የአሜሪካ ወታደሮች ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር የሚደረገውን ውጊያ ለመደገፍ ናይጄሪያ ገቡ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ወደ 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ወታደሮች የናይጄሪያ ወታደሮች ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ እንዲደግፉ ተላኩ። አሜሪካውያኑ ወታደሮች የደኅንነት መረጃ በማሰባበሰብ ናይጄሪያውያን ወታደሮችን እንደሚያግዙም ተገልጿል።

የናይጄሪያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ጄነራል ሳሚላ ኡባ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ ወታደሮች እና የጦር መሣሪያዎች በአገሪቱ ሰሜን ምዕራባዊ ግዛት ባውቺ ደርሰዋል።

አሜሪካውያኑ ወታደሮች ወደ ናይጄሪያ የሄዱት በአገሪቱ መንግሥት ጥያቄ እንደሆነ እና ውጊያ ውስጥ እንደማይሳተፉ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ እስላማዊ ታጣቂዎች የሚገኙባቸው ሁለት ካምፖች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።

የአሜሪካ ጦር በሶኮቶ ግዛት 'ላኩራዋ' የተባሉ እስላማዊ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ምስጋና አቅርበዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት እንደ ቦኮ ሀራም እና ኢስላሚክ ስቴት ካሉ እንዲሁም ከሌሎችም ታጣቂ ቡድኖች ጋር እያደረገ ያለውን ትግል የአሜሪካ መንግሥት እንዲደግፍ መጠየቁን አስታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ናይጄሪያ የተለያየ ፍላጎት ባላቸው ታጣቂዎች ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ከእነዚህ መካከል እስላማዊ ታጣቂዎች እና አገሬው 'ሽፍታ' ሲል የሚጠራቸው ለገንዘብ ሰዎችን የሚያግቱ የወንጀል ቡድኖች ይገኙበታል።

ከመሬት ይዞታ እና ከመገንጠል ጥያቄ ጋር የተያያዙ አለመረጋጋቶችም በናይጄሪያ ተስፋፍተዋል።

የናይጄሪያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ "የቴክኒክ ሥልጠና በመስጠት ናይጄሪያ ከአሸባሪዎች ጋር የምታደርገውን ትግል እንድታጠናክር እና ለአደጋ የተጋለጡ ማኅበረሰቦችን እንድትከላከል ያግዛሉ" ብለዋል።

በዚህ ወር መባቻ ላይ የአሜሪካ-አፍሪካ ኮማንድ በናይጄሪያ አሜሪካውያን ወታደሮች መሰማራታቸውን አስታውቆ ነበር። ተጨማሪ 200 ወታደሮች ወደ ናይጄሪያ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የናይጄሪያ መንግሥት መግለጹም ይታወሳል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የናይጄሪያ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ እንዳሰጋቸው መግለጻቸው አይዘነጋም። የናይጄሪያ መንግሥት ለክርስቲያኖች የተሻለ ጥበቃ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

ትራምፕ በናይጄሪያ "ክርስቲያኖች ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው" በሚል ያቀረቡትን ክስ የናይጄሪያ መንግሥት በጽኑ አስተባብሏል።

በአገሪቱ ዒላማ እየተደረጉ ያሉት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊሞች እና የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችም ጭምር መሆናቸውን የናይጄሪያ መንግሥት በተደጋጋሚ ገልጿል።

በናይጄሪያ ከ250 በላይ ጎሳዎች ያሉ ሲሆን በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በብዛት ሙስሊሞች እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ በአብላጫው ክርስቲያኖች ይኖራሉ።