በናይጄሪያ አንድ ፓስተር እና ሙሽራ ከነሚዜዎቿ በታጣቂዎች ታገቱ

በናይጄሪያ ከታገቱ 20 ሰዎች መካከል አንድ ፓስተር እና አዲስ ሙሽራ እንደሚገኙበት ተገለጸ።

ባለፉት ሳምንታት በናይጄሪያ የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰው የቀጠሉ ሲሆን፤ ትናንት እሑድ ኅዳር 21/2018 ዓ. ም. በኮጊ ግዛት በተፈጸሙ ሁለት እገታዎች አንድ ፓስተር እና አዲስ ሙሽራ ታፍነው ተወስደዋል።

አዲስ የተመሠረተው 'ቸሩቢም ኤንድ ሰራፐሒም'፤ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታጣቂዎች ገብተው ተኩስ ከከፈቱ በኋላ ምዕመናን በድንጋጤ ሸሽተዋል።

ታጣቂዎቹ ፓስተሩን፣ባለቤታቸውን እና በርካታ ምዕመናን አግተው ወስደዋል።

የእሁዱ እገታ ከመፈጸሙ አስቀድሞ በሶኮቶ ግዛት በተፈጸመ ሌላ እገታ አዲስ ሙሽራ ከነሚዜዎቿ ታግተዋል።

የፈረነሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ አንድ ሕጻን ከነእናቱ እንዲሁም ሌላ ሴትም ታግተዋል።

በሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ናይጄሪያ ተባብሶ በቀጠለው እገታ ትምህርት ቤቶች እና ቤተ እምነቶች ዒላማ ተደርገዋል።

እገታው በማን እንደሚፈጸም ግልጽ አይደለም። ተንታኞች እንደሚሉት ግን ከእገታው ጀርባ ያሉት የወንጀል ቡድኖች ሲሆኑ እገታውን የሚፈጽሙት ገንዘብ ለማግኘት ነው።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደገለጹት እገታው የሚፈጸመው በጂሃዲስት ቡድኖች ነው።

የኮጊ ግዛት አስተዳደር ቃል አቀባይ ኪንግስሊ ፋናዎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢጂባ በሚባለው ቦታ ጥቃት ተፈጽሟል። ምን ያህል ሰዎች ታግተው እንደተወሰዱ በትክክል መግለጽ እንደማይቻልም አክለዋል።

ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

"የግዛቱ የፀጥታ ኃይሎች እና የደኅንነት ባልደረቦች ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሙስሊም በሆኑባት ሶኮቶ ግዛት በተፈጸመው እገታ ለሰርግ እየተሰናዳች የነበረች አዲስ ሙሽራ፣ ጓደኞቿ እንዲሁም ሌሎችም ታዳሚዎች መታገታቸውን የናይጄሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ባለፉት ሳምንታት በተፈጸሙ እገታዎች ወደ 250 የሚጠጉ ተማሪዎች እና 12 መምህራን የደረሱበት እንዳልታወቀ ተገልጿል።

በሌሎች እገታዎች ተይዘው የነበሩ ሰዎች መለቀቃቸውም ተዘግቧል።

እገታዎች መበራከታቸው በተለይም በገጠሪቱ ናይጄሪያ ነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

በዋነኛነት ተጋላጭ በሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ተገልለው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የሚደረግላቸው ጥበቃ ላይ ጥያቄም አጭሯል።

እገታን ለማስቆም በሚል የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ የሚፈጸም ክፍያ ክልከላ ተጥሎበታል። ሆኖም ግን የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ክፍያዎች መፈጸም እንደቀጠለ ይነገራል።

ባለፈው ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የናይጄሪያ መንግሥት "ክርስቲያኖች እንዲገደሉ መፍቀዱን ከቀጠለ" ወታደሮቻቸውን እንደሚልኩ ዝተዋል።

የናይጄሪያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች እገታ እንዲሁም ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው በመጥቀስ፤ ክርስቲያኖችን ለይቶ የተፈጸመ ድርጊት አለመሆኑን ተናግረዋል።