ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ታጣቂዎች ከትምህርት ቤት ያገቱትን ልጄን ሲወስዱ ረዳት አልባ ሆኜ እየተመለከትኩ ነበር" - ናይጄሪያዊ አባት
ታጣቂዎች በሰሜናዊ ናይጄሪያ ወደሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው የእርሱን ልጅ ጨምሮ በርካታ ሕጻናትን ሲወስዱ የተመለከተ አባት፤ በወቅቱ አቅም አልባነት እንደተሰማው ለቢቢሲ ተናገረ።
ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ጠዋት በኒጀር ግዛት በሚገኘው ቅድስት ማርያም ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት የገቡት በሞተር ሳይክል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በርካታ ሕጻናትን አፍነው ወስደዋል።
ወንድ ልጁ የተወሰደበት አባት እንደሚናገረው፤ በዕለቱ ከእንቅልፍ ያነቃው ታጣቂዎቹ ያፈኗቸውን ልጆች ጭነው በሚኖርበት መንደር በኩል ሲያልፉ ያሰሙት ጩኸት ነው።
"እረኛ በጎቹን እንደሚቆጣጠረው፤ [ልጆቹም] በእግራቸው እንዲጓዙ እየተደረገ ነበር። የተወሰኑ ልጆች ሲወድቁ ሰዎቹ እየጎቷቸው እና እንዲነሱ እያዘዟቸው ነበር" ሲል ከቤቱ ሲወጣ የተመለከተውን ተናግሯል።
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙን ቀይረን ቲዮ እያልን የምንጠራው አባት፤ "ታጣቂዎቹ 50 ገደማ ሞተር ሳይክሎች ላይ ሆነው ነበር የሚቆጣጠሯቸው" ይላል። ልጁ ይተኛበት በነበረው የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ዶርም ውስጥ ሆኖ ቢቢሲን ያነጋገረው ይህ አባት፤ ታፍኖ የሚወሰደነውን ልጁን ማዳን የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልነበር ያስረዳል።
"ሄጄ [ለማገዝ] እያሰብኩ ነበር፤ ነገር ግን ሐሳቤን ቀየርኩ። ብሄድስ ምን ማድረግ እችላለሁ? ምንም ማድረግ አልችልም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። ለፖሊስ ደውሎ የነበረ ቢሆንም የጸጥታ አካላት ወደ ቦታው የደረሱት ዘግይተው እንደነበር አክሏል።
የናይጄሪያ ክርስቲያን ማኅበር 303 ተማሪዎች እና12 ሠራተኞች ከትምህርት ቤቱ መወሰዳቸውን አስታውቋል። 50 ልጆች ደግሞ ከመወሰድ መትረፋቸውን እና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጿል።
በማኅበሩ የኒጀር ግዛት ቅርንጫፍ ሊቀመንበር በሆኑት ቄስ ቡሉስ ባዋ ዮሃንስ የሚመራው ይህ ትምህርት ቤት፤ ታፍነው የተወሰዱ ልጆችን ዝርዝር ለቢቢሲ አጋርቷል። ፖሊስ በበኩሉ አፈናው በተፈጸመበት ምሽት ያመለጡት ልጆች ጥቂት ብቻ መሆናቸውን እንደሚያውቅ ገልጿል።
የታገቱት ተማሪዎች ቁጥር ተጋንኗል የሚሉት የኒጀር ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኡማር ባጎ ደግሞ የህጻናቱ ብዛት ከ303 "እጅግ፣ እጅግ ያነሰ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ከአራት ዓመት በፊት እንደሁም በድጋሚ ከሁለት ወር በፊትም ባልታወቁ ታጣቂዎች የተሰነዘሩ ዛቻዎች እንደነበሩ እየታወቀ ትምህርት ቤቱን ከፍተዋል ያሏቸውን አመራሮችም ጥፋተኛ አድርገዋል።
ዋና አስተዳዳሪው ባጎ፤ "በዚያ አካባቢው ያለው ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት ተዘግቶ ነበር። ትምህርት ቤቱ አሁንም ክፍት መሆኑን ሳውቅ ተገርሜያለሁ" ብለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው "ለማስፈራራት" ብቻ እንደሆነ እና በቅርቡ ወይም ዘግይቶም ቢሆን ህጻናቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ እንደሚያስረዱት እገታው ከተፈጸመ በኋላ እስካሁን ድረስ ምንም የጸጥታ ኃይል በአካባቢው አልተሰማራም።
ልጁ የታገተበት ቲዮ በመንግሥት ምላሽ ከተናደዱ ሌሎች ወላጆች ጋር በመሆን በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ ተቃውሞውን እያሰማ ነው። "ልጆቻችን ታግተዋል፤ መንግሥት ግን ትኩረት የሰጠው አይመስልም" ይላል።
የግዛቱ ዋና አስተዳዳሪ በቦታዉ ተገኝተው ትምህርት ቤቱን ሳይጎበኙ በቅርብ የሚገኙ የጸጥታ አካላትን እና አካባቢ መሪዎችን ብቻ አነጋግረው መመለሳቸው እንዳሳዘነው ይገልጻል።
"መንግሥት ስለ እኛ አያሳስበውም ብለን ደምድመናል። የአገሪቱ አካል እንዳልሆንን ነው የሚሰማን፤ ትተውናል" ሲል ተፈጠረበትን ስሜት አጋርቷል።
ልጆቻቸው በተወሰዱባቸው ወላጆች ላይ የተፈጠረው ሕመም በግልጽ የሚታይ ነው። ልጇ የታገተባት አንዲት እናት፤ "አዝኛለሁ፤ መላ ሕይወቴ በሐዘን ተሞልቷል" ብላለች። "ልጄ ነው፤ የመጀመሪያ ልጄ ነው። እባካችሁ እርዱን" በማለት ትማጸናለች።
ሁለት ልጆቹ የተወሰዱበት ሉካስ የተባለ ሌላ ወላጅ ደግሞ፤ የስድስት ዓመቱ ታናሽ ልጁ ከአጋቾቹ መዳፍ ማምለጥ መቻሉን ተናግሯል። "እንዳየሁት፤ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በስሙ ስጠራው ዞረና ወደ እኔ ሮጠ። አቀፍኩት" ሲል ያመለጠውን ልጁን ያገኘበትን ቅጽበት አስታውሷል።
እገታው የተፈጸመባት ፓፒሪ መንደር የሚገኝበት የኒጀር ግዛት ሰሜናዊ ክፍል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ እገታ በርክቶበታል።
ለታጣቂዎች የሚደርሰውን የገንዘብ ፍሰት ለመግታት ሲባል በእገታ ለተያዙ ሰዎች ማስለቀቂያ ገንዘብ መክፈል በሕግ ቢከለከልም፤ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣም።
የቢቢሲ ዘጋቢዎች ከኒጀር ግዛት ዋና ከተማ ሚና ተነስተው ወደ ፓፒሪ ለመድረስ የ500 ኪሎ ሜትር ጉዙ በጀመሩበት ወቅት በተወሰኑ መንገዶችን እንዳይጓዙ፤ በአንዳንድ ጊዜያትም መንገድ ላይ እንዳይሆኑ ተመክረዋል። ጉዞውን ያደረጉትም በፖሊስ እጀባ ነው።
ብዙዎች ይህንን የጸጥታ ችግር ግዛቱ ካለው ስፋት ጋር ያያይዙታል። ናይጄሪያ ውስጥ ከሚገኙ ግዛቶች በቆዳ ስፋት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘው ኒጀር ነው። የግዛቱ መሬት ስፋት እንደ ዴንማርክ እና ኔዘርላድስ ካሉ አገራት ይበልጣል።
በተጨማሪም በግዛቱ በርካታ ጫካዎች አሉ። እነዚህን ጫካዎች በአካባቢው ሰዎች ሽፍቶች ተብለው የሚጠሩት የወንጀል ቡድኖች ካምፕ ለመመሥረት ምርጫቸው አድርገዋቸዋል። ወደሌሎች የናይጄሪያ ግዛቶች እና አጎራባች አገራት ለመንቀሳቀስም በመተላለፊያነት ያገለግላሉ።
በዚህ ትምህርት ቤት የተፈጸመው እገታ በአንድ ሳምንት ውስት ለሦስተኛ ጊዜ በናይጄሪያ የታየ ክስተት ነው። ባለፈው ሳምንት ሰኞ የኒጀር አጎራባች በሆነው ኬቢ ግዛት ከሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ20 በላይ ሴት ተማሪዎች ተወስደዋል። የታገቱት ተማሪዎች ሙስሊም እንደሆኑ እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በደቡባዊ ክዋራ ግዛት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለው በርካታ ምዕመናን ታግተዋል።
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ይህንን ቀውስ ለመፍታት ሲሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በደቡብ አፍሪካ ከተካሄደው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ ቀርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ እሑድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ በክዋራ ግዛት የታገቱት 38 ምዕመናን እንዲለቀቁ መደረጉን አስታውቀዋል።
"ግልፅ አድርጌ ልናገር፤ ተስፋ አልቆርጥም። ማንኛውም ናይጄሪያዊ፣ በማንኛውም ግዛት ውስጥ፣ ደኅንነቱ የመጠበቅ መብት አለው። በእኔ ኃላፊነት ሥር የዚህን አገር ደኅንነት እናስጠብቃለን፣ ሕዝባችንን እንጠብቃለን" ብለዋል።
ከሰሞኑ ያገረሸው እገታ በመላው ናይጄሪያ የሚገኙ በርካታ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው፤ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲወስዱ አስገድዷል።
የናይጄሪያ መንግሥት ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጫና እየደረሰበት ነው። ትራምፕ፤ የአገሪቱ መንግሥት ኢስላማዊ ታጣቂዎች "ክርስቲያኖችን መግደል እንዲቀጥሉ የሚፈቅድ" ከሆነ ወደ ናይጄሪያ ወታደሮችን እንደሚልኩ በዚህ ወር መጀመሪያ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ መንግሥት በበኩሉ ክርስቲያኖች እየተገደሉ ነው የሚለው ድምዳሜ "እውነታውን በከፍተኛ መጠን ያዛባ" አገላለጽ እንደሆነ በመጥቀስ ውንጀላውን ውድቅ አድርጓል። "አሸባሪዎች ነፍሰ ገዳይ የሆነውን ርዕዮተ ዓለማቸውን የሚቃወም ሁሉንም ሰው ያጠቃሉ፤ ሙስሊም፣ ክርስቲያን እና እምነት የሌላቸውንም" ብሏል።
ናይጄሪያ ውስጥ የተወሰኑ እገታዎች የሚፈጸሙት በኢስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሚካሄዱት ገንዘብ በሚጠይቁ የወንጀል ቡድኖች ነው።