ዛሬ ከሚጀምረው የተኩስ አቁም ቀደም ብሎ የሱዳን ኃይሎች ከባድ ውጊያ ማድረጋቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዛሬ ሰኞ ምሽት ይጀምራል የተባለው እና ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱ ከተነገረ በኋላ እሁድ ዕለት በሱዳን ተፋላሚ ኃይሎ መካከል ውጊያ ሲካሄድ እንደነበር ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከዋና ከተማ ካርቱም አቅራቢያ በሚገኝ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋነኛ የአየር ኃይል ሠፈሩ ላይ እሁድ ዕለት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የተከፈተበትን ጥቃት እየተከላከለ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአየር ማረፊያውን የሱዳን ሠራዊት ተቀናቃኞቹ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲጠቀምበት የቆየ ሲሆን፣ በግጭቱ መጀመሪያ ላይ የውጭ አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት ሲገለገሉበት ነበር።
ይህ ውጊያ መካሄድ የጀመረው ሁለቱ ወገኖች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረሳቸው ከተነገረ በኋላ ነው።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ቀደም ሲል የተደረሱ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች ብዙም ሳይቆዩ መጣሳቸው ይታወሳል።
በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አማካይነት በወጣው መግለጫ መሠረት አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም “ተፈጻሚነቱን በሚቆጣጠር አካል” ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል።
ለአንድ ሳምንት ይቆያል በተባለው በዚህ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም ስምምነት የሱዳን ባለሥልጣናት መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አደራዳሪነት ጄዳ ውስጥ የተደረሰው የተኩስ አቁም ሊጸና የሚችለው በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች የሚታገዝ ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪ አካል ሲኖር ብቻ መሆኑን በርካታ የካርቱም ነዋሪዎች ይናጋራሉ።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ እምነት ያጡ የካርቱም ነዋሪዎች አሁንም በበርካታ አውቶብሶች እየተሳፈሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተጓዙ ነው ተብሏል።
ሃያ በሚሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተሳፈሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላት ወደ ዋዲ ሳኢድና አየር ማረፊያ ለመጠጋት በአቅራቢያው ያለውን ድልድይ መሻገራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ሠራዊትም በምላሹ ከባድ መድፎችን መተኮሱ የዐይን እማኞች መስክረዋል።
ቁልፍ የሆነውን የአየር ማረፊያ ለመቆጣጠር ሁለቱም ኃይሎች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። የሱዳን ጦር ሠራዊት አየር ማረፊያው በቁጥጥሩ ስር እንዲቆይ ለማድረግ የመከላከል ውጊያ ማድረጉን ሲቀጥል፣ ተቀናቃኞቹ ደግሞ በእጃቸው ለማስጋበት ሲሉ ውጊያው ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የሱዳን ጦር ካርቱምን እና በዙሪያዋ ያሉ ሁለት ቁልፍ ከተሞችን መልሶ በእጁ ለማስገባት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በአየር ጥቃት ማዳከም ዋነኛ ስልቱ በመሆኑ በአየር ማረፊያው ዙሪያ ውጊያው ሊቀጥል ይችላል።
በኦምዱርማን ከተማ ላይ እሁድ ዕለት የአየር ድብደባ መፈጸሙን እና በከተማዋ ደቡባዊ ክፍል ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ቀደም ሲል የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተግባራዊ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ጠቅሶ፣ የአሁኑ ግን ከቀደሙት ወሳኝ ልዩነት እንዳለው አመልክቷል።
መግለጫው ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ “አሁን ጄዳ ላይ የተፈተመው ስምምነተ ከቀደሙት የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተለየ በአሜሪካ እና በሳዑዲ እንዲሁም ዓለም አቀፍ አካላት ድጋፍ ባለው የተኩስ አቁም ተቆጣጣሪዎች ተግባራዊነቱ ክትትል የሚደረግበት ነው” ብሏል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ የሱዳን ጦር ሠራዊት ለስምምነቱ ተገዢ እንደሚሆን የገለጸ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።
ለሰባት ቀናት ይቆያል በተባለው በዚህ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተኩስ አቁም ስምምነት የሱዳን ባለሥልጣናት መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ የተቀሰቀሰው ውጊያ ሱዳንን ወደ ከባድ ቀውስ የተከተታት ሲሆን፣ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎችንም ለመፈናቀል እንደዳረገ ይታሰባል።
በአገሪቱ የምግብ፣ የገንዘብ እና የሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች ክምችት በፍጥነት የተመናመነ ሲሆን፣ የእርዳታ ድርጅቶች አብዛኛው ግጭት ወደ ተካሄደባት ዋና ከተማዋ ካርቱም አስፈላጊ እርዳታ ለነዋሪዎች ማቅረብ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ቆይተዋል።
ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች የእርዳታ አቅርቦት እንዲካሄድ እንዲፈቅዱ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እንዲያደርጉ እና ኃይሎቻቸውን ከሆስፒታሎች እንዲያስወጡ ሲጠየቁ ቆይተዋል።
በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ድርድር ሲመሩ የነበሩት አሜሪካ እና ሳዑዲ እንዳስታወቁት፣ አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ነው ተብሏል።
አሁን ሱዳንን ከባድ ቀውስ ውስጥ የከተታት ግጭት የተቀሰቀሰው በሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በቆዩት የአገሪቱን ሉዓላዊ የሽግግር መንግሥትን በዋናነት እና በምክትልነት ሲመሩ በቆዩት የጦር ኃይሎቹ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሚመሯቸው ወታደሮች መካከል ነው።
ለቀናት ከቆየ ውጥረት በኋላ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላቱን በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች ማሰማራቱን ተከትሎ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዦች ስጋት ውስጥ በመግባታቸው ሚያዚያ 07/2015 ዓ.ም. ካርቱም ውስጥ ግጭቱ መቀስቀሱ ይታወሳል።












