የመጨረሻው የፈረንሳይ ጋዜጣ አዟሪ ከቀድሞ ደንበኛው፣የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እጅ የክብር ሽልማት ሊቀበል ነው

የፈረንሳይ የመጨረሻው ጋዜጣ አዟሪ ነው፤ በአውሮፓም ቢሆን የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም።
አሊ አክባር ጋዜጣ ይዞ በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ እየተዘዋወረ፣ ጮክ ብሎ የዕለቱን ጋዜጣ ዋና ዋና ርዕሶች እየተናገረ ለደንበኞቹ ጋዜጣ ከ50 ዓመታት በላይ ሸጧል።
አሁን ደግሞ ለፈረንሣይ ባህል ላበረከተው አስተዋፅዖ በይፋ እውቅና ሊሰጠው ነው።
በአንድ ወቅት ተማሪ በነበሩበት ወቅት ከአክባር ጋዜጦችን ይገዙ የነበሩት ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በሚቀጥለው ወር ከፈረንሳይ ከፍተኛ የክብር ሽልማቶች አንዱ የሆነውን ሊሸልሙት ነው።
"እዚህ በ1973 ጋዜጣ መሸጥ ስጀምር በፓሪስ 35 ወይም 40 የምንሆን አዛሪዎች ነበርን" ብሏል።
"አሁን ግን ብቻዬን ነኝ።በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። ሁሉም ነገር አሁን ዲጂታል ነው። ሰዎች ስልካቸውን መነካካት ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው።"
በአሁኑ ወቅት አክባር በሴንት ጀርሜን ጎዳናዎች ላይ በሚገኙ ካፌዎች በየቀኑ 30 ያህል የሌ ሞንዴ ጋዜጦችን ለመሸጥ ይሞክራል።
የሽያጩን ግማሽ ዋጋ ለራሱ አስቀርቶ ቀሪውን ይመልሳል፤ ለሚመልሳቸው ጋዜጦች ግን ምንም ክፍያ አያገኝም።
እንዲህ የዓለም ወሬ የእጅ መዳፍ በሚያካክሉ ስልኮች በኩል ቅርብ ሳይሆን በፊት፣ጋዜጣው ገበያ ላይ በዋለ በጥቂት ሰዓታት 80 ቅጂዎችን ይሸጥ ነበር።
"በድሮ ጊዜ ሰዎች ጋዜጣ ፈልገው ይከብቡኝ ነበር። አሁን ግን አንድ ጋዜጣ ለመሸጥ ደንበኞችን እግር በእግር መፈለግ አለብኝ" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አክባር በሥራው ለሚያገኘው ትልቅ ደስታ ሲል በየዕለቱ በጎዳናዎች ላይ ጋዜጣ ማዞሩን መቀጠሉን ሲናገር የገበያው ማሽቆልቆል፣ የአንባቢዎች መጥፋት እንደማያስጨንቀው ይናገራል።
"ደስተኛ ሰው ነኝ።ነፃ ነኝ። በዚህ ስራ ሙሉ በሙሉ ራሴን የቻልኩ ነኝ።አዛዥ አናዛዥ የለብኝም፤ ለዚህም ነው ይህንን የምሰራው።"
የ72 ዓመቱ አክባር በአካባቢው ታዋቂ እና ተወዳጅ ነው።
አንዲት ሴት "መጀመሪያ እዚህ የመጣሁት በ1960ዎቹ ሲሆን ያደግኩት ከአሊ ጋር ነው። ወንድሜ ማለት ነው" ስትል ተናግራለች።
ስለእርሱ ምስክርነቱን የሰጠ ሌላ ሰው ደግሞ "ሁሉንም ሰው ያውቃል። እና በጣም ደስተኛ የሆነ ሰው ነው" ይላል።
አሊ አክባር የተወለደው በፓኪስታን ራዋልፒንዲ ሲሆን በ1960ዎቹ ማብቂያ ላይ ወደ አውሮፓ መጣ።
በመርከብ ላይ ስራ ካገኘ በኋላ በቀጥታ ያመራው ወደ አምስተርዳም ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1972 መርከቧ በፈረንሣይ ሩዋን ከተማ መቆሟን ተከትሎ ከአንድ ዓመት በኋላ መኖሪያውን ፓሪስ አደረገ።
እአአ በ1980ዎቹ የመኖሪያ ፈቃዱን አግኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"እኔ፣ ያኔ ዘመናዊ ሰው አልነበርኩም፣ ግን ብዙ ዘመነኞችን አውቃለው" ይላል የተለመደውን ሳቁን እየሳቀ።
"ወደ አውሮፓ ለመመጣት አፍጋኒስታን እያለሁ ሃሺሽ ሊያጨሱኝ ከሚሞክሩ ሰዎች ጋር ተገናኘሁ።
"ይቅርታ አልኳቸው፤ በሕይወቴ ውስጥ ግብ ነበረኝ፤ የሚቀጥለውን ወር በካቡል ጎዳናዎች ላይ ለመተኛት አልነበረም እቅዴ!"
በአንድ ወቅት የምሁራን መናኸሪያ በነበረው ሴንት ጀርሜይን ጎዳና ታዋቂ ሰዎችን እና ደራሲዎችን ተዋውቋል።
እንግሊዛዊው ድምጻዊ ኤልተን ጆን እንዲሁም በታዋቂው ሳይንስ-ፖ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ጋዜጦችን ሲሸጥ ያኔ ተማሪ የነበሩት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ማክሮን ደንበኞቹ ነበሩ።
ለመጀመሪያ ጊዜ የሌ ሞንዴን ጋዜጣ ከፍ አድርጎ ይዞ የዋናውን ዜና ርዕስ ጮክ ብሎ እየተናገረ ገዢዎችን ሲጠብቅ የነበረበት ሌፍት ባንክ ዛሬ ተለውጧል።
"አካባቢው አንድ አይደለም" ሲል በቁጭት ይናገራል። "ያኔ በየቦታው አሳታሚዎች እና ደራሲዎች፤ ተዋናዮች እና ሙዚቀኞች ይገኙ ነበር። አሁን ግን የቱሪስት ከተማ ሆኗል።"
"ቆሌው ጥላው ሄዳለች" ይላል፤ይህንን እያለም ግን ያንን የተለመደውን ፈገግታው ከፊቱ ላይ አልጠፋም።















