮንን ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ያለመረጋጋት እና ስምምነት ማጣት አሻራ ሆኖ ታይቷል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ቦይሩ ከሥልጣን መውረድ ምክንያት የሆነው የፈረንሳይ የእዳ ጉዳይ ሲሆን፤ በ2026 በጀት ዓመት 44 ቢሊዮን ዩሮ ለመቆጠብ ሲሉ ሁለት ብሔራዊ በዓላት እንዲሰረዙ እና የማኅበራዊ ዋስትና እና የጡረታ ክፍያዎች እንዲቋረጡ ሀሳብ አቅርበዋል።
በአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አብላጫ ወንበር የሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግራ ዘመም እና አክራሪ የቀን ዘመም ፓርቲዎች ተባብረውባቸው እጣ ፈንታቸውን ወስነዋል።
የፖለቲካ ተንታኞች የመተማኛ ድምፅ ለመስጠት አስፈላጊ እንዳልነበር በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ወራት ድጋፍ ማሰባሰብ ይችሉ ነበር ብለዋል።
የመተማመኛ ድምፁ ከመሰጠቱ በፊት ንግግር ያደረጉት ቦይሩ ከፖለቲካ ይልቅ ታሪክ ለመስራት መወጠናቸውን ለምክር ቤት አባላቱ ጠቁመው፤ ፈረንሳይ የገንዘብ ነፃነቷን ብታጣ መጭው ትውልድ እንደሚጎዳ ተናግረዋል።
"ለእዳ እጅ መስጠት በኃይል እጅ ከመስጠት ጋር ተመሳሳይ ነው" ሲሉ ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቶችን ወደ ባሪያነት የሚወስድ ነው" ብለዋል።
"መንግሥትን ለማውረድ ሥልጣን ይኖራችሁ ይሆናል። ነገር ግን ገሀዱን ዓለም ማምለጥ አይቻልም" ሲሉም ለምክር ቤት አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይሁን እንጂ ይህን የማስጠንቀቂያ መልዕክታቸው ከቁብ ያልቂጠሩት የምክር ቤት አባላት የራሳቸውን እና የማክሮንን ኃላፊነት ለመሸፋፈን ሞክረዋል ብለዋል።
ቦይሩ ባለፈው ታኅሳስ ሚሼል ባርኒየር በጀታቸውን በምክር ቤት ማፀደቅ አለመቻላቸውን ተከትሎ ነበር ሥልጣን የተረከቡት።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ወግ አጠባቂ የሆኑት ባርኒየር እና መሀከለኛ ፖለቲካ አራማጅ የሆኑት ባይሩ ስኬት ከራቃቸው በኋላ ግራ ዘመም ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ማክሮን ምንአልባትም የቅርብ አጋሮቻቸው የሆኑትን የመከላከያ ሚኒስትር ሰባስቲያን ሉኮሩኑ፣ የሥራ ሚኒስትር ካትሪን ቫውቲን አሊያም የፋይናንስ ሚኒስትር ሆኑትን ኤሪክ ሎምባርድን ሊሾሙ ይችላሉም እየተባለ ነው።















