በናይጄሪያ 13 ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ታፍነው ተወሰዱ

በማዕከላዊ ናይጄሪያ፣ ኮጊ ግዛት ታጣቂዎች 13 ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን አፍነው ወሰዱ።

ይህ በሳምንታት ውስጥ የተፈጸመ ሁለተኛው ጥቃት ሲሆን፤ ታጣቂዎች 'ዊኒንግ ኦል' ወደተባለ የኢቫንጃሊካል ቤተ ክርስቲያን ገብተው ሰዎችን አግተው ወስደዋል።

አዚ ኪሪ በሚባለው መንደር ውስጥ የእሑድ ማለዳ የፀሎት ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ሳለ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመው።

የኮጊ ግዛት የመረጃ ኮሚሽነር ኪንጋሊ ፋናዎ እንዳሉት ከታጣቂዎቹ አምስቱ ተገድለዋል። የተቀሩት ጉዳት ቢደርስባቸውም አምልጠዋል።

ጥቃት አድራሾቹን "ሽፍቶች" ሲል መንግሥት የገለጻቸው ሲሆን፤ ሰዎችን አግቶ ገንዝብ መጠየቅ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ድርጊት ሆኗል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ታጣቂዎች ኢጃባ በተባለ ከተማ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ፓስተር፣ ባለቤታቸውን እና ሰባት ምዕመናንን አፍነው ወስደዋል።

ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረት ቢደረግም እስካሁን እንዳልተሳካ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የኮጊ ግዛት የመረጃ ኮሚሽነር "በኒጀር እና በካውራ ግዛት ያለው ነውጥ በኮጊ ግዛት ሽፍቶች እንዲንቀሳቀሱ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።

በተለይም በሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ ናይጄሪያ እየተፈጸሙ ያሉ ተከታታይ ጥቃቶች እና አፈናዎች የአገሪቱን ደኅንነት ስጋት ላይ ጥለዋል።

ከደረሱት ጥቃቶች የከፋው በኒጀር ግዛት፣ ፓፒሪ ከተማ በሚገኝ የካቶሊክ ትምህርት ቤት 250 ሕጻናት እና 12 የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞች የታገቱበት ነው።

የናይጄሪያ መንግሥት በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የቦኮ ሀራም እና ኢስላሚክ ስቴት ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ እገታን ለመከላከል የፀጥታ ኃይሎች አሰማርተዋል። በእገታ ታዋቂ ወደሆኑ አካባቢዎች ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ተሰማርቷል።

ወታደሮች እና ፖሊሶች ተጣምረው የተሰማሩ ቢሆንም በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች አሁንም እገታዎች እንደቀጠሉ ነው።