ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያን ያሰጉት ወደ ድመት 'የሚቀየሩ' መተተኞች
ማሳሰቢያ፡ ይህ ጽሑፍ ለአንዳንድ አንባቢዎች ተገቢ ያልሆነ ሊመስል ይችላል።
ቤንጋ አዴዊዪን በናይጄሪያዋ ኢባዳብ ከተማ ስል ቢላውን እንደያዘ የድምጽ ማጉያ በጎን በኩል አድርጎ እንዲሁም ሙሉ ጥቁር ለብሶ በገበያ ውስጥ ሲመላለስ ለተመለከተው በጥንት ዘመን 'ጠንቋዮችን' የሚያድኑ ሰዎችን ነው የሚመስለው።
"ከሰዎች በላይ ኃይል አለው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ እስቲ ማስረጃ አቅርቡልኝ'' የሚለውን መልዕክቱን ሲሰሙ በርካቶች ተሰብስበው ሲያዩት ከነበረው ወዲያው ይበተናሉ።
ቤንጋ ይቀጥላል "መተት (ጁጁ) ሆነ ማንኛውም ዓይነት ነገር ለሚያሳየኝ ሰው 6 ሺህ ዶላር እሰጠዋለው'' በማለት በዩሩባ እና በእንግሊዝኛ መልዕክቱን ያስተላልፋል።
የ24 ዓመቱ ቤንጋ ሃይማኖት የሌለው ሲሆን በጣም በሃይማኖት በምትታወቀው ናይጄሪያ መነጋገሪያ እየሆነ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2010 በተሠራ አንድ ጥናት መሠረት ናይጄሪያ ውስጥ በርካቶች ጥንታዊ የአፍሪካ እምነቶችን ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና ጋር በማጣመር ነው ጎን ለጎን የሚያስኬዷቸው።
በርካቶችም አንዳንድ ሰዎች ከፈለጉ ወደ ድመትነት መቀየር እንደሚችሉ፣ ማንኛውም ስል እና ሹል ነገር እንዳይጎዳቸው ማድረግ እንደሚችሉ እንዲሁም ድንገት ከእንስራ ውስጥ ገንዘብ ማፍለቅ እንደሚችሉ ያምናሉ።
ታዲያ እነዚህ እምነቶች ባልተማሩ ሰዎች ብቻ አይደልም የሚዘወተሩት፤ አሉ የተባሉ ምሁራንም ጭምር በመሰል ተግባራት ውስጥ ሲሳተፉ መመልክት የተለመደ ነው።
ዶክተር ኦላሌዬ ካዮዴ በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ አገር በቀል የአፍሪካ እምነቶችን የሚያስተምሩ ሲሆን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገንዘብ ለማግኘት የሚከናወነው ሥነ ሥርዓት የሰዎችን የሰውነት ክፍሎች ከወሳኝ ሃይማኖታዊ ቁሶች ጋር በመቀላቀል ነው የሚካሄደው ብለዋል።
"የናይጄሪያ ገንዘብ ላይ ያሉት ምልክቶችና ጽሑፎችን ለማግኘት ደግሞ እንስራው ውስጥ የሚፈለገው የገንዘብ ኖት ይጨመራል'' ሲሉ ያስረዳሉ።
"በጥንታዊ የአፍሪካ እምነቶች ውስጥ ሰዎች ሲያሻቸው ወደ ድመትነት መቀየር አልያም በድንገት መጥፋትና መከሰት ይችላሉ። ምናልባት ይህ የማይሆን ነገር ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር እውነት ነው'' ይላሉ ዶክተር ኦላሌዬ።
መሰል እምነቶች በተለይ ደግሞ ከእንስራ ውስጥ ገንዘብ ለማፍለቅ በሚል የሰዎችን የሰውነት ክፍሎች መጠቀም በቅርብ ጊዜያት በርካታ ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እንዲገደሉ ምክንያት እየሆኑ ነው።
በዚህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ተጠቂ የሚሆኑት ትዳር የሌላቸው ሴቶች ናቸው።
"ወጣቶች በመሰል ተግባራት ሲሳተፉ ማየትና ሰዎች ሲጎዱ መመልከት በጣም ያሳዝነኛል። የገንዘብ ማፍለቅ ሂደቱ በትክክል የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ኢኮኖሚያችን በዋጋ ንረት ያብጥ ነበር'' ይላል ቤንጋ አዴዊዪን።
ቤንጋ በሄደበት ሁሉ እንዲሁም ትዊተር በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ በኩል በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶቹ የጁጁ ኃይልን ለሚያሳየው ሰው 6 ሺህ ዶላር ወይም 2.5 ሚሊየን ናይራ እንደሚሰጥ ቃል ይገባል።
"ቢላ ይዤ የምዞረው ጁጁ ከማንኛውም ጉዳት ይጠብቀኛል ብለው ለሚያስቡ ሰዎች ነው። እውነት ከሆነ በተግባር እንዲያሳዩኝ እፈልጋለው" ይላል።
ናይጄሪያ ውስጥ ከሰዎች በላይ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ እምነቶችን እና ሥርዓነቶች መኖርን መጠራጠር እንደ ትልቅ ሀጥያት የሚቆጠር ጉዳይ ነው።
ቤንጋ በየገበያው እየዞረ እስቲ እምነታችሁ እውነት ከሆነ በተግባር አሳዩኝ እያለ ሲጮህ እራሱን ትልቅ አደጋ ውስጥ ጥሎ ነው።
በየትኛውም ሰዓት ሃይማኖትን በማንቋሸሽ በሚል በቁጥጥር ሥር ሊውል አልያም የደቦ ጥቃት ሊደርስበት ይችላል።
"ምን ማለቱ ነው? ጁጁ በትክክል ይሠራል'' የሚል ግለሰብ በአጠገቡ አለፈ።
ይህ ግለሰብ ምትሀታዊ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚታመንበት ጥቁር ቁስ በኪሱ የያዘ ሲሆን በሰዎች ፊት ቀርቦ ግን በትክክል ይሠራል ወይስ አይሠራም የሚለውን ለማሳየት ፈቃደኛ እልነበረም።
6 ሺህ ዶላር እንኳን አላጓጓውም።
ምንም እንኳን አብዛኛው ናይጄሪያዊ በሃይማኖት ደረጃ ክርስትና እና እስልምና እምነቶችን የሚከተል ቢሆንም ጥንታዊ የአፍሪካ እምነቶችም ትልቅ ቦታ አላቸው።
የሃይማኖት መሪዎች በተደጋጋሚ ይህ ተግባር የእርኩስ መንፈስ እንደሆነ በመግለጽ ተከታዮቻቸውን ቢገስጹም እምነቶቹ ግን ሥር የሰደዱ ናቸው።
በርካታ የናይጄሪያ ፓስተሮችና ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲሁም በእስልምናው ደግሞ ኢማሞች ከመሰል እርኩስ መንፈስ የሚጠብቅ ኃይል እንዳላቸው በመግለጽ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል።
ቤንጋ በሄደበት ሁሉ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ብሎ ይህንን እንደሚያደርግ በማሰብ በርካቶች ትኩረት አይሰጡትም።
ነገር ግን በቅርቡ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሰዎች አካላት ጎድለው፣ አይናቸው የተጎለገለ አስክሬኖችን ለተመለከተ ሰው ችግሩ እየተባባሰ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ ደግሞ ከጁጁ ሥነ ሥርዓት ጋር ተያይዞ በየቀኑ አድራሻቸው ስለጠፋ ሰዎች አልያም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ስለተገደሉ ሰዎች ማየትና መስማት የተለመደ እየሆነ ነው።
ባሳለፍነው ወር ሦስት ሰዎች አንዲትን የ17 ዓመት ታዳጊ በመግደል የሰውነት ክፍሎቿን ገንዘብ ከእንስራ ለማፍለቅ የሚደረገውን ሥነ ሥርዓት ማዋላቸው የሚታወስ ነው።
በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ወንጀሉን መፈጸማቸውን በማመን ሀብታም ለመሆን አስበው እንደሆነ ገልጸው ነበር።
የዚህች ታዳጊን መገደል ተከትሎ የናይጄሪያ ሕግ አውጪዎች በጁጁ ዙሪያ በርካታ ክርክሮችን ያደረጉ ሲሆን እንደውም ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ይሁን የሚል ሐሳብም ቀርቦ ነበር።
በሌላ በኩል የናይጄሪያ የመረጃ ሚኒስትር ላይ ሞሐመድ ደግሞ ኖሊዉድ የተባለው የናይጄሪያ ፊልም ኢንዱስትሪ ችግሩን እያባባሰው እንደሆነ ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ታዳጊዎችና ሕፃናት በፊልሞቹ ላይ የሚመለከቱትን ነገር እውነት አድርገው የመቀበላቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።
ስለዚህ የፊልሙ ኢንደስትሪ መሰል ፊልሞችን ከመሥራት መቆጠብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ነገር ግን የኖሊዉድ ፊልም ሠሪዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።
"ሚኒስትሩ ተሳስተዋል። የእኛን አዝናኝና አስተማሪ ነገር የመፍጠር መሠረታዊ መብታችንን የሚጋፋ ነው'' ሲል ፊልም ሠሪ ለቢቢሲ ገልጿል።
አክሎም "ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቡ፣ ሃይማኖታዊ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የተፈጠረን ችግር በእኛ ማሳበብ ተገቢ አይደለም'' ይላል።
ናይጄሪያ ውስጥ አሁን ላይ በርካቶች በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር መጀመራቸው ግልጽ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ግን መኖራቸው አያጠራጥርም።
ቤንጋ እንደሚለው የናይጄሪያ መንግሥት ከታች ጀምሮ ባሉ ትምህርት ቤቶች ድረስ በመውረድ ይህንን ችግር ማስተካከል አለበት።