እስካሁን ድረስ እያወዛገበ ያለው የአውሮፕላን ፈጣሪ እና የፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ

የራይት ወንድሞች፣ ሳንቶስ ዱሞንት እና 14-ቢስ ምስሎች ኮላዥ
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አውሮፕላንን የፈጠረው ማን ነው? ቀላል ጥያቄ ሊመስል ይችላል።

ግን አይደለም፤ እውነቱን ለመናገር የመቶ ዓመት ውዝግብ መነሻ ጥያቄ ነው።

በርካታ አሜሪካውያን የብስክሌት መካኒኮቹ እና ራሳቸውን ያስተማሩት መሃንዲሶቹ ወንድማማቾቹ ኦሊቨር እና ዊልበር ራይት በ1903 የመጀመሪያውን ተከታታይ በረራ ያደረጉ የአቪዬሽን አባቶች እንደሆኑ ያምናሉ።

በሌላ ወገን ደግሞ ብዙ ብራዚላውያን ይህ ክብር እና ማዕረግ የሚገባው በ1906 በፓሪስ በዓለም አቀፍ የኤሮናቲካል ፌዴሬሽን የተረጋገጠውን በረራ ያከናወነው የባለጸጋ የቡና አምራቾች ቤተሰብ ወራሽ የሆነው አልቤርቶ ሳንቶስ ዱሞንት ነው ብለው ያምናሉ።

ታዲያ ማን ነው ትክክለኛ?

ሳንቶስ ዱሞንት በፓሪስ ለመጀመርያ ጊዜ ከበረረባት 14-ቢስ አውሮፕላኑ ጋር

የፎቶው ባለመብት, National Library of France

የምስሉ መግለጫ, ሳንቶስ ዱሞንት በፓሪስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከበረረባት 14-ቢስ አውሮፕላኑ ጋር

ሳንቶስ ዱሞንት፡የመጀመሪያው ይፋዊ በረራ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች የሰውን ልጅ የረጅም ጊዜ የመብረር ህልም ማሳካት የሚችል በሞተር የሚንቀሳቀስ ማሽን ለመሥራት እየሞከሩ ነበር።

ብዙዎቹ ወደ ፓሪስ ይጎርፉ ነበር።ፓሪስ ቀደምት የአቪዬሽን ፈጠራዎች መገናኛ ቦታ ነበረች። ስለዚህ ብዙ የበረራ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አውሮፕላኖችን ለመሥራት ወደዚያ ያመሩ ነበር።

ከተማዋ እንደ ብረታ ብረት፣ ሜካኒክስ፣ ፊዚክስ እና ኬሚስትሪ ባሉ የምርምር ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ጥሩ የምህንድስና ትምህርት ቤቶች እና መዋዕለ ነዋይ ነበራት።

ፈረንሳያዊው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ዣን ፒየር ብሌይ "የነበረው ስሜት የጊዜ ጉዳይ ነው የሚል ነበር" ብለዋል።

በወቅቱ የአቪዬሽን አድናቂዎች በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን በረራ ለማድረግ ዝርዝር ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ይህም ያለምንም እገዛ አኮብኩቦ የሚነሳ አውሮፕላን (ማለትም ምንም ዓይነት ማስወንጨፍያ ሳይኖር) እና የሚታይ እና የተመዘገበ ተከታታይ በረራ ማድረግ ናቸው።

እናም እንደ አውሮፓውያኑ ኅዳር 12/1906 ሳንቶስ ዱሞንት 14-ቢስ በተባለው አውሮፕላን በፓሪስ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት በ220 ሜትር ከፍታ ላይ በመብረር ሁሉንም መስፈርቶች አሟልቷል።

በቀጣዩ ዓመት የብራዚሉ አውሮፕላን አምራች ዴሞዜል (Demoiselle) የተሰኘ አዲስ ሞዴል አወጣ። እርሱም በዓለም ላይ የመጀመሪያው ቀላል፣ በብዛት የተመረተ አውሮፕላን ሆኖ ተመዘገበ።

ዴሞዜል በበረራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴሞዜል የመጀመሪያዋ በብዛት የተመረተች አውሮፕላን ነች

ማስረጃዎችን እንመልከት

በ1908 ነበር የራይት ወንድማቾች (ራይት ብራዘርስ) ከአምስት ዓመት በፊት አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ያበረርነው እኛ ነን ብለው ተናገሩ።

ፈረንሳዮች እጅጉን ተገረሙ።

በዩናይትድ ስቴትስ እና በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ የበረራ ክበቦች መካከል በነበረው የማያቋርጥ የደብዳቤ ልውውጥ ምክንያት ለተወሰነ ሰዓት መሬንት ለቅቆ በአየር ላይ እየተንሳፈፈ የሚቆይ የመጀመሪያውን አውሮፕላን ለመሥራት ፉክክር እንዳለ ያውቃሉ።

ግን አውሮፓውያን ስለ ራይትስ ወንድማማቾች ከሰሙ ዓመታት አልፈው ነበር።

ወንድማማቾቹ ግን የባለቤትነት መብታቸው እስኪጸድቅ ድረስ በመጠባበቅ ላይ እንደነበሩ እና ሀሳባቸው እንዳይሰረቅ በመፍራት መዘግየታቸውን በመግለጽ ተከራክረዋል።

እውነታው ግን በሰሜን ካሮላይና ውስጥ በኪቲ ሃውክ እአአ በታኅሣሥ 17/1903 በአየር ላይ ሲበርሩ እንዳዩ የተናገሩት አምስት ሰዎች ብቻ ናቸው።

ለዚህም ማስረጃ ሆነው ከቀረቡት መካከል የቴሌግራም መልዕክት፣ ጥቂት ፎቶግራፎች እና የወንድማማቾቹ የዕለት ማስታወሻ ይገኙበታል።

የብራዚል የአስትሮኖሚ እና ተዛማጅ ሳይንስ ሙዚየም የቀድሞ ዳይሬክተር ሄንሪክ ሊንስ ደ ባሮስን የመሳሰሉ ሳይንቲስቶች ኦርቪል ራሱ ነፋሱ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደሚነፍስ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ እንደፃፈ ይከራከራሉ፤ ይህ ፍጥነት ደግሞ ያለ ሞተር እርዳታ አውሮፕላኑን ለማንሳት በቂ ነበር ።

ለራይት ወንድማማቾች የሚሟገቱ በዚህ አይስማሙም።እንዲሁም የተሻሻሉ በራሪዎች 14-ቢስ የፓሪስ ሰማይ ላይ ከመቅዘፏ በፊት በ1904 እና 1905 መካከል ተሠርተዋል ይላሉ።

እአአ በታሕሳስ 17/1903 ለመጀመሪያ ጊዜ የራይት ወንድማማቾች የበረራ ሙከራ ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Library of Congress

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ1903 ለመጀመሪያ ጊዜ የራይት ወንድማማቾች የበረራ ሙከራ ሲያደርጉ

በስሚዝሶኒያን ናሽናል ኤር ኤንድ ስፔስ ሙዚየም አስተባባሪ እና ስለ ራይት ወንድማቾችች በርካታ መጽሐፍትን የጻፉት የታሪክ ምሁር ቶም ክሩክ "ያን ዕለት ጠዋት (ታኃሣሥ 17/1903) የራይት ወንድማማቾች በልባቸው አሁን ችግሩን ፈትተነዋል ብለው እስኪሰማቸው ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚገባ በርረዋል" ብለዋል።

"ብዙ ማስተካከያ ማድረግ ነበረባቸው፤ ነገር ግን አውሮፕላን ሠርተው መብረር ችለዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላ እስከ 1908 ድረስ የመጀመሪያው ሆነው ለመታወቅ ዘመቻ እስኪጀምሩ ድረስ መደረግ የነበረባቸው ማስተካከያዎች ሁሉ በድብቅ ሲሠሩ የነበረ ይመስላል።

የራይት ወንድማማቾች ወደ አውሮፓ ለጉብኝት ሄደው እንደ ፈረንሳይ እና ጣሊያን ባሉ አገራት ከ200 በላይ ማሳያ በረራዎችን፣ በአንድ በረራ እስከ 124 ኪሎ ሜትር ከፍ ብለው በመብረር አድርገዋል።

"የአውሮፓ ሮያሊቲ በአውሮፕላኑ ውስጥ ከዊልበር አጠገብ እንዲቀመጥ ጠየቀ። እንደ ክብር ይቆጠር ነበር" ይላሉ ፕሮፌሰር ብሌይ።

እናም ያኔ ነው እንደ ፈረንሣይ አቪዬሽን መሥራቹ ፈርዲናንድ ፌርበር ያሉ ሰዎች፣ተንቀሳቃሽ አውሮፕላን በአንድ ጀምበር ሊፈጠር እንደማይችል በመግለጽ፣ ራይትስ የመጀመሪያው ነን ሲሉ ያቀረቡትን ጥያቄ የተቀበሉት።

ግራፊክስ

ማስወንጨፍያዎች (The catapult)

በአውሮፓ ለዕይታ የበቁት የተሻሻሉ የሚበሩ አውሮፕላኖች ምንም ጎማ ስላልነበራቸው ለማኮብኮብ የሚያስወነጭፋቸው ነገር ያስፍለግ ነበር።

ይህ ትልቅ የክርክር ነጥብ ሆኗል።

ተቺዎች የአውሮፕላኑ ሞተር በቂ አቅም ስላልነበረው ማሽኑ የበረረው በማስወንጨፍያው (ካታፑል) እገዛ ነው ይላል።

ሌሎች ደግሞ ማስወንጨፍያው ጥቅም ላይ የዋለው ወንድማማቾቹ ከየትኛውም ቦታ ላይ ለመነሳት ስለፈለጉ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ነገር ግን የታሪኩ ውስብስብነት ይህ ብቻ አይደለም። ሳንቶስ ዱሞንት እና የራይት ወንድማማቾች ብቻ አልነበሩም የበረራ ጀማሪዎች እኛ ነን የሚሉት።

በአሜሪካ የሚኖረው ጀርመናዊው ጉስታቭ ዌይስኮፕ የአቪዬሽን መሥራች ነኝ ሲል ይከራከራል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የሚኖረው ጀርመናዊው ጉስታቭ ዌይስኮፕ የአቪዬሽን መሥራች ነኝ ሲል ይከራከራል

በአሜሪካ ይኖር የነበረው ጀርመናዊው ጉስታቭ ዌይስኮፕ እአአ በ1901 በረራ አድርጎ ነበር ተብሎ ይታመናል።

ኒውዚላንዳዊው ሪቻርድ ፒርስ በመጋቢት 1903 አውሮፕላን እንዳበረረ ተመዝግቧል።

እንዲሁም ጆን ጉድማን እና ቤተሰቡ ምንም እንኳ በሞተር ባይንቀሳቀስም በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ሆዊክ እአአ ከ1871 ቀድም ብሎ በዓለም የመጀመሪያውን የበረራ አባላት የነበሩትን አውሮፕላን እንዳበረረ መረጃዎች አሉ።

የተሳፋሪዎች መንሳፈፊያ ዛሬም ድረስ ለመታሰቢያነት ተቀምጧል።

በዚህ ምክንያት አንዳንድ የአቪዬሽን ባለሙያዎች አውሮፕላንን ማን ፈጠረው የሚለው አጠቃላይ ውይይት ትርጉም የለሽ ነው ብለው ይከራከራሉ።

ለ25 ዓመታት ያህል የጄን ኦል ዘ ዎርልድ ኤርክራፍት ዋና አዘጋጅ የነበረው ፖል ጃክሰን "አንድ ቀን አንድ ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ፣ ሥዕል ሠርቶ 'ይህ አውሮፕላን ነው የሚሠራው!' በማለት በድንገት የተፈጠረ ፈጠራ አይደለም" ይላል።

አክሎም "ይህ የበርካቶች ጥረት ውጤት ነው፣ አብረው በሚሠሩ በርካታ ሰዎች የተደረገ የቡድን ጥረት ነበር።"

የእውቅና እሽቅድምድም

ጃክሰን የአቪዬሽን ፈር ቀዳጆቹ ሳንቶስ ዱሞንት፣ ዌይስኮፕፍ እና ሌሎችም ካገኙት የበለጠ እውቅና ይገባቸዋል ብሎ ያምናል።

የብሪታኒያው የአቪዬሽን ስፔሻሊስቱ "አሁንም ግን ትልቅ ስም ያላቸው እና ከፍተኛ ተከፋይ ጠበቃ ያላቸው ሰዎች ናቸው እውቅናውን የሚያገኙት" ባይ ነው።

"አሳዛኙ ነገር በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹን ፈጠራዎችን ብንመለከት፣ ብዙውን ጊዜ እውቅናውን የሚያገኙት የማይገባቸው ሰዎች ናቸው" ይላል።

ስልክን እንደፈጠረ የሚነገርለትን ስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት አሌክሳንደር ግርሃም ቤልን በመጥቀስ፣ አከራካሪ መሆኑን ይገልጻል።

ምንም እንኳን ቤል መሳሪያውን በፈጠራ ባለቤትነት ቢያስመዘግብም በአውሮፓውያኑ 2002 የአሜሪካ ኮንግረስ ከቤል ጋር አንድ ዎርክሾፕ የሚጋራው ምስኪኑ ጣሊያናዊ አንቶኒዮ ሜውቺ ነው ስልክን የፈጠረው ሲል ዕውቅና ሰጥቶታል።

ግሌን ሃሞንድ ከርቲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግሌን ሃሞንድ ከርቲስ በራይት ወንድማማቾች ተከስሷል

ማርሲያ ኩሚንግስ እአአ 1909 ጀምሮ በራይት ወንድማማቾች በባለቤትነት መብት ጥሰት የተከሰሰው የአሜሪካ የአቪዬሽን ፈር ቀዳጅ የግሌን ሃሞንድ ከርቲስ የቅርብ ዘመድ ነች።

ዛሬም ከሚንግስ የራይት ወንድማማቾች ፈጠራን በጦማር ገጿ ላይ ትሞግታለች።

ኩሚንግስ የራይት ወንድማማቾች ሆን ብለው እንደ ኩርቲስ ያሉ ሰዎችን ከታሪክ ለማጥፋት እንደሠሩ ታምናለች።

አማንዳ ራይት ሌን፣ የኦርቪል እና የዊልበር ታላቅ እህት ልጅ እና ታሪካቸውን ለማስጠበቅ የምትሠራ ስትሆን ይህንን ሀሳብ ውድቅ አድርጋለች።

"ሰውዬውን ስለማውቅ ኦሊቪል [ዊልበር በ1912 ሞቷል] ሆን ብሎ ግለሰቡን ለማጥቃት የሚሄድ አይመስለኝም።

"ነገር ግን እርሱ እና ዊልበር የሠሩትን እና ያደረጉትን እውነታ ይከላከል ነበር" ስትል አክላለች።