ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በናይጄሪያ ታግተው የነበሩት ቀሪዎቹ 130 ተማሪዎች መለቀቃቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት፤ ከካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ተወስደው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ ሳይመለሱ የቀሩትን 130 ታጋቾች ማስለቀቃቸውን ገለጹ።
የናይጄሪያ ፌደራል መንግሥት፤ በኒጀር ግዛት በተፈጸመው አስከፊ የጅምላ እገታ የተወሰዱ ተማሪዎች መለቀቃቸውን "የድል እና እፎይታ ጊዜ" በማለት ገልጾታል።
ከ250 በላይ ህጻናት እና ሠራተኞች 'ሴንት ሜሪስ ካቶሊክ' ከተባለው ትምህርት ቤት የተወሰዱት ከአንድ ወር በፊት በሕዳር 12/2018 ዓ.ም. ነበር። በዚያው ወር መጨረሻ ከታጋቾቹ ውስጥ 100 ገደማ የሚሆኑት ህጻናት ተለቅቀዋል።
ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ፤ "የቀሩትን 139 ልጆች እና ሠራተኞችን ማዳን" መቻሉን አረጋግጠዋል። "አንድም ተማሪ ታግቶ አልቀረም" ሲሉም አክለዋል። ከእገታ የወጡ አጠቃላይ ተማሪዎች ብዛት 230 መሆኑን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ባዮ ኦናኑጋ እሁድ ዕለት ተናግረዋል።
እገታው ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተወሰዱ እና ምን ያህሉ እገታ ውስጥ እንደቀሩ ግልጽ አይደለም። የአገሪቱ መንግሥት የቀሩትን ተማሪዎች በምን አይነት መንገድ እንዳስመለሰ አልያም የማስለቀቂያ ገንዘብ ተከፍሎ እንደሆነ በይፋ አልተገለጸም።
ቃል አቀባዩ የተማሪዎቹን መለቀቅ በኤክስ ገጻቸውን ይፋ ካደረጉበት ልጥፍ ጋር እየሳቁ እና እጃቸውን እያውለበለቡ ያሉ ህጻናትን ምስል አያይዘዋል። ተማሪዎቹ ዛሬ ሰኞ የኒጀር ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ሚና ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በተለቀቁበት ወቅት የአጎራባቿ ናሳራዋ ግዛት ገዢ የሆኑት አብዱላሂ ሱሌ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፤ ታጋቾቹን በማስመለስ ሂደት ውስጥ የፌደራል መንግሥት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከደህንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የተነሳ ግን ከመጋረጃ ጀርባ ምን አይነት ጥረቶች እንደተደረጉ እንደማይገልጹ አስረድተዋል።
የናይጄሪያ የክርቲያኖች ማህበር እንደገለጸው ከሆነ 50 ተማሪዎች ለእገታ እየተወሰዱ ሳሉ ማምለጥ ችለዋል።
የሕዳሩ እገታ፤ በሰሜናዊ እና መካከለኛው ናይጄሪያ ትምህርት ቤቶች እና የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው።
በሴንት ሜሪ ትምህርት ቤት ይህ ጥቃት ከመፈጸሙ ጥቂት ቀናት አስቀድሞም በርካታ ሰዎች በጅምላ ታግተው ነበር።
ሕዳር 9 ቀን በክዋራ ግዛት በሚገኘው 'ክራይስት አፖሰቶሊቸ ቸርች' ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለው፤ 38 ሰዎች ታግተዋል። ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን አስቀድሞ ደግሞ በኬቢ ግዛት ከሚገኝ የመንግሥት የሴቶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሁለት ሰዎች የተገደሉበት እና 25 ሙስሊም ተማሪዎች የተወሰዱበት ሌላ ጥቃት ተፈጽሟል።
ከክዋራ እና ኬቢ ግዛት የተወሰዱት ታጋቾች በሙሉ ለቀቅቀዋል።
ከእነዚህ እገታዎች ጀርባ ያለው አካል ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ብዙ ተንታኞች፤ በእገታ ገንዘብ ማግኘት በሚፈልጉ ወንጀለኛ ቡድኖች የተፈጸመ እንደሆነ ያምናሉ።
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ፤ መንግሥታቸው "የትምህርት ቤቶች ደህንነት ለማስጠበቅ እና የመማር ማስተማር ሂደት ለታዳጊዎች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ እንዲሆን ለማድረግ" ከኒጀር እና ሌሎች ግዛቶች ጋር መስራት እንደሚቀጥል በሕዳር ወር መጨረሻ ተናግረዋል።