በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ተማፀኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በየመን ሰንዓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች "በሞት እና በሽረት መሃል" ነን ሲሉ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደረግላቸው ተማፀኑ።
የስደተኞች ማኅበረሰብ የኮሚቴ አባል ጀማል ጀይላን በድርጅቶቹ ይደረግላቸው የነበረው ድጋፍ በመቋረጡ ላለፈው አንድ ወር ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እርዳታ ይሰጡ የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት በአጠቃላይ ቢሯቸውን በመዝጋታቸው ከዚህ ቀደም በድርጅቶቹ አማካኝነት የሚያገኙት የሕክምና ድጋፍ እና የስደተኝነት ወረቀት እድሳት መቆሙን አቶ ጀማል አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎም "የታመሙ መድኃኒት አያገኙም። የስደተኛ ወረቀት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እየተያዙ እየታሰሩ ነው። በጣም እየተሰቃዩ ነው" ብለዋል።
ቀድሞ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን በነፃ የሚያገኙት የስደተኛ ወረቀት እድሳት አገልግሎት መቆሙን ተከትሎ ለከፍተኛ የሕክምና ወጪ ተዳርገናል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ቤተሰብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወረቀት ማሳደስ ባለመቻላቸው ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ለማስቀረት መገደዳቸውንም አቶ ጀማል ለቢቢሲ አስረድተዋል።
"ስደተኞች በየሁለት ዓመቱ የሕክምና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው" የሚገልጹት አቶ ጀማል ይህን ካላደረጉ የስደተኛ ወረቀታቸውን ማሳደስ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ለድርጅቱ የዮርዳኖስ ቢሮ አካባቢውን ለቆ ስለመውጣቱ ጥያቄ በኢሜይል አቅርቦ የነበረ ሲሆን እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ሆኖም የድርጅቶቹ ከአካባቢው መውጣት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ሠራዊታቸውን ለማስወጣት ከመወሰናቸው ጋር ሊገናኝ ይችል ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች አሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 30/2025 ወዲህ በሰነዓ የነበረውን ቢሮውን እንደዘጋ አቶ ጀማል ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም ከድርጅቱ ጋር ይሠሩ የነበሩ አጋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሥራቸውን ለማቆም በመገደዳቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል ብለዋል።
ያሉበትን ፈታኝ ሁኔታ ዮርዳኖስ ለሚገኘው የእስያ እና የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ መጻፋቸውን እና ይህን ተከትሎ መጠነኛ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።
በዚህም መቋረጥ የሌለባቸው መድኃኒቶች ያለቀባቸው ታማሚ የሆኑ ስደተኞች ለሁለት ወር የሚሆን ተጨማሪ የመድኃኒት እርዳታ እንደተረገላቸው ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመን የሚገኙ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማኅበረሰብ ሰብሳቢ በአቶ ሙክታር ከድር ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ ኢትዮጵያውያን በየበረሃው በመውደቅ ለአደጋ መዳረጋቸውን ጠቅሷል።
እንዲሁም በወንጀለኞች አማካኝነት ለሕገ ወጥ የሰውነት አካል ንግድ መጋለጣቸውን እና የታመሙ ሰዎችም በመድኃኒት እጥረት ስቃይ ላይ መሆናቸውን በማመልከት መፍትሄ የሚገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በየመን ብሔራዊ የስደተኞች ጉዳዮች ኮሚቴ ሰሞኑን በውጭ ጉዳይ እና በውጭ ዜጎች ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አብዱልዋሂድ አቡራስ የተመራ ስብሰባ ማካሄዱንና የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ አጀንዳ እንደነበረ 'ሱራ ኔት' የተሰኘ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
ይህ ስብሰባ የተካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ፀሐፊ እና ምክትል ኮሚቴው ሊቀመንበር ሜጀር ጄነራል መሐመድ አል-ሃኪም እና ሌሎች የኮሚቴ አባላት በተገኙበት ነው።
ስብሰባው ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ የሚመጡ ሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሶ፤ ይህን ለመግታት የተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ሪፖርቶችን ማቅረባቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ የተለያዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በመተባበር እነዚህን እርምጃዎች ለማሻሻል የሚያስችሉ መንገዶችን ላይ መወያየታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
በየመን ውስጥ በአጠቃላይ 18 ሺህ ኢትዮጵያውያን በስደተኞች ድርጅት ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 8 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በሰንዓ የሚገኙ መሆናቸውን ሰብሳቢው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቀሪዎቹ አብዛኞቹ በሌላኛዋ የአገሪቱ ከተማ አደን እና በሌሎችም ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ይታመናል።
በተጨማሪም እዚያው ሰንዓ ከተማ ውስጥ በስደተኝነት ያልተመዘገቡ እና በእርሻ እና በፋብሪካ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚኖሩም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የመን ለሰባት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ከ23 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦቿ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለችው የመን ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከ95 ሺህ በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙባት ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሶማሊያውያን እና ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኖች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
በተለይ በቀይ ባሕር በኩል በአደገኛ የጉዞ ሁኔታ በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ እና ሌሎች የአረብ አገራት ለመሄድ ዋነኛዋ መተላለፊያ በሆነችው የመን ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ከጂቡቲ እና ከሶማሊያ በመነሳት በትናንሽ ጀልባዎች የተሻለ ሥራ እና ሕይወትን ፍለጋ ከኢትዮጵያ የሚነሱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ፈተና የሚገጥማቸው የመን ከደረሱ በኋላ ብቻ አይደለም።
በሶማሊያ እና በጂቡቲ ውስጥ እንዲሁም ቀይ ባሕር ላይ በችግር እና በአደጋ ሕይወታቸውን የሚያጡት ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም።
በተደጋጋሚ እንደተዘገባው እና የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክቱት በየጊዜው በባሕር ላይ በሚደርሱ አደጋዎች በርካቶች እንደወጡ ቀርተዋል።
በተጨማሪም በየመን ውስጥ እና ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት ለሞት እና ከአካል ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ ማብቂያ ለሌለው እስር ይዳረጋሉ።















