በኮሎምቢያ ታግተው የነበሩ የፖሊስ አባላት ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኮሎምቢያ ደቡባዊ ካኬታ ግዛት በነበረው የተቃውሞ ሰልፎች ታግተው የነበሩ የፖሊስ አባላት እና የነዳጅ ማውጫ ሰራተኞች ነጻ መውጣታቸውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ተናገሩ።
ባለፈው ሐሙስ የነዳጅ አውጭው ኩባንያ፣ ኤመራልድ ኤነርጂ ግቢ በነዋሪዎች ከተዘጋ በኋላ ብጥብጥ ተቀስቅሷል።
ነዳጅ በሚወጣበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች መንገዶችን እንዲሰራ ኩባንያውን እየጠየቁም ነበር።
የኮሎምቢያ ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ የታገቱት 79 ፖሊሶች እና ዘጠኝ የነዳጅ ማውጫ ሰራተኞች እንዲለቀቁም ጠይቀው ነበር።
በተነሳው አለመረጋጋት አንድ የፖሊስ አባል እና ሰላማዊ ሰው ተገድለዋል።
የታገቱት የፖሊስ አባላትና ሰራተኞች መለቀቅን በተናገሩበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ግለሰቦች ሞት ተጠያቂነት እንዲሰፍን ምርመራ እንዲጀመር አዘዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አልፎንሶ ፕራዳ፣ቀደም ብለው ግለሰቦቹ በጥይት መገደላቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች የአገሪቱ ቀደምት ሕዝቦች ሲሆኑ ኤመራልድ ኤነርጂ ነዳጅ በሚያወጣበት ሳን ቪሴንቴ ዴል ካጓን የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲዘረጋም ጠይቀዋል።
የነዳጅ ኩባንያው በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የሮይተርስ የዜና ወኪል ቢጠይቀውም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የኮሎምቢያ ፖሊስ በግጭቱ ለተገደለው ሪካርዶ ሞንሮይ ለተሰኘው ፖሊስም በትዊተር ገጹ ኃዘኑን ገልጿል።
"ዛሬ ከምንጊዜውም በበለጠ አንድነታችን ተጠናክሯል" በማለት ፖሊስ በትዊተር ገጹ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን “ሪካርዶ ለሙያው ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል” ብሏል።
በስፍራው የአሸማጋይነት ሚና ነበረው የተባለው የኮሎምቢያ የሰብአዊ መብት እንባ ጠባቂ ሰራተኛ ካርሎስ ካማርጎ ተቃዋሚዎችን በማነጋገር በኩባንያው ላይ የቤንዚን ቦምቦችን እንዳይወረውሩ እንዳሳመኗቸው ተናግረዋል።
በኮሎምቢያ ውስጥ በነዳጅ እና በማዕድን ማውጫዎች አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ተቃውሞዎች የተለመዱ ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪዎች እነዚህ ኩባንያዎች መንገዶችን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መሠረተ ልማት እንዲገነቡም በተደጋጋሚ ሲጠይቁም ይሰማሉ።
ፖሊስ በበኩሉ በአውሮፓውያኑ 2016 የነበረውን የሰላም ስምምነት ያልተቀበለው የፋርክ አማጽያን ንኡስ ቡድን በግዛቱ ውስጥ እንደሚገኝ እና ከዚህ ግጭት ጀርባ ሊኖር ይችላልም ብሏል።
ከዚህ በተለየ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ባልተጠበቀ ሁኔታ የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በራሳቸው ልጅ እና ወንድማቸው ላይ የሙስና ወንጀል ምርመራ እንዲከፍት የሚጠይቅ መግለጫ በትዊተር ገጻቸው አውጥተዋል።
መግለጫቸው በትልቁ ልጃቸው ኒኮላስ ፔትሮ ቡርጎስ እና ወንድማቸው ሁዋን ፈርናንዶ ፔትሮ ኡሬጎ ላይ ስለቀረበው ክስ በዝርዝር አልገለጸም።












