የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ወንጀል የሚያደርገውን ሕግ አጸደቀ

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የጾታ ለውጥ አቀንቃኝ

የኡጋንዳ ፓርላማ በአገሪቱ ውስጥ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን የሚያደርገውን ረቂቅ ሕግ አጸደቀ።

ፓርላማው ማንኛውንም ራሱን በተመሳሳይ ጾታ ግንኑትነት አፍቃሪነት የመደበ፣ ወይም የጾታ ለውጥ ያስደረገ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ምሕጻራቸው ኤል-ጂ-ቢ-ቲ-ኪው ዝርዝር ውስጥ የሚካተት የጾታ ዝንባሌ ያለው ዜጋን ሁሉ ወንጀለኛ ያደርጋል።

በጸደቀው አዲሱ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ያለው ዜጋ ዘለግ ያለ የእስር ጊዜ ይጠብቀዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ሕጉ እነዚህን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን በጉያው ያቀፈ፣ በቤተሰብ ደረጃ ያስጠለለ፣ ወዳጃቸው የሆነ ወይም አብሯቸው ያለ ሰው “እከሌ እና እከሌ” ብሎ ለሕግ አካላት ማንነታቸውን የማጋለጥ ግዴታን በሌሎች ላይ ይጥላል።

በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ቀድሞም ሕገ ወጥ ተደርጎ ነው የቆየው።

ይህ ሕግ ከሕገ ወጥነቱ አልፎ ነገሩን ወንጀል እና በተራዘመ እስር የሚያስቀጣ ያደርገዋል።

በዚህ ወር መጀመርያ ለፓርላማ የቀረበው ይህ ሕግ በከፍተኛ ድምጽ ነው ትናንት ማክሰኞ የጸደቀው።

ከዚህ በኋላ ሕጉን የመሻር ብቸኛ ሥልጣን ያላቸው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው። ምናልባት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዳይሻክር እና እርዳታ እንዳይቆም ከፈለጉ ፕሬዝዳንቱ ሕጉ እንዳይጸና ሊወስኑ ይችላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ካልሆነ ግን ሕጉ ላይ በፈረሙ ቅጽበት ተፈጻሚነቱ ይረጋገጣል።

በዚህ ሕግ ልጆችን ለዚሁ ለተመሳሳይ ጸታ ያጨ ወይም ያስተላለፈ የእድሜ ይፍታህ ፍርድ ይጸናበታል።

በዚህ አዲስ ሕግ መሠረት በተመሳሳይ ጸታ መብት ዙርያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግንኙነቱን የሚያበረታታ ማንኛውንም የሕትመት ውጤት ማተም አልያም በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ማሠራጨት አይችሉም።

ይህን ካደረጉ በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ።

በኡጋንዳ የሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ሕጉ በከፍተኛ ሁኔታ ለጥቃት እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

በጎርጎሮሲያዊያኑ አቆጣጠር በ2014 ተመሳሳይ ሕግ ጸድቆ የነበረ ሲሆን የኡጋንዳ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ግን ሕጉ ተጸፋሚ እንዳይሆን ወስኖ ነበር።

ያን ጊዜ የሕገ መንግሥቱ ፍርድ ቤት ረቂቁን ውድቅ ያደረገው ፓርላማው ይህን ሲያጸድቅ የተሟሉ አባላት ባልተገኙበት ነበር በሚል ነው።

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ምዕራባውያን አገራት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችን መብቶች በአፍሪካ አገራት ላይ በኃይል ለመጫን እየጣሩ ነው ሲሉ የወቀሱት ባለፈው ሳምንት ነበር።

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መጋቢት 07/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ ፓርላማ ቀርበው ንግግር ሲያደርጉ፣ “እንግዳ የሆነ ባህል” ያሉትን የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንድንፈቅድ ምዕራባዊያኑ ማዕቀብ በመጣል ጫና ያሳድራሉ ብለዋል።

ሙሴቬኒ ጨምረውም፣ “ምዕራባውያን የራሳቸውን አሠራር በሌሎች ላይ ለመጫን የሚያባክኑትን ጊዜ ማቆም አለባቸው” ብለው ነበር።

ይህን አስተያየት ፓርላማ ተገኝተው የሰጡት ፕሬዝዳንቱ አዲሱን ሕግ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ተጠቅመው ሥራ ላይ እንዳይውል ያደርጋሉ የሚል ግምት የለም።

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ከ30 በሚበልጡ የአፍሪካ አገራት ክልክል አልያም ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል።