የሚሻሻለው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በሲቪል ምኅዳሩ ላይ የደቀነው ስጋት

ድምጽ የምትሰጥ መራጭ እና የሲቪል ማኅበራት ሕግ
የምስሉ መግለጫ, የሚሻሻለው ሕግ ከያዛቸው ለውጦች መካከል ሲቪል ማኅበራት ከምርጫ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ከውጭ ገንዘብ ማግኘትን የሚከለክል መሆኑ ተነግሯል

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ፍትህ ሚኒስቴር እያዘጋጁት ያለው ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሲቪል ምኅዳሩን እንደሚያጠበው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቸ ስጋታቸውን ገለጹ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ስጋታቸውን የገለጹበት ረቂቅ ከስድስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት የወጣውን እና በሥራ ላይ የሚገኘውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ የሚያሻሽል ነው።

ቢቢሲ የተመለከተው እና በፍትህ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የማሻሻያ ሰነድ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ ውስጥ 12 አንቀጾች ላይ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ማሻሻያዎችን ያደርጋል።

እነዚህ ማሻሻያዎች ከድርጅቶች ምዝገባ፣ የዕለት ተዕለት ሥራ፣ የሂሳብ አያያዝ እና ሪፖርት እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎች ጋር የተያያዙ ናቸው።

ቢቢሲ በዝግጅት ላይ የሚገኘውን የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶችን አነጋግሯል።

ጦማሪ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ኃይሉ ረቂቁ "የሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት አካልን ሥልጣን የሚለጥጥ እና ሕዝብን ወክለው የሚሟገቱ አካላትን መብት የሚያጣብብ ነው" ሲሉ ትችታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ረቂቅ ማሻሻያው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳይመክሩበት "ድንገት የመጣ" መሆኑን ገልጸዋል።

"የማሻሻያ [ረቂቅ] አዋጁ አሳሳቢ ነገር አለው" የሚሉት ግለሰቡ፤ "እኛ የተሳተፍንበት፤ ክፍተቶች የተባሉትንም እኛ የምናውቃቸው አይደሉም" ሲሉ ያክላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ማሻሻያው ያስፈለገው አዋጁ "ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል" እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።

አንድ ምርጫ ላይ የሚሠራ ድርጅት አመራር የሆኑ ሌላ ግለሰብ "ምን ዓይነት ተግዳሮቶች አጋጥመው፣ እነዚያ ተግዳሮቶች በምን ዓይነት መንገድ ተለይተው፣ አዋጁ አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት የሞከረበትን [እና] የረቂቁ ዝግጅት መነሻዎችን አላውቅም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሁን በኃላፊነት ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ራሳቸው በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ "ከማርቀቅ ሂደት ጀምሮ መርተውታል፤ ስለዚህ እነሱም ተገቢ ነው ብለው ያሰቡት አዋጅ ነው" የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ "አሁን ደግሞ ይኸው አዋጅ ክፍተት አለበት ብለው አስበዋል ማለት ነው። በእኛ በኩል ልንለው የምንችለው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም ዕውቀቱም የለንም፤ ስላልተሳተፍንበት አናውቀውም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የሰጣቸውን አመቺ ሁኔታዎች የመፍጠር ለሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ደጋፊ የሆኑ መርሆችን እና አሠራሮችንም ለመዘርጋት የሞከረ ነበር" የሚሉት ምርጫ ላይ የሚሠራው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አመራሩ "ይሄኛው [ማሻሻያ] ግን ያንን አሠራር የለውጠው ይመስላል" ይላሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ከተከለሱ እና ውዳሴዎችን ካገኙ አዋጆች መካከል አንዱ አሁን ሊሻሻል በሂደት ላይ የሚገኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ነው።

ከዚህ አዋጅ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን የሚመለከቱ አዋጆችም ክለሳ ተደርጓል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከትበት መነጽር የተቀየረ ይመስላል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ኃይሉ መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቸን በሁለት ጎራ ከፍሎ እንደሚመለከታቸው ያወሳሉ።

በአንደኛው ጎራ ያሉት ዕርዳታ ሰጪ (humanitarian) ድርጅቶች ሲሆኑ፣ መንግሥት በእነዚህ ተቋማት ላይ "ከሞላ ጎደል ቅሬታ የለውም" የሚሉት በፍቃዱ፤ "ዋነኛ ቅሬታው የተሟጋች ድርጅቶች ላይ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እነዚህ ተሟጋች ድርጅቶች የዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ መብታቸውን እንዲጠይቁ በማድረግም ይሁን ሌሎች የውትወታ ዘዴዎችን እና አካላትን በመጠቀም መንግሥትን ጫና ውስጥ ይከቱታል። ስለዚህ አይወዳቸውም" ይላሉ።

"በወቅቱ ወደ ሥልጣን እየወጣ ያለው መንግሥት ራሱን እንደ ነፃ አውጪ ለማሳየት የሕግ ክለሳዎቹን ተጠቅሞባቸው ነበር" የሚሉት በፍቃዱ፤ "ይሁንና አዋጁ ከፀደቀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ አዲሱ መንግሥት (ብልፅግና) ሥልጣኑን እያደላደለ ስለመጣና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውትወታ ዒላማ ውስጥ ስለገባ ወደ አፋኝነት ተመልሷል" ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ ያሬድ ኃይለማርያምም አንዲሁ ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በወጣበት ወቅት "መንግሥትን በእያንዳንዱ ሥራዎቹ ላይ ደጋፊም ጠያቂም ማድረግ የሚችል ለኢትዮጵያ ዴሞክራታይዜሽን ሂደት፣ ለሕግ የበላይነት እና ለሰብዓዊ መብት መከበር አስተዋጽዖ የሚያበረክት የሲቪክ ማኅበረሰብ መፍጠር ነበር እሳቤው" ይላሉ።

"ያ እሳቤ አሁን በተወሰነ ደረጃ ተቀይሯል፤ [ነገር ግን] የተከለሰው ሕጉ ሳይሆን ይህ የፖለቲካ አቋም ነው" የሚሉት ባለሙያው፤ "ስለዚህ እነዚህን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫም እየቀረበ ስለሆነ እየጠነከሩ ሲመጡ ድምጻቸው በጣም እየጎላ እና የሰላ ትችት እየሰነዘሩ ነው። ስለዚህ መግራት ያስፈልጋል የሚል የፖለቲካ ውሳኔ ከተወሰደ በኋላ፤ በዚህ የፖለቲካ አቋም መሠረት ተደርጎ የተዘጋጀ ረቂቅ ነው" ሲሉ ከማሻሻያ ረቂቁ ጀርባ አለ ያሉትን አመክንዮ አብራርተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም አክለውም ማሻሻያው የተደረገው "ከተለመደው የሕግ ማርቀቅ ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ" መሆኑን ይገልጻሉ።

"የሲቪክ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ድንጋጌዎችን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ግምት ነበረኝ። የሆነውም ያ ነው" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በቀጥታ ማጥቃት የጀመረው ልክ የዛሬ ዓመት ነበር። ይህ ጥቃት ግን በእግድ አሊያም በፍርድ ቤት በኩል የተላለፈ ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሳቸው በፓርላማ ንግግር የተደረገ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ ዓመት በፊት ባደረጉት ንግግር በሰብዓዊ መብት በኩል አድርገው የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ወርፈዋል።

"የሰብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው" ብለው የጀመሩት ዐቢይ "ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው" ብለዋል።

በወቅቱ "ዋናው" የሰብዓዊ መብት "ትርጉም" ምን እንደሆነ ለመተርጎም አልደከሙም፤ ከዚያ ይልቅ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ወደ መተቸት ነበር የገቡት።

"እኛ ደሞዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው" ብለዋል።

ዐቢይ ይህን ንግግር ካደረጉ አንድ ዓመት በኋላ ይህንኑ የንግግር መንፈስ የሚያንጸባርቀው የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ መዘጋጀት ጀምሯል።

አቶ ያሬድ በዝግጅት ላይ ያለው ረቂቅ "የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለመግራት እና መንግሥት ላይ የሚኖራቸውን ጫና ለመቀነስ ከገቢ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን [እንዲሁም] የፖለቲካ አድቮኬሲ ምርጫ ነክ እና ተያያዥ ሥራዎችን መሥራት እንደማይቻል ያስቀምጣል" ይላሉ።

የአዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለ'ፖለቲካ አድቮከሲ'፣ የመራጮች ትምህርት፣ ምርጫ መታዘብ እና ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለመሥራት ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ እንዳይቀበሉ ይከለክላል።

ይህ ድንጋጌ የተሟጋችነት ሥራ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን እንደሚጎዳ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።

"ለተሟጋችነት ሥራዎች ከአገር ውስጥ ምንጮች ሀብት ማሰባሰብ በጣም አስቸጋሪ" መሆኑን የሚያነሱት በፍቃዱ፤ "የመለገስ አቅሙም ፍላጎቱም ያላቸው አካላት ቢኖሩም እንኳን ልግስናች የመንግሥት ጥርስ ውስጥ ያስገባናል ብለው ይሰጋሉ" ይላሉ።

"ብዙዎቹ የአገር ውስጥ ልግስናዎች ለነፍስ አድን ጥሪዎች ብቻ የሆኑበት ምክንያትም ይኸው ነው። በዚያ ላይ የአካባቢያዊ ልገሳ (local philanthropy) ባሕል ኢትዮጵያ ውስጥ አልዳበረም" ሲሉ ያክላሉ።

ምርጫ ላይ የሚሠራው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አመራር በበኩላቸው "የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብትን በገንዘብ ምንጭ ምክንያት ማጣበብ እና መገደብ እንደማይቻል" የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማንሳት ይሞግታሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ከውጭ አገር ወይም ከአገር ውስጥ ከሚገኝ የውጭ አካል የፋይናንስ ድጋፍ ሲያገኝ በ15 ቀናት ውስጥ "የገንዘቡን ምንጭ፣ መጠን፣ ዓላማ እና ሌሎች መረጃዎችን ከደጋፊ ማስረጃ ጋር አያይዞ" በጽሑፍ ለባለሥልጣኑ የማስታወቅ ግዴታ አለበት።

አቶ ያሬድ "ከዚያም አልፎ በጣም ተቆጣጣሪ የሆነ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያልተገራ ሊባል የሚችል (arbitrary) ሥልጣን የሚሰጡ ድንጋጌዎች ተጨምረውበታል" ሲሉ ያክላሉ።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ላይ ምርመራ እያከናወነ ባለበት ወቅት የድርጅቱን የባንክ ሂሳብ "በከፊል ወይም በሙሉ" ማገድ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ "አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም" እና "ድርጅቱ ካልታገደ የማይመለስ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ካመነ" ለሦስት ወር የማገድ ሥልጣን በረቂቁ ተሰጥቶታል።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቶች የሕዝብ እና የአገርን ሰላም፣ ጥቅም ወይም ደኅንነት "አደጋ ላይ በሚጥል ሕገ ወጥ ተግባር" መሳተፋቸው ወይም መፈጸማቸው ከተረጋገጠ ሊሰረዙ እንደሚችሉ የሚያትት ድንጋጌ በረቂቁ ተካትቷል።

አቶ ያሬድ ረቂቁ "የትኞቹ ድርጊቶች ናቸው ለአገር ደኅንነት ስጋት የሚባሉት" የሚለውን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

"ስለዚህ እንደልብ መተርጎም ይቻላል። የመንግሥትን ሥራ መተቸት በመንግሥት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማጋለጥ ለአገር ደኅንነት ስጋት እንደሆኑ ተደርገው ላለመተርጎማቸው ምንም ዋስትና የለም" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

በተጨማሪም "እነሱም [አስፈጻሚው አካል] ያንን ሽፋን አድርገው ሲያግዱ የትኛው ሥራ ለዚያ ፍረጃ እንደዳረገ፣ ለማስፈረጅስ መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው? የሚለው ግልጽ አይደለም" ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው እና የመብት ተሟጋቹ ለዚህ በማሳያነት የሚጠቅሱት ከወራት በፊት ለአጭር ጊዜ ታግደው የነበሩ ድርጅቶችን ጉዳይ ነው።

"በቅርቡ አምስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሲታገዱ አንዱ ምክንያት ለአገር ደኅንነት ስጋት መሆን የሚል ነበር። ነገር ግን የትኞቹ ተግባራት ለአገር ደኅነነት ስጋት እንደሚባሉ በግልጽ አልተገለጸም" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ምርጫ ላይ የሚሠራው ድርጅት አመራር የሆኑት ግለሰብ ረቂቅ ማሻሻያው "ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ምን ያህል የተጣጣመ ነው የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው" ይላሉ።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት "ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ የመደራጀት መብት አለው" ሲል ይደነግጋል። ሆኖም ይህ መብት "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ" እንደሚሆን ያትታል።