ትራምፕ እንደሚሉት በናይጄሪያ ክርስትያኖች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው?

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስትያኖች" ሞትን ለማስቆም "ጦራቸውን እንደሚያዘምቱ" የተናገሩት ዝም ብሎ የመጣ ዛቻ አይደለም።

ለወራት በዋሺንግተን ያሉ ፖለቲከኞች እና የክርስትያን ደህንነት ተሟጋቾች እስላማዊ ታጣቂዎች በናይጄሪያ የሚገኙ ክርስትያኖች ላይ ስልታዊ የሆነ ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ይወነጅሉ ነበር።

ነገር ግን ቢቢሲ የተመለከታቸው ሰነዶች ላይ የሰፈሩ ቁጥሮችን እውነተኛነት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ናቸው።

በመስከረም ወር ላይ ኮሜዲያን እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢው ቢል ማሄር በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ ይፈፀማል ያለውን "የዘር ማጥፋት" ሲያብራራ ነበር፥።

ቦኮ ሃራም የተባለውን ቡድን በመጥቀስም "ከ2009 ጀምሮ ከ100 ሺህ ባለይ ሰዎችን ገድለዋል፣ 18ሺህ ቤተክርስትያኖችን አቃጥለዋል" ብሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያም ተመሳሳይ ቁጥር በስፋት ሲሽከረከር ነበር።

በአቡጃ የሚገኘው መንግሥት ግን ይህንን መረጃ "ከእውነታው ጋር የሚጣረስ" ሲል ውድቅ አድርጎታል።

የናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ሞት ያስከተሉ ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ማስተባበያ አልሰጠም። ነገር ግን የአገሪቱ ባለሥልጣናት "የሽብርተኞች ጥቃት ገዳይ የሆነው ርዕዮተ ዓለማቸውን የማይቀበል ላይ ሁሉ የሚፈጸም ነው፤ ሙስሊሞች፣ ክርስትያኖች እና ሌላ እምነት የሚከተሉ ላይ ሁሉ" ይላሉ።

በናይጄሪያ የሚፈጸሙ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን የሚከታተሉ ቡድኖች እንዲሁ በናይጄሪያ የተገደሉ ክርስትያኖች ቁጥር ከሚባለው በጣም ያነሰ ነው በማለት በእስላማዊ ጂሃዲስት ቡድኖች የበለጠ ጥቃት የሚደርስባቸው ሙስሊሞች ናቸው ባይ ናቸው።

የናይጄሪያ የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ የሆነችው ክርስትያን አኒ በክርስቲያኖች ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የነበረው ሽብር የመፍጠር ሰፊ ስልት አካል ሆኖ እንጂ ክርስቲያኖች ሆን ተብሎ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚሉ መረጃዎችን ማረጋገጥ አይቻልም ትላለች።

ናይጄሪያ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከጂሃዲስቶች ጥቃት በተጨማሪ የተለያዩ የደህንነት ስጋቶችን ያለባት አገር ነች።

እነዚህ የደህነንነት ስጋቶች ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳላቸው መሳት አይገባም ስትል ታስረዳለች።

የአገሪቱ 220 ሚሊዮን ሕዘብ በሁለቱ እምነቶች መካከል የተከፈለ ሲሆን ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩት ተደጋጋሚ ጥቃቶች በሚፈጸሙባቸው የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ነው።

የቴክሳስ ሴናተር ቴድ ክሩዝ በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ከሚሉት ወገን ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለፃ ከሆነ እአአ ከ2009 ጀምሮ 50,000 ክርስትያኖች የተገደሉ ሲሆን 18,000 ቤተክርስትያኖች እና 2000 የክርስትያን ትምህርት ቤቶች ወድመዋል።

ቴድ ክሩዝ ይህንን "የዘር ማጥፋት" ከማለት ይልቅ "በእስላማዊ ጂሃዲስቶች የሚፈጸም የጅምላ ግድያን ቸል ማለት እንዲሁም ማመቻቸት" ማለት መርጠዋል።

ትራምፕም ይህንኑ የሴናተሩን ቃል በመጠቀም ናይጄሪያን "የተዋረደች አገር" በማለት የአገሪቱ መንግሥት "የክርስትያኖች መገደል እንዲቀጥል ፈቅዷል" ብለዋል።

የናይጄሪያ መንግሥትንም የጂሃዲስቶች ጥቃትን መከላከል ባለመቻል እና ቸል በማለት የቀረበበትን ውንጀላ በማጣጣል እንደ ቦኮ ሃራም እና ኢስላሚክ ስቴት ያሉ ጽንፈኛ ቡድኖችን እየተዋጋ እንደሆነ ገልጿል።

ነገር ግን አሜሪካ በእነዚህ ቡድኖች ተገደሉ ያለቻቸው ክርስትያኖችን ቁጥር ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።

ሴናተር ክሩዝ የጠቀሱት በናይጄሪያ የሚንቀሳቀስ እና በአገሪቱ ያለን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚከታተል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እአአ በ2003 ያወጣውን ሪፖርት ነው።

ምንም እንኳ ድርጅቱ ከቢቢሲ የቀረበለትን ጥያቄ ባይመልስም፣ ክሩዝ የተጠቀሙት ቁጥር ከድርጅቱ ሪፖርቶች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።

ኢንተር ሶሳይቲ የተሰኘው ይህ ድርጅት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆኑን ያህል የግልፅነት ችግርም እንዳለበት ከዚህ ቀደም ያወጣቸውን ሪፖርቶች የተመለከቱ ሰዎች ይገልጻሉ።

በነሐሴ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው እአአ ከ2009 ጀምሮ በጂሃዲስቶች ጥቃት ከ100,000 በላይ ክርስትያኖች ተገድለዋል ይላል።

በእነዚህ ዓመታት 60,000 "ለዘብተኛ ሙስሊሞች" መገደላቸውንም ያትታል።

ኢንተርሶሳይቲ የመረጃ ምንጮቹን ስለማያጋራ ቁጥሮቹን በገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ኢንተርሶሳይቲ ባለፈው ዓመት ከጥር ወር እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ብቻ 7,000 ክርስትያኖች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጓል።

ይህ ቁጥርም ራይሊ ኤም ሙር የተሰኙ የኮንግረስ አባልም አስተጋብተውታል።

ድርጅቱ ለዚህ ሪፖርቱ 70 የሚዲያ ዘገባዎችን በመረጃነት መጠቀሙን ቢናገርም በግማሽ ያህል የሚዲያ ሪፖርቶች ላይ ግን የተጠቂዎቹ ሃይማኖት አልተጠቀሰም።

ለምሳሌ ኢንተርሶሳይቲ አልጀዚራ ቦኮሃራም በርካታ ክርስትያን ገበሬዎችን ማገቱን መዘገቡን ቢገልጽም በአልጀዚራ ሪፖርት ላይ ግን የተጠቂዎቹ ሃይማኖት አልተጠቀሰም።

ኢንተርሶሳይቲ ለቢቢሲ እንደገለፀው የተጠቂዎቹን ማንነት ለመለየት የራሱን ትንተና እንደሚጠቀም ቢናገርም ስለ አካባቢው ማኅበረሰብ ያለውን እውቀት እና "የክርስትያን መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን" ስለመጠቀሙ ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ በኢንተርሶሳይቲ የተጠቀሱትን 70 የሚዲያ ሪፖርቶች ሲመለከት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 3,000 ብቻ መሆኑን መረዳት ችሏል።

ይህም በ2025 ተገደሉ ከተባሉት በግማሽ ያህል የቀነሰ ሲሆን የተወሰኑ ጥቃቶችም በተደጋጋሚ ተቆጥረው ተገኝተዋል።

ኢንተርሶሳይቲ ይህንን ሲያስተባብል በእገታ ላይ ሳሉ የሞቱ ሰዎችን ከግምት አንደሚያስገባ ገልፆ የዓይን ምስክሮች እማኝነትም እንደሚካትት ገልጿል።

ኢንተርሶሳይቲ ክርስትያኖችን የሚገድሉት ቦኮ ሃራም እና የፉላኒ አርብቶ አደሮች መሆናቸውን ይናገራል።

ነገር ግን አብዛኞቹ ሙስሊም የሆኑትን የፉላኒ አርብቶ አደሮች እንደ "ጂሃዲስት" መግለጽ በናይጄሪያ ውስጥ ውዝግብ ያስነሳል።

በጉዳዩ ላይ ጥናት እና ምርመር የሠሩ ባለሙያዎች በአብዛኛው ከፉላኒ አርብቶ አደሮች ጋር የሚኖር ግጭት መነሻው የግጦሽ መሬት እና የውሃ እጥረት እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም ይላሉ።

በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ ይፈፀማል ስለሚባለው ጥቃት የአሜሪካ ፖለቲከኞች እና ዓለማቀፍ የክርስተያን ቡድኖች በሰፊው የሚነጋገሩበት ጉዳይ ነው።

ይህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በናይጄሪያ ውስጥ በሚገኙ እና በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ የሚገኙት የቢያፍራ ክርስትያኖችም ሲቀነቀን ነበር።

የናይጄሪያ ጦር ኢንተርሶሳይቲ ከታገደው የቢያፍራ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው ሲል ይወነጅለዋል።

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የቢያፍራ ሪፐብሊክ መንግሥት "በክርስትያኖች ላይ ስለሚፈጸም የዘር ጭፍጨፋ" አጀንዳን በወትዋቾች በኩል የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ትኩረት እንዲያገን ያደርጋል።

ከእነዚህ የአሜሪካ ፖለቲከኞች መካከል ደግሞ ሴናተር ቴድ ክሩዝ የሚገኙበት ሲሆን ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ላቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ኢንተርሶሳይቲ በሙስሊም ታጣቂዎች ተገድለዋል የሚላቸው ናይጄሪያውያን ክርስትያኖች ቁጥር ሌሎች ምንጮች ከሚያስቀምጡት በእጅጉ ከፍ ያለ ነው።

በምዕራብ አፍሪካ ያለውን አለመረጋጋት የሚከታተለው አክሌድ በኢንተርሶሳይቲ የተገለፀው 100,000 የሚለው ቁጥር በናይጄሪያ የተከሰቱ ግጭቶችን ሁሉ የሚያካትት ነው ይላል።

አክሎም እአአ ከ2009 ጀምሮ የተገደሉ ክርስትያኖች ቁጥር ይህ ነው ማለት ስህተት መሆኑን ይገልጻል።

አክሌድ እአአ ከ2009 ጀምሮ በተፈጠሩ ግጭቶች የተገደሉት ሙስሊሞች እና ክርስትያኖች ቁጥር 53,000 መሆኑን አስታውቋል።

አክሌድ አክሎም እአአ ከ2020 እስከ መስከረም 2025 ድረስ ደግሞ 21,000 ሰላማዊ ሰዎች ታግተዋል፤ ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ብሏል።

በእነዚህ ጊዜያት ክርስትያኖችን ዒላማ ያደረጉት ክስተቶች 384 መሆናችንም ጨምሮ ገልጿል።

በዚህም 317 ሰዎች መሞታቸውን አስቀምጦ ይህም ቁጥሩ የሚባለውን ያህል የተጋነነ አለመሆኑን እንደሚያሳይ አስታውቋል።