ኢትዮጵያ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መግለጫ ወገንተኛ እና ከፋፋይ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, mofa
ኢትዮጵያ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የደረሰበት ድምዳሜ አንድን ወገን ነጻ የሚያወጣ፣ ጊዜውን ያልጠበቀ እና አቀጣጣይ ነው ስትል ወቀሰች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲሉ መሥሪያ ቤታቸው የደረሰበትን ድምዳሜ ሰኞ መጋቢት 11/2015 ዓ.ም. መስጠታቸውን ተከትሎ ነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ የሰጠው።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው ውስጥ የተካተቱትን ጥቅል ውግዘቶች አይቀበልም። ምንም ዓይነት እሴት የለውም” ሲል የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአንድ ወገን እና የተቃዋሚነትን አቀራረብ የያዘ ነው ሲልም ዛሬ መጋቢት 12/2015ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ተችቷል።
በተጨማሪም በግጭቱ ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ወገኖችን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚወቅስ በመሆኑ የተመረጠ ነው ብሏል።
ከጦር ወንጀሎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች ግድያዎችን፣ መድፈር እና አስገዳጅ ማፈናቀልን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአማራ ኃይሎች አባላት በምዕራብ ትግራይ አስገዳጅ ማፈናቀል እና የዘር ማጽዳት ወንጀል መፈጸማቸውንም ነው ብሊንከን ያሳወቁት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የአሜሪካ ድምዳሜ ያለ ምንም ምክንያት አንዱን ወገን ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክስ ነጻ የሚያደርግ ይመስላል ብሎታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የትኛውን ወገን እንደሆነ በግልጽ ባያስቀምጥም የአሜሪካ መንግሥት ይፋ ያደረገው ሪፖርት የህወሓት ኃይሎችን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል አልጠቀሳቸውም።
በዚህ ድምዳሜ ያልተስማማው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ይህ አካል መድፈር እና ሌሎች የወሲባዊ ጥቃት ዓይነቶች ስለመፈጸማቸው ግልጽ እና በርካታ ማስረጃዎች አሉ” ብሏል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድምዳሜም ሆነ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየት ላይ የህወሓት አመራሮች እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

የፎቶው ባለመብት, mofa
በተጨማሪም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አላማው ምንም ይሁን ምን ያወጣው ሪፖርት አቀጣጣይ ነው ሲልም ነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የወቀሰው።
“አንድን ማኅበረሰብን በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ለማጋጨት በሚውሉ ዘመቻዎች ላይ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አቀጣጣይ ነው። ይህ ከአሜሪካ የመጣ ወገንተኛ እና ከፋፋይ አካሄድ ምክረ ሃሳብ ይጎድለዋል” ብሏል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን እየተገበረች ባለችበት ወቅት “ጥፋተኝነትን ማከፋፈል ተገቢ ያልሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ባለው ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት የአሜሪካን ድጋፍ የማያሳይ ነው” ብላለች።
ከዚህ ቀደም በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በጥምረት የሰሩትን የጋራ ምርመራ የጠቀሰው ይህ መግለጫ፣ የአሜሪካ ድምዳሜ አዳዲስ ግኝቶችን አላካተተም ብሏል።
ኢትዮጵያ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድምዳሜ ላይ ሌላኛው ያነሳችው ጉዳይ ወቅታዊ ስላለመሆኑ ነው።
ለዚህም አገሪቱ የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ላይ አገራዊ ምክክር ከተጀመረ በኋላ መውጣቱን በመጥቀስ ነው።
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አንደኛው መሠረት ተጠያቂነት እንደሆነም የጠቀሰው መግለጫው አሜሪካ ተፈጽመዋል የምትላቸውን ወንጀሎች እና ጥሰቶች ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች ይኖራሉ ብሏል።
ምርመራዎቹን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት እና የኢሰመኮን የጋራ ምርመራ ምክረ ሃሰቦችን እየተገበረ ያለው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተግባራቱን እያጠናከረ ይገኛል ብሏል።
የአሜሪካ ድምዳሜ “ወንጀለኛው ማንም ይሁን ማን ጥሰቶቹን በጥልቀት ለመመርመር የሚደረገውን አገራዊ ጥረት የሚጎዳም ነው” ብሏል።
የአንቶኒ ብሊንከን የቅርብ ጉብኝት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሻሻል ተስፋ የተጣለበት እንደነበር መግለጫው ጠቅሷል።
የአሜሪካ መንግሥት እንዲህ ዓይነት መግለጫ ቢያወጣም “የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ጋር የተካሄደው ግልጽ ውይይት እና መግባባት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ተስፋ ያደርጋል” ብሏል።
በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት ብሊንከን “እነዚህ ወንጀሎች ብዙዎቹ በዘፈቀደ ወይም በጦርነት ውስጥ የተከሰቱ ሳይሆን ሆን ተብለው ታስበው የተፈጸሙ ናቸው” ብለዋል።
ብሊንከን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአገራትን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን በተመለከተ የሚያደርገውን ግምገማ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ በተደገረበት ወቅት መሥሪያ ቤቱ ያሉትን መረጃዎች መርምሮ ድምዳሜ ደርሷል ብለዋል።
ይህ ድምዳሜ በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ወዲያውኑ የሚያስከትለው ለውጥ እንደማይኖር ቢገልጹም፣ ወንጀሎቹን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።












