ናይጄሪያ ጽንፈኛውን ቦኮ ሃራምን 'ማስወገድ' ያልቻለችባቸው 6 ምክንያቶች

የናይጄሪያ መንግሥት ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራምን ለማስወገድ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የአገሪቱ ጦር ባደረጋቸው ዘመቻዎች ቡድኑ ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቁን ቢገልጽም የቡድኑ ህልውና ግን አላከተመም። አሁንም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ይገኛል።

በቅርቡ በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ ቡድኑ የፈጸመው ጥቃት የአገሪቱ መንግሥት ቡድኑንን 'እንዳያስወግድ' እንቅፋት የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄን አጭሯል።

በተያዘው ዓመት ብቻ የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን 100 ጥቃቶችን ፈጽሟል። በርካታ ወታደራዊ ካምፖችን መስርቷል። በቡድኑ ሺህ ዎች ተገለዋል። መሳሪያ፣ ምግብና መድሃኒቶች ተዘርፈዋል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ቡድኑን በሚከተሉት 6 ምክንያቶች ማሸነፍ አልተቻለም ይላሉ።

1፡ ለመሠረታዊ ችግሮች ትኩረት ማጣታቸው

ቦኮ ሃራምን ለማስወገድ የአገሪቱ መንግሥት ወታደራዊ ጡንቻው ላይ ብቻ ያለልክ መተማመኑ የችግሮች ሁሉ ምንጭን ነው ይላሉ የደህንነት አማካሪው አዳሙ ካቢካን።

"ለዚህም ነው እንዳለመታደል 11 ወይም 12 ዓመታት ቡድኑን ለማስወገድ ዘመቻ ቢደረግም ውጤት ያላየነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አዎ በእርግጥ አሸባሪዎቹን ወታደሩ ያስወግዳቸዋል። ነገር ግን ተጽኗቸውን ማሳደር ይቀጥላሉ፣ ሰዎችን መመልመል፣ ገንዘብ መሰብሰብና መሳሪያ ማግኘት ይችላሉ ስለዚህ እንደገና ይደራጃሉ"።

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምስራቅ የሚገኙ ሰዎች ለቡድኑ ራርተው ሳይሆን በመንግሥት አካላት ችላ ስለተባሉ ቦኮ ሃራም እጅ ላይ ይወድቃሉ በማለት ያስረዳሉ።

"እውነታው አመጽን ወይም ሽብርተኝነትን ለመከላከል ከወታደራዊ ርምጃ ያለፈ ተግባር ያስፈልጋል። የአመጻውን ስረ መሠረት ሊታይ ይገባዋል" የሚሉት አዳሙ፤ "እንዳለመታደል በዚህ በኩል የሚደረግ ጥረት ማየት አይቻልም" ሲሉ ይገልጻሉ። ህዝቡን ለድህነት እና ለስጋት የዳረገው የመልካም አስተዳደር እጦት አንዱና ትልቁ የችግሩ ምንጭ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ምስራቅ መንግሥት ልማትን ለማፋጠን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም ውጤቱ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

2፡ የቦኮሃራም የመመልመል አቅም

ቡድኑ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ያለው ስር የሰደደ ድህነትና የቦኮ ሃራም የጥቃት ስልቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ ለአላማው የሚሰለፉ ሰዎችን ለመመልመል ያስችለዋል ይላሉ ባለሙያዎች።

"ሰዎች ለመኖር ሲሉ ቡድኑን በቀላሉ ይቀላቀላሉ" ሲሉ የሚገልጹት ደግሞ የደህንነት ባለሙያው አብዱላሂ ያላዋ ናቸው።

የዚህም መነሻ ሥራ አጥነትና ደካማ መልካም አስተዳደር እንደሆነ በመጥቀስ።

ቦኮ ሃራም ወጣቶችን ስልታዊ በሆነ መንገድ የመመልመል ዘመቻም እንደሚያካሂድ ይጠቀሳል። ቡድኑ ራሱ በፈጠረው ችግር የሚፈናቀሉ ሰዎችን ጭምር እንደሚመለምል የሀገሪቱ ባልስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

3፡ የትጥቅ እጥረት

እንደ ደህንነት ባለሙያው አዳሙ ገለጻ፤ ቦኮሃ ራምን ለማስወገድ በሚደረግ ዘመቻ ላይ የትጥቅ እጥረት ያጋጥማል።

በዚህ ዘመቻ የተሰማራውን የመከላከያ ሠራዊትን ያልተሟላ ትጥቅ የያዘ ብለውታል። የእርሳቸው የአማካሪ ተቋም ባደረገው ጥናት በናይጄሪያ ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ቀላልና አነስተኛ የጦር መሳሪያ ቢኖርም የጸጥታ ሃይሉ እጅ የሚገኘው ግን 586 ሺህ ብቻ ነው።

የተቀረው ጦር መሳሪያ በእስላማዊ ታጣቂው ቡድን እጅ ገብቷል ማለት ሳይሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር መሳሪያ ከአገሪቱ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

"በማስረጃ ላይ ተመስርተን እያየነው ያለነው እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች በሚያሳዝን ሁኔታ ከወታደራዊ ኃይሎች የበለጠ የመሳሪያ ትጥቅ እንዳላቸው ነው" ሲሉ ባለሙያው ገልጸዋል።

ቦኮ ሃራምን በጨረፍታ

  • እአአ 2002 ተመሠረተ
  • በመጀመሪያ ትኩረት ያረገው የምዕራብውያኑንን ትምህርት መቃወምን ነበር
  • እእአ 2009 ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጀመረ
  • እአአ 2014 ላይ እገታ ፈጸመ። በዚህም ትኩረትን ሳበ
  • እአአ 2015 ላይ ታማኝነቱ ለኢስላሚክ ስቴት (አይ ኤስ) መሆኑን ገለጸ
  • እአአ 2016 ላይ ለሁለት ተሰነጠቀ

4፡ ሙስና

ሙስና የአገሪቱን ወታደራዊ ትጥቅ እንዳይሻሻል ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ይገመታል።

ቦኮ ሃራምን ለመዋጋት ለሚደረጉ ዘመቸዎች የሚመደቡ በርካታ ገንዘቦች መጨረሻቸው የባለስለጣናቱ ኪስ ነው የሚሉ ጥርጣሬዎችም ይሰማሉ።

አብዱላሂ ያላዋ እንደሚሉት በአንድ አንድ ሁኔታዎችን ቦኮሃራምን ለመዋጋት የተደረጉ ውጊያዎች "በቅን ልቦና" የተደረጉ ሳይሆኑ "አንዳንድ ሰዎች ወደ ንግድ ቀይረውት ራሳቸውን ያበለጸጉበት ይመስላል" ብለዋል።

5፡ ውጤታማ ያልሆነ ወታደራዊ ስትራቴጂ

ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የቦኮሃራም ታጣቂዎች "የጦር ሠራዊቱን የአየር ላይ ድብደባ ንድፍን የተረዱና የተላመዱ" ናቸው።

በተጨማሪም ቡድኑ የሚንቀሳቀስበት የአገሪቱ ሰሜናዊ ምስራቅ ያለው አስቸጋሪ መልክአ ምድር ከወታደራዊ ጥቃት እንዲሸሹ ምቹ ሆኖላቸዋል።

በአካባቢው ቋሚ ወታደራዊ ሰፈር ተገንብቶ የነበረ ቢሆንም እንደ አውሮፓውያኑ 2020 እንዲፈርስ ተደርጓል። ምክንያቱም ወታደሩን ለጥቃት ስላጋለጠና ተደጋጋሚ ዘረፋ ስለተፈጸመ ነው።

6፡ የቦኮሃራም ተጽእኖ መጠናከር

ሌላኛው ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ችግር ተብሎ የሚጠቀሰው የቦኮሃራም ተጽእኖ ከሰሜናዊ ምስራቅ የናይጄሪያ ክፍል አልፎ በመላው አገሪቱ መስፋፋት ነው።

በሰሜንና በማዕከላዊ የአገሪቱ አከባቢዎች ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ትስስር እንዳላቸው የተጠረጠሩ የወሮበላ ስብስቦች መኖር ስጋት ፈጥሯል።

ባለፈው ዓመት ቦኮሃራም ይንቀሳቀስበታል ተብሎ ከሚታሰበው ስፍራ ርቆ በኒጀር የተቀረጸ ቪዲዮ አሰራጨቶ ነበር። በአከባቢው ያሉ ባለስልጣናት ቦኮሃራም ወድ ግዛታቸው ዘልቆ መግባቱንና በነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጽሙን አስታውቀው ነበር።

ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ወታደሩና መደበኛ ዜጎች ተቀናጅተው ካልተዋጉት ቦኮሃራም በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል ብለዋል።