የአማራ ፖሊስ በተለያዩ ወንጀሎች ስፈልገው ነበር ያለውን ዘመነ ካሴን መያዙን ገለጸ

ዘመነ ካሴ

የፎቶው ባለመብት, facebook

የምስሉ መግለጫ, ዘመነ ካሴ

የአማራ ክልል ፖሊስ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥሮ ሲፈልገው እንደቆየ የገለጸውን ዘመነ ካሴን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ዘመነ ካሴ የክልሉ መስተዳደር ከወራት በፊት ሕግ ማስከበር ያለውን ዘመቻ ባካሄደበትና በሺዎች የሚቆጠሩ “ሕገ ወጥ ያላቸውን ታጣቂዎች” በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ሲፈለጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዳለው ዘመነ ካሴን በተለያዩ ወንጀሎች ሲፈልገው እንደነበረና ከወራት በኋላ በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር ውስጥ እንደያዘው ገልጿል።

ዘመነ ካሴ በአማራ ክልል በጎጃም አካባቢ የሚንቀሳቀውና እራሱን የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ፋኖ በማለት የሚጠራው ቡድን ሰብሳቢ እንደሆነ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ መናገሩ ይታወሳል።

ፖሊስ እንዳለው ዘመነ ካሴ የተያዘው በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 03 ውስጥ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ተደብቆ ሳለ ከኅብረተሰቡ ባገኘው ጥቆማ መሠረት ነው።

የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ክፍል ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ክንዱ ወንዴ እንዳሉት ዘመነ በተያዘበት ጊዜ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ መያዙንና ሌሎች ምርመራ እና ፍተሻ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ አካሄድኩት ባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከ4 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህ ወቅት ዘመነ ካሴን ጨምሮ ሌሎች በፋኖ ቡድን አባልነት የሚታወቁና ሌሎች የታጣቂ ቡድን አባላት በፀጥታ ኃይሎች ሲፈለጉ እንደነበር ተነግሯል። በዚህም ዘመነ ካሴ እስከ ዛሬ ድረስ ያለበት ሳይታወቅ ቆይቶ ነበር።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው በቁጥጥር ስር የዋሉት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች ብዛት 4 ሺህ 552 እንደሆነና ከእነዚህ ውስጥ 210 የሚሆኑት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ምርመራ ተጣርቶባቸው የተከሰሱና በሕግ ጥላ ስር ማድረግ ሳይቻል የቆዩ መሆናቸው ተገልጾ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች ከተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከወጡ በኋላ በተለያዩ ቡድኖች የተደራጁ ኢመደበኛ ታጣቂ ቡድኖች በክልሉ ውስጥ የደኅንነት ስጋት መፍጠራቸውን የገለጸው መስተዳደሩ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር እርምጃ መውሰዱን አሳውቋል።

በዚህም “ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስ” አሳውቆ የመሳሪያ ምዝገባ ማካሄዱ ይታወሳል።

በወቅቱ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደተናገሩት “የመንግሥትን የማድረግ አቅም እና የሕግ የበላይነትን በመፈታተን በክልሉ ሥርአት አልበኝነት እንዲነግስ” አድርገዋል ብለዋል።