የሩሲያው ታዋቂ የተቃዋሚ መሪ እስራት ወደ 19 ዓመት ተራዘመ

Alexei Navalny

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታዋቂውና በእስር ላይ የሚኘው የሩሲያው የተቃዋሚ መሪ አሌክሲይ ናቫልኒ የእስራት ጊዜው ወደ 19 ዓመት ተራዝሟል።

ይሁንና ናቫልኒ ደጋፊዎቹን በጥንካሬያቸው እንዲቀጥሉ አበረታትቷል።

ናቫልኒ የአክራሪዎች ድርጅትን በመመስረት እና በመደገፍ ነው ጥፋተኛ ተብሎ ወደ ዘብጥያ የወረደው። ናቫልኒ ግን የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።

ክሱ ፖለቲካዊ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይተቻል። የክስ ሂደቱ ከ2021 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረ ነው።

እንደዚህ አይነት እስረኞች በሩሲያ ልምድ በከፍተኛ የጥበቃ ሁኔታ የሚታሰሩ ናቸው።

አሁን የተበየነውን የ19 ዓመት እስራት ተከትሎ ናቫልኒ ከእስካሁኑም የከፋ ቁጥጥር እና ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው ግንኙነቱ ሊቋረጥ ይችላል ተብሏል።

ምናልባትም ከቅርብ ቤተሰቦቹ እና ጠበቆቹ ውጭ ሌላ ሰው እንዳይጎበኘው ሊደረግ ይችላል ተብሏል።

የእስራት መራዘሙ ብይን ከተሰጠ በኋል ናቫልኒ በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ባስተላለፈው መልዕክት፣ “እኔም ሆንኩ እናንተ መፍራት የለብንም። ፑቲን ግቡን ሊመታ አይገባም። የመቃወም ወኔያችሁን እንዳታጡ” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍርድ ሂደቱ ላይ እንደሌሎች ጋዜጠኞች ሁሉ ቢቢሲም በስፍራው ተገኝቷል። ነገር ግን ናቫልኒ ጥፋተኛ ቢባልም የተበየነበት የእስራት መጠን ግልጽ አልነበረም። በኋላ ላይ ግን ናቫልኒ ራሱ 19 ዓመት መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጿል።

“19 ዓመት በተለየ የእስራት ሁኔታ እንዳሳልፍ ተፈርዶብኛል። አሃዙ ምንም ማለት አይደለም። እንደሌሎቹ የፖለቲካ እስረኞች የእኔም የዕድሜ ልክ እስራት መሆኑን እረዳለሁ። ዕድሜ የሚለካው ደግሞ በእኔ የመኖር ዕጣ ወይም ደግሞ በአገዛዙ እርዝማኔ ነው” ብሏል።

አዲሱ ብያኔ በዳኝነት ሚዛናዊነት እና ፍርድ ቤትን ለፖለቲካ አጀንዳ እንደመሳሪያ መጠቀም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሃላፊ ቮልከር ቱርክ አሳስበዋል።

የናቫልኒ ፕረስ ሴክሬታሪ ኪራ ያርሚሽ ደግሞ “ፑቲን እስከቻለው ድረስ ብዙ የአሌክሲይ ደጋፊዎችን ማስፈራራት ይፈልጋል” ያሉ ሲሆን “በመሆኑም ፑቲንን ምንገላገልባቸው ሁሉንም መንገዶች እንጠቀማለን፣ ያኔ አሌክሲይ ነጻ ይሆናል” ብለዋል።

ናቫልኒ ለአስርት ዓመታት በሩሲያ ሲካሄድ የነበረውን ሙስና በማጋለጥ ይታወቃል።

የሩሲያን መንግሥት በመነቅነቅ እና ሰፊ የሕዝብ ድጋፍን በማፍራት ናቫልኒ በሩሲያ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪው ነው።

ናቫልኒ በዚህ ተቀባይነቱ ምክንያት በ2020 ሳይቤሪያ ውስጥ ተመርዞ የጤና እክል ገጥሞት ነበር።

በኋላ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳሳዩት ናቫልኒን በመመረዝ ሂደት የሩሲያ የአገር ውስጥ ደኅንነት (ኤፍኤስቢ) እጁ ሳይኖርበት አይቀርም።

ከመመረዝ ሕመሙ ከዳነ በኋላ ናቫልኒ እስራት ሊጠብቀው እንደሚችል ቢነገረውም ማስጠንቀቂያውን ውድቅ በማድረግ በ2021 ወደ ሩሲያ ተመለሰ። ሞስኮ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ ወዲያውኑ ታሰረ።