በጋዛ እርዳታ በአውሮፕላን መጣል "አስቂኝ ማታለያ" ነው ሲሉ የእርዳታ ኤጀንሲዎች አስጠነቀቁ

የእስራኤል ወታደር ከእርዳታ ሬሽን አጠገብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ወደ ጋዛ እርዳታ በአውሮፕላን ለመጣል ትኩረት መሰጠቱ "አስቂኝ ትኩረትን የሚከፋፍል" በግዛቱ እየተባባሰ ያለውን የረሃብ ቀውስ የማይቀለበስ ነው ሲሉ የእርዳታ ኤጀንሲ መሪዎች አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤል ጦር እሁድ ዕለት ማለዳ ላይ እንደተናገረው እርዳታ ለጫኑ የተባበሩት መንግሥታት ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ ኮሪደሮች መከፈታቸውን ካስታወቀ በኋላ በጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ እርዳታ በአውሮፕላን መጣል መጀመሩን አስታውቋል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ዮርዳኖስ በመጪዎቹ ቀናት በተመሳሳይ መልኩ እርዳታ በአውሮፕላን ይጥላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር መንግሥታቸው በአየር እርዳታን በመጣል ለጋዛ ነዋሪዎች ለማድረስ "የሚችለውን ሁሉ" እያደረገ ነው ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ባልደረባ የሆኑት ሲያራን ዶኔሊ በበኩላቸው እርዳታ ከአየር ላይ መጣል የሚፈለገውን የእርዳታ መጠን ወይም ጥራት በፍፁም ሊያቀርብ አይችልም ብለዋል።

ከ100 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዛ ሰርጥ የጅምላ ረሃብ እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል።

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ተጨማሪ አምስት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

ይህ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በረሃብ የሞቱ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር 127 አድርሶታል፤ ይህ ቁጥር 85 ልጆችን ያጠቃልላል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሦስቱ ጋዛውያን አንዱ ለቀናት ምግብ እንደማይመገብ እና "ሰው ሠራሽ የጅምላ ረሃብ" ሲል በገለጸው በዚህ ቀውስ የተነሳ 90,000 ሴቶች እና ሕጻናት አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል ሲል አስጠንቅቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እርዳታ በአውሮፕላን ማድረስ ላይ የሚነሳው ክርክር በዋናነት የመጣው በተለምዷዊ መንገድ በመሬት ተሽከርካሪዎችን ተጠቅሞ እርዳታ ወደ ጋዛ ለማድረስ ባለመቻሉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት በአውሮፕላን እርዳታ መጣል "ውድ፣ አባካኝ እና በአግባቡ ወደ መሬት ካልተጣለ የተራቡ ሰላማዊ ዜጎችን ሊገድል ይችላል" ብለዋል።

ላዛሪኒ ድርጅታቸው በዮርዳኖስና በግብፅ ወደ ጋዛ እንዲገቡ "ፈቃድ" እየተጠባበቁ ያሉ "6,000 ያህል የጭነት መኪናዎች" እንዳለው ተናግረዋል።

"ከበባውን ለማንሳት፣የድንበር መተላለፊያዎችን ለመክፈት እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ እና የተቸገሩ ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ የፖለቲካ ፍላጎት ያስፈልጋል" ብለዋል።

"እርዳታን በተሽከርካሪ ማድረስ በጣም ቀላል፣ የበለጠ ውጤታማ፣ ፈጣን፣ርካሽ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ለጋዛ ሕዝብ የበለጠ ክብር ያለው ነው" ሲሉ ላዛሪኒ ጽፈዋል።

የላዛሪኒ አስተያየት የመጣው እስራኤል "የተባበሩት መንግሥታት መኪኖች ምግብ እና መድሃኒት ለማድረስ ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሰብዓዊነት መስመሮችን እንደምታቋቁም" ይፋ ከማድረጓ በፊት ነው። እነዚህ መስመሮች ግን የት እንደሚሆኑ እና እንዴት እንደሚሠሩ አልተገለጸም።

እስራኤል እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ ምንም ገደብ እንደሌለባት ስትገልጽ የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ስርጭትን ለማደናቀፍ ከሐማስ ጋር እየሰራ ነው ሲል ወንጅሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን ውንጀላ አይቀበለውም፤ እስራኤል በጋዛ ውስጥ በቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች እርዳታ የማሰራጨት አቅምን እያደናቀፈች ነው ብሏል።

ሐማስ ከእርዳታ መሰብሰቢያ ቦታዎች እየሰረቀ ነው መባሉን አስተባብሏል። በቅርቡ የወጣው የዩኤስኤአይዲ ዘገባ ስልታዊ ዘረፋ ስለመኖሩ ምንም ማስረጃ የለም ብሏል።

የምዕራባውያን እና የአረብ መንግሥታት እርዳታ ከአየር ወደ ጋዛ ለማድረስ ሲሞክሩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ዓመት የብሪታኒያው ሮያል አየር ኃይል በዮርዳኖስ የሚመራ ዓለም አቀፍ የአየር ጥምር አካል በሆነው 10 ጊዜ ከአውሮፕላን እርዳታዎች የተጣሉ ሲሆን በዚህም 110 ቶን እርዳታ አቅርቧል።

ይሁን እንጂ እነዚያ እርዳታዎች በጋዛ የሚታየውን የጅምላ ረሃብ አደጋ ለመቅረፍ ብዙም አይረዱም ሲሉ የእርዳታ ኤጀንሲዎች ተናግረዋል።

የቢቢሲ ትንታኔ እንዳመለከተው ለሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎች ለአንድ ጊዜ የሚሆን ምግብ ለማቅረብ ወደ 160 የሚጠጉ አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እዝ የ ሲ-130 ጭነት አውሮፕላኖቻቸው በአንድ ጉዞ ወደ 12,650 የሚጠጉ ምግቦችን እንዴት እንዳቀረቡ ባለፈው ዓመት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ያ ማለት በግምት 2.1 ሚሊዮን ለሚጠጋው የጋዛ ሕዝብ ለእያንዳንዱ አንድ ምግብ ለማቅረብ ከ160 በላይ በረራዎች ያስፈልጋሉ።

ዮርዳኖስ ወደ 10 የሚጠጉ የሲ-130 የጭነት አውሮፕላን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ተጨማሪ ስምንት እንዳላት ይታሰባል።

እርዳታ እየጠበቀ ያለ ፍልስልጤማዊ ሕጻን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ብዙ የእርዳታ ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠር ቶን ምግብ ሰው በሚበዛባት ጋዛ ላይ መጣል ስላለው አደጋ አስጠንቅቀዋል።

የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት ባልደረባ ሻይና ሎው እንዳሉት ሰዎች ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የተበላሹ እርዳታዎችን ለመሰብሰብ ሲሞክሩ ሰምጠው እየቀሩ ነው፤ እና ሳጥኖች ከሰማይ ሲወድቁ "ሰዎችን ጨፍልቀዋል" ብለዋል።

እርዳታ ከአውሮፕላን መጣል ስኬታማ ቢሆን እንኳን "ሁከት ነበር" ብለዋል፤ "ሰዎች በእርዳታው ላይ እየተጣሉ ነበር፣ ሰዎች እየተጎዱ ነበር።"

እና በጋዛ ውስጥ ስላለው አደጋ ስጋት ሰፍኗል።

ቢቢሲ ይህ የእረዳታ ማከፋፈያ መንገድ "ከባድ ጉዳት" ሊያስከትል ይችላል ብለው የሚሰጉ በርካታ በጋዛ ሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ቅዳሜ ዕለት አነጋግሯል።

በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖር አንድ ሰው ለቢቢሲ አረብኛ ሚድል ኢስት ዴይሊ እንደተናገረው ሂደቱ "ደህንነቱ ያልተጠበቀ" እና "በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎችን አስከትሏል" ብሏል።

"እርዳታ ከአየር ላይ በሚወርድበት ጊዜ በቀጥታ በድንኳኖች ላይ ሊያርፍ ይችላል፤ይህም ጉዳት አለው፤ ሞትን ጨምሮ ከፍተኛ የአካል ማጉድልን ሊያደርስ ይችላል" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍልስጤማውያን ከውሃ ጥም እና ከረሃብ ጋር እየታገሉ ነው።

አንዲት እናት ለቢቢሲ "ምግብና ውሃ የለንም፤ያለ ምግብ፣ ያለ ዳቦ፣ ውሃ እንኳን በሌለበት እየኖርኩ ነው። ውሃ እንኳን እንናፍቃለን" ብላለች።

እስራኤል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ አጠቃላይ የእርዳታ አቅርቦትን የከለከለች ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጥቃትን ቀጥላ ለሁለት ወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ስምምነት አፍርሳለች።

በቡድኑ ላይ የቀሩትን የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈታ በዚህ መልክ ጫና ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግራለች።

የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ባለሙያዎች በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ እንደሆነ ደጋግመው ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ እገዳው በከፊል የተነሳ ቢሆንም አሁንም የምግብ፣ የመድሃኒት እና የነዳጅ እጥረት ተባብሷል።

አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ በተደጋጋሚ ተፈናቅሏል፤ እንዲሁም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቤቶች ተጎድተዋል ወይም ወድመዋል ተብሎ ይገመታል።