በደቡብ ወሎ ዋሻ የተናደባቸው ማዕድን አውጪዎች አጽም ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ተገኘ

ማዕድን አውጪዎች ከመሬት በታች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማዕድን አውጪዎች ከመሬት በታች (ፎቶ ከፋይል)

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን ቁፋሮ ላይ እያሉ ዋሻ የተናደባቸው ስምንት ግለሰቦች ከአንድ ዓመት አስር ወራት በኋላ አጽም ተገኘ።

የማዕድን አውጪዎቹ አስክሬን የተገኘው በሌሎች የማዕድን ቆፋሪዎች እንደሆነ ግለሰቦቹ አባል የሆኑበት የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራች እና ግብይት ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በሌላ አቅጣጫ ገብተው ሌሊት ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፤ ወደዚያኛው አቅጣጫ ሲሄዱ የስምንቱንም አስክሬን አግኝተውታል" ሲሉ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

የስምንቱም ማዕድን አውጪዎች ሥርዓተ ቀበር ዛሬ [አርብ ኅዳር 5/2018 ዓ.ም] ረፋድ ላይ መፈጸሙንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

የማዕድን አውጪዎቹ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት የኦፓል ማዕድን በቁፋሮ ለማውጣት ሲሞክሩ ነበር ዋሻ ውስጥ የተቀበሩት።

150 ሜትር ርዝማኔ ወዳለው ዋሻ ዘልቆ ለመግባት መቆፈር የተቻለው 33 ሜትር ገደማ ብቻ መሆኑን በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ግለሰቦቹን ለማውጣት ሲደረግ የነበረው ጥረት በቁፋሮ ወቅት አፈሩ በመደርመሱ ከስድሰት ቀናት በኋላ መቋረጡ ይታወሳል።

አቶ ተስፋዬ አጋዥ ከሁለት ዓመት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ሕገ ወጥ የማዕድን አውጪዎች በአካባቢው መሰማራት ለዋሻው መደርመስ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤተሰቦቻቸውም ከዋሻው መደርመስ 19 ቀናት በኋላ እርማቸውን አውጥተው ሐዘን ተቀምጠዋል።

ከማዕድን አውጪዎቹ መካከል አንዱ የእህታቸው ልጅ እንደሆነ የተናገሩ አስር አለቃ ተስፋዬ አስማረ የተባሉ ግለሰብ "አስክሬናቸው በዓመት ከአስር ወራቸው ተገኝቷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አጋዥ የማዕድን ቆፋሪዎቹ አስክሬን የተገኘበተን ሁኔታ ሲያብራሩ "በአንድ አንድ ሜትር ርቀት ነው ያገኟቸው። ተዘጋጅተው ነው የተገኙት። መጨረሻ የሞተው ብቻ ገለል ብሎ ተገኝቷል። በሥነ ሥርዓት በአንድ አንድ ሜትር ርቀት አስቀምጧቸዋል። በረሃብ ነው የሞቱት" ይላሉ።

አቶ ተስፋዬ አክለውም "እነሱ ያሉበት እና የሚቆፍሩበት ቦታ ውስጥ አልተናደም፤ ከእነሱ ወደታች ያለው ክፍል ነው የተናደው እና የተዘጋው መውጫ አጥተው ነው፤ አቅጣጫው በጣም ከባድ ስለሆነ መውጣት ይችሉ ነበር። የተገኙበት ሁኔታ ልጆቹ ውሃ እየጠጡ እንደቆዩ የሚያስረዳ ነው። ዋሻው ውስጥ ውሃ ስላለ ውሃ ለማግኘት የቆፈሩትን ሁሉ አግኝተነዋል" ሲሉ አስረድተዋል።

ከማዕድን ቆፋሪዎቹ አስክሬን መገኘት በኋላ ምን እንደተሰማቸው የተጠየቁት አስር አለቃ ተስፋዬ "ጉዳቴን እኔ ራሴ [አውቀዋለሁ]። መንግሥትም በወቅቱ እንዳንወቅሰው ሰፊ እርዳታ አድርጓል። ስሜቱ እንዳለ ሁኖ ፈጣሪ ባዘዘው ቀን አስክሬኑን አግኝተን ወደ ቤተክርስቲያን አስቀምጠናል" ብለዋል።

የማኅበሩ ሊቀምንበር አቶ ተስፋዬም በተመሳሳይ የቅርብ ዘመዳቸው ዋሻ ውስጥ ተቀብሮ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸው፤ "ምን ዋጋ አለው መውጣት ባለመቻላቸው በጣም ከባድ ስሜት ነው የተሰማኝ። ዙሮ ዙሮ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣታቸው ጥሩ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ስሜታቸውን አጋርተዋል።

አስር አለቃ ተስፋዬ ልጃቸው የተቀበረባቸው እህታቸው ያሳለፏቸውን ሁለት ዓመት የሚጠጉ ጊዜያት፤ "ማንም የማይቀንሰው ትልቅ ስቃይ" ሲሉ ይገልጹታል።

"ምንም አማራጭ እስከ ሌለው ድረስ ደግሞ አግኝታ ያለውን ነገር ቤተ ክርስቲያን መቅበሯ ለዘመድም ሆነ ለእሷ የዘላለም እሳት ከሚሆን ቁርጡን አውቃ ተቀመጠች። ቢያንስ ዘመዷ ጋር ቀበረችው እስካሁን ጫካ ውስጥ ነበር" ሲሉ ያክላሉ።