በናይጄሪያ የነብዩ መሐመድን ስም አጠልሽታለች የተባለች ሴት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለች

በሰሜን ናይጄሪያ፣ ማዕከላዊ ኒጀር ግዛት፣ አንዲት ሴት በደቦ በተፈጸመባት ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደለች።

የናይጄሪያ ፖሊስ እንደገለፀው ግለሰቧ የተገደለችው የነብዩ መሐመድን ስም አጠልሽታለች በሚል ነው።

በዚህ የደቦ ጥቃት ግለሰቧ ከነሕይወቷ በእሳት እንድትቃጠል ተደርጋ ነው የተገደለችው።

ሟች ስሟ አሚያ እንደሚባል እና በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ፣ ምግብ በመቸርቸር፣ ትተዳደር እንደነበር የገለጸው ፖሊስ ድርጊቱን 'አረመኒያዊ' ሲል አውግዞታል።

በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ወንጀል የተሳተፉትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደሚሠራም ፖሊስ ቃል ገብቷል።

የአገሬው መገናኛ ብዙኃን ሁኔታው ወደ አሰቃቂ ግድያ ሊያመራ የቻለበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ አንድ ግለሰብ ለአሚያ የቀልዱን የጋብቻ ጥያቄ ካቀረበላት በኋላ እርሷ ለሰውየው የሰጠችው መልስ በአካባቢው ለተሰበሰቡት ሰዎች የሃይማኖት ጥላቻ ንግግር ሆኖ ተሰምቷቸዋል።

"ሁኔታው አሳዛኝ ነው፤ ነገሩ እየተጋጋለ ሄዶ እርሷን ከነሕይወቷ በእሳት አነደዷት፤ ይህ የሆነው ፖሊስ በአካባቢው ከመድረሱ ቀደም ብሎ ነው" ሲሉ የግዛቲቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዋሲዩ አቢዱን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረው ሕዝቡ እንዲረጋጋ እና ከማንኛውም ዓይነት የበቀል ድርጊት አንዲታቀብ ተማጽነዋል።

እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ መልክ ያለው የደቦ ጥቃት በናይጄሪያ አዲስ ነገር አይደለም።

በሸሪዓ ሕግ የነብዩ መሐመድን ስም ማጠልሸት እና በተመሳሳይ ሃይማኖት ላይ የሚሰነዘሩ ጸያፍ ንግግሮች ወንጀል ናቸው።

በናይጄሪያ በ12 ግዛቶች ውስጥ ሸሪዓ ሕግ ከዓለማዊው ሕግ ጋር መሳ ለመሳ ያገለግላል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በናይጄሪያ ሌሎች ሁለት ሰዎች ሃይማኖትን የሚያጥላሉ ጸያፍ ንግግሮችን ተናግራችኋል በሚል በተመሳሳይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች መንግሥት ይህን ለማቆም በቂ ጥረት አላደረገም ሲሉ ይወቅሳሉ።

በእንዲህ ዓይነቱ የደቦ ፍርድ ተጠቂ የሚሆኑት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ሙስሊሞችም ጭምር ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2022፣ በናይጄሪያ ሶኮቶ ግዛት፣ ዲቦራህ ሳሙኤል የተባለች ሴት ክፉኛ ከተደበደበች በኋላ ከነሕይወቷ በእሳት እንድትነድ ተደርጋ ተገድላለች።

ባለፈው ዓመት ደግሞ ኡስማን ቡውዳ የተባለ ሥጋ ነጋዴ በተመሳሳይ መልኩ በድንጋይ ተቀጥቅጦ ተገድሏል።

የናይጄሪያ ሕገ መንግሥት የመናገር ነጻነት የተፈቀደ ቢሆንም፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ናይጄሪያዊያን 'እስከምን ድረስ ነው የመናገር ነጻነቱ መሆን ያለበት' በሚለው ላይ የተከፋፈለ ሐሳብ አላቸው።

የናይጄሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ሃይማኖታዊ የጥላቻ ንግግር ተፈጸመ ለማለት ጉዳዩ በገለልተኛ ፍርድ ቤት መጣራት አለበት የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ አምነስቲ በአሚያ አሰቃቂ ግድያ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ መንግሥት ነጻ እና ገለልተኛ የምርመራ በማድረግ አጥፊዎቹን ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቋል።

አምነስቲ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳተተው በሰሜን ናይጄሪያ ነዋሪዎች ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ሲሉ በሐሰት ግለሰቦችን በጥላቻ ንግግር እንደሚከሱ ጠቅሷል።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው ግለሰቦች በግል ሊያጠቁት ያሰቡትን ሰው በአደባባይ ''ነብዩን ተሳደበ!' እያሉ በመጮኽ የደቦ ጥቃት እንዲፈጸም ያነሳሳሉ ሲል አምነስቲ አብራርቷል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የኡስማን ቡውዳን አሰቃቂ ግድያ ያስታወሰው አምነስቲ ግለሰቡ ሙስሊም ኾኖ 'ነብዩን ተሳደበ' በሚል በተፈጠረ ግርግር ተቀጥቅጦ እንዲገደል ሆኗል። በድርጊቱ የተሳተፉት አብዛኞቹ ትንንሽ ልጆች እንደሆኑም አምነስቲ አስታውሷል።

እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በተለይ የሃይማኖት አባቶች እንደሚያበረታቱ እና በዚህም የተነሳ ተከታዮች በስሜታዊ እና ግብታዊ እርምጃ ያለ ፍርድ የደቦ ጥቃት እንደሚፈጽሙ የአምነስቲ መግለጫ ጠቅሷል።