ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ ይደርሳል ያሉትን ግድያ በመጥቀስ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ዛቱ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ናይጄሪያ በክርስትያን ዜጎቿ ላይ የሚፈጸም ስቃይን ቸል ብላለች በማለት ከወነጀሉ በኋላ የመከላከያ ሚኒስቴር ለወታደራዊ እርምጃ እንዲዘጋጅ ማዘዛቸውን ተናገሩ።

ናይጄሪያ ይህንን የዶናልድ ትራምፕን ውንጀላ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በአገሪቱ የሚገኙ ክርስትያኖች ላይ "የጅምላ ግድያ" ይፈጸማል ሲሉ ጽፈው፣ የአገሪቱ መንግሥት "በፍጥነት እርምጃ" የማይወስድ ከሆነ "ለናይጄሪያ የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ ወዲያውኑ እናቆማለን" ሲሉ ዝተዋል።

አርብ ዕለት እንዲሁ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስቲያኖች ላይ ይደርሳል ያሉትን መጠነ ሰፊ መከራ እና ግድያ በመጥቀስ አገሪቱን "አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ በተለየ መልኩ የምትታይ" በሚል መፈረጇን አስታውቀው ነበር።

ቅዳሜ ዕለት የናይጄሪያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ባወጣው መግለጫ የዶናልድ ትራምፕን ፍረጃ ውድቅ አድርጎታል።

የናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር የሱፍ ቱጋር በሰጡት መግለጫ የትራምፕ አቋም በናይጄሪያ ያለውን እውነታ አያሳይም ብለዋል።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ አርብ ዕለት በለጠፉት በዚህ ጽሑፍ ላይ ክርስትያኖች በናይጄሪያ የመኖር ኅልውናቸው አደጋ ላይ ወድቋል በማለት፣ አሜሪካ "እንዲህ ዓይነት ግፍ ሲፈጸም ዝም ብላ አትመለከተም" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ክርስትያኖች "በጽንፈኛ ሙስሊሞች" ተገድለዋል ሲሉ በልጥፋቸው ላይ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ "በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ እና የሳህል አካባቢዎች የተለየ ፍላጎት ባላቸው ውስን ቡድኖች አማካኝነት ግጭቶችን እና መከፋፈሎችን የፈጠረውን አመጽ የተቀለቀለበት ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ባለን ቁርጠኝነት እንቀጥልበታለን" ብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የዌስት ቨርጂኒያው ተወካይ ሬይሊ ሙር እና የኦክላሆማው ቶም ኮልን ጨምሮ በርካታ የኮንግረስ አባላት በጉዳዩ ላይ ምርመራ አድርገው በቀጥታ የደረሱበትን እንዲያሳውቋቸው ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።

በአሜሪካ ሕግ መሠረት "አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ በተለየ መልኩ የምትታይ አገር" የሚለው ፍረጃ ዋሺንግተን ከምትጠቀምባቸው እጅግ ጠበቅ ያሉ ፍረጃዎች መካከል አንዱ ነው።

ይህ ፍረጃም የሃይማኖት ነጻነትን በመጋፋት እና በመጣስ የሚወነጀሉ አገራት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ወይንም ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ለማድረግ ይፈቅዳል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ በክርስትያኖች ላይ የሚደርሰውን ግድያ ማስቆም ካልቻለች መከላከያ "ፈጣን" የሆነ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከፍተኛ የሕዘብ ብዛት ያላት እና ነዳጅ አምራች ለሆነችው ናይጄሪያ የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ ወዲያውኑ እንደሚያቆም በትሩዝ ሶሻል ልጥፋቸው ላይ ገልፀዋል።

አሜሪካ ወታደሮቿን የምትልክ ከሆነ አሰቃቂ ግፎችን የፈጸሙ እስላማዊ አሸባሪዎችን ጠራርጎ ለማስወገድ ይሆናል ያሉት ትራምፕ በናይጄሪያ ክርስትያኖች ላይ ይደርሳል ስላሉት ግድያ እና ስቃይ ግን ተጨባጭ መረጃ አልሰጡም።

ትራምፕ ናይጄሪያን "የተዋረደች አገር" በማለት መንግሥቷ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ አስጠንቅቀዋል።

"ጥቃት ከፈጸምን ፈጣን፣ ጨካኝ እና ጣፋጭ ይሆናል፤ ልክ ወሮ በላ አሸባሪዎቹ በውድ ክርስትያኖቻችን ላይ እንደሚፈጽሙት ማለት ነው!" ሲሉ ጽፈዋል።

አቡጃ ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲሉ ለሰጡት ማስጠንቀቅያ ምላሽ አልሰጠችም።

ዋይት ሐውስም እንዲሁ አሜሪካ ስለምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ ያለው ነገር የለም።

ነገር ግን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄጌሴት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ መስሪያ ቤታቸው "እየተዘጋጀ ነው" ሲሉ ጽፈው "የናይጄሪያ መንግሥት ክርስትያኖችን ይከላከላል ወይም ይህንን ሰቅጣጭ ግፍ የሚፈጽሙ እስላማዊ አሸባሪዎች እንገድላቸዋለን" ብለዋል።

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ በትራምፕ የመጀመርያው የሥልጣን ዘመንም በዓለም አቀፉ የሃይማኖቶች ነጻነት ሕግ መሠረት የሃይማኖት ነጻነትን በመግፈፍ ወይንም ጥሰት ሲፈጸም በመታገስ ከተወነጀለች በኋላ፣ እአአ በ2020 ታሕሳስ ወር "አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ በተለየ መልኩ የምትታይ አገር" ተብላ ነበር።

ይኹን እንጂ እአአ በሕዳር 2021 የባይደን አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከዚህ ምድብ ውስጥ እንድትወጣ ያደረገ ሲሆን ስለ ፍረጃውም ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሳይሰጥ ቀርቷል።

ይህ ውሳኔ በአሜሪካ የሃይማኖቶች ነጻነትን በሚያቀነቅኑ እና በዩኤስ ኮሚሸን ኦን ኢንተርናሽናል ሪሊጂየስ ፍሪደም ተቋማት ዘንድ ትችትን ያስከተለ ሲሆን በናይጄሪያ አሁንም የሃይማኖት ነጻነት እየተጣሰ ይገኛል ሲሉ መወትወታቸውን ቀጥለዋል።

ትራምፕ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ከመዛታቸው በፊት የናይጄሪያዉ ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ቅዳሜ ዕለት የሃይማኖት አለመቻቻልን በመቃወም አገራቸው የእምነት ነፃነትን ለማስጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ዘርዝረዋል።

"ናይጄሪያ ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ይታይባታል መባሉ የአገሪቱን እውነታ አያሳይም፤ እንዲሁም መንግሥት የሁሉም ናይጄሪያውያን የእምነት እና የሃይማኖት ነፃነት ለመጠበቅ የሚያደርገውን ተከታታይ እና ቅን ጥረት ግምት ውስጥ አላስገባም" ሲል ቲኑቡ ተናግረዋል። "የትኛውንም እምነት የሚከተሉ ዜጎችን ለመጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አለ" ሲሉ አክለዋል።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ፅንፈኝነትን በመታገል ላይ እንደሚገኝ ገልፆ ዋሽንግተን የቅርብ አጋር ሆና ትቀጥላለች የሚል እምነት እንዳለው አስታውቋል።

አክሎም "ዘር፣ እምነት እና ሃይማኖት ሳንለይ ሁሉንም ዜጎች መከላከላችንን እንቀጥላለን። ልክ እንደ አሜሪካ ሁሉ ናይጄሪያም ትልቁ ጥንካሬዋ የሆነውን ብዝሃነትን ከማክበር በቀር ሌላ አማራጭ የላትም።"

ናይጄሪያ በተለይ ቦኮ ሃራም እና ኢስላሚክ ስቴት በአገሪቱ ሰሜናዊ ምሥራቅ አካባቢ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ላለፉት አስርት ዓመታት በሚፈጽምባቸው ግዛቶች የሃይማኖት እና የብሔር ውጥረቶች በተደጋጋሚ ያጋጥሟታል።

በማዕከላዊ ናይጄሪያ ሁለት ግዛቶች ግን በከበት አርቢዎች እና በአርሶ አደሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የክርስትያኑ ማኅበረሰብ ስልታዊ በሆነ መልኩ ዒላማ ተደርጓል፤ ጥቃት ተፈጽሞበትም ተገድሏል ሲሉ ይናገራሉ።

ምንም እንነኳ አንዳንድ ወገኖች መንግሥት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎችን መከላከል አልቻለም ሲሉ ቢወቅሱም የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ግን ሁለቱም ክርስትያን እና ሙስሊም ማኅበረሰቦች በግጭቶቹ ተጎድተዋል ይላሉ።

የናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ "የፕሬዚዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ መንግሥት በእውነተኛ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ነፃነት እና ዲሞክራሲ ከሚያምኑ አጋሮች ጋር ለመስራት የማያወላውል ቁርጠኝነት አለው" ብሏል

ታዛቢዎች ግን ይህ የዶናልድ ትራምፕ እርምጃ የሁለቱ አገራትን ግንኙነት የበለጠ እያደፈረሰው እንደሚሄድ እንዲሁም የውጭ አገራት በአገሪቱ ውስብስብ እና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት በሚቀጥፈው ሃይማኖታዊ ግጭት ላይ ተሳትፏቸው ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ አዲስ ክርክር ያስነሳል ብለዋል።