አሜሪካ በናይጄሪያ አይኤስ ላይ "ከባድ ጥቃት" ማድረሷን ትራምፕ ተናገሩ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ኢስላሚክ ስቴት ላይ "ከባድ ጥቃት ማድረሷን" ተናግረዋል።

አይኤስን "አጭበርባሪ አሸባሪዎች" ሲሉ የጠሯቸው ትራምፕ ቡድኑ "በተለይ ንፁሕ ክርስትያኖች ላይ ዒላማ ያደረገ ግድያ እያደረሰ ነው" ሲሉ ወቅሰውታል።

ፕሬዝደንቱ እንዳሉት የአሜሪካ ጦር "በርካታ የተሳኩ ጥቃቶችን" ፈፅሟል። የዩኤስ አፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) በበኩሉ የሐሙሱ ጥቃት በሶኮቶ ግዛት የተፈፀመው ከናይጄሪያ ጋር በመተባበር ነው ብሏል።

የናይጄሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ማይታማ ቱጋር "አሸባሪዎችን" ዒላማ ያደረገው ጥቃት "ጥምር ኦፕሬሽን" ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቱጋር ተጨማሪ ጥቃቶች ሊፈፀሙ እንደሚችሉ ጠቁመው "በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውሳኔ የሚሆን" መሆኑን ተናግረዋል።

ሐሙስ አመሻሹን በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው መልዕክት ያሰፈሩት ዶናልድ ትራምፕ "በኔ አመራር ሀገራችን ፅንፈኛ የኢስላም አሸባሪዎች እንዲበለፀጉ አትፈቅድም" ብለዋል።

ባለፈው ኅዳር ትራምፕ በናይጄሪያ የኢስላሚክ ታጣቂዎች እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አሳውቀው እንደነበር ይታወሳል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀኝ ዘመም አሜሪካዊያን ዘንድ በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመ ነው የሚል ወሬ ሲስፋፋ ነበር።

በሌላ በኩል የአሜሪካው የጦር ሚኒስትር ፒት ሄግሴዝ ሐሙስ በኤክስ ገፃቸው "የናይጄሪያ መንግሥት ላሳየው ድጋፍ እና ትብብር ምስጋና አቀርባለሁ" ሲሉ ለጥፈዋል።

አክለው "መልካም የገና በዓል" ብለዋል።

በርካታ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሉባት ናይጄሪያ ክርስትያኖች ከሙስሊሞች በበለጠ ቁጥር እየተገደሉ እንደሆነ የሚያሳይ የቁጥር መረጃ የለም።

የፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ አማካሪ አሜሪካ በጂሃዲስት ቡድኖች ላይ የምትወስደው ማንኛውም እርምጃ በትብብር የሚሆን እንደሚሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዳንኤል ቡዋላ ሀገራቸው ኢስላሚክ ታጣቂዎችን ለመመከት ከዩኤስ የሚመጣን ድጋፍ እንደምትቀበል ገልፀው ነገር ግን "ሉዓላዊ" ሀገር መሆናቸውን አስምረዋል።

አማካሪው እንደሚሉት ጂሃዲስቶቹ የአንድ እምነት ተከታዮችን ብቻ ለይተው የሚያጠቁ ሳይሆን የሁሉም እምነት ተከታዮችን የሚገድሉ ናቸው።

ፕሬዝደንት ቲኑቡ በሀገራቸው የኃይማኖት መቻቻል እንዳለ ተናግረው የፀጥታ መደፈርሱ "የሁሉም እምነት ተከታዮችን" እየፈተነ መሆኑን ገልፀዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ክርስትያን ሕዝቦቿ "የኅልውና ስጋት ስላለባቸው" ናይጄሪያ "ልዩ ትኩረት ሊሰጣት ያለባት ሀገር" ናት ብለው ማወጃቸው ይታወሳል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት "በሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል" ቢሉም ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረቡም።

ይህ አዋጅ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "የኃይማኖት ነፃነት ላይ ጥሰት ፈፅመዋል" ያላቸው ሀገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ይጠቀምበት የነበረ ሕግ ነው።

እንደ ቦኮ ሀራም እና ኢስላሚክ ስቴት ያሉ ጂሃዲስት ቡድኖች በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ለዓመታት ጥቃት ሲፈፅሙ የቆዩ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። አክሌድ የተሰኘው በዓለም የፖለቲካ ነውጥን የሚከታተል ድርጅት መረጃ መሠረት አብዛኛዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ሙስሊሞች ናቸው።

በማዕከላዊ ናይጄሪያ ደግሞ በሙስሊም አርብቶ አደሮች እና በክርስትያን አርሶ አደሮች መካከል በውሀ እና በመኖ ምክንያት ግጭት ይነሳል።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በሶሪያ የአይኤስ ታጣቂዎች ላይ "መጠነ ሰፊ ጥቃት" መፈፀሟን አስታውቃ ነበር።