በሁለት ቀውሶች መካከል ተይዘው መሄጃ ያጡት ኤርትራውያን ስደተኞች

ለመጓዝ ከሚጠባበቁ ቤተሰባቸው ጋር በፓሎይች አየር ማረፊያ የተሰበሰቡ ህጻናት
የምስሉ መግለጫ, ለመጓዝ ከሚጠባበቁ ቤተሰባቸው ጋር በፓሎይች አየር ማረፊያ የተሰበሰቡ ህጻናት
    • ፀሐፊ, በካትሪን ቢያሩሃንጋ
    • የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ኒውስ የአፍሪካ ዘጋቢ

የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማውጫ ሠራተኞችን ሲያገለግል የቆየው የፓሎይች አየር ማረፊያ አሁን አንድ ወር የሆነውን የሱዳን ጦርነትን የሸሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ ሆኗል።

መጸዳጃ ቤት፣ የቧንቧ ውሃ እና ማብሰያ ቦታ በሌለበት የተሰበሰቡት ሰዎች በሻንጣዎቻቸው ዙሪያ ተኮልኩለው ወይም ጊዜያዊ ከለላ ሰርተው ጋደም ብለው በቀጣይ ሊኖር የሚችል በረራን ይጠባበቃሉ።

በግጭት እየታመሰች ካለችው የሱዳን ድንበር አራት ሰዓት ተጉዘው በአየር ማረፊየው ውስጥ የተሰባሰቡት ሰዎች ከዚያ በመነሳት ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ ተስፋ አድርገው እየተጠባበቁ ነው።

ነገር ግን ከአየር ማረፊያው የሚነሱ ጥቂት በረራዎች ብቻ ከመኖራቸው ባሻገር፣ መቼ አውሮፕላን አግኝተው ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ እንደሚችሉ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ቀደም ሲል በአገራቸው ካለው ጭቆና ሸሽተው ሱዳን የቆዩ ኤርትራውያን ለሁለተኛ ጊዜ የተሰደዱ ይገኙባቸዋል። እዚህም ወደ የትም ለመሄድ ተቸግረው እየተጉላሉ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት ሱዳን ውስጥ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት ከ136,000 ሺህ በላይ ኤርትራውያን በአገሪቱ ውስጥ ነበሩ።

የአገራቸውን ባለሥልጣናትን የአጸፋ ቅጣት በመፍራት አብዛኞቹ ኤርትራውያን ለጋዜጠኞች ስማቸውን መናገር አይፈልጉም።

ኤርትራ ከሞላ ጎደል የሕዝቧን አጠቃላይ ሕይወት የምትከታተል በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር የበዛባት አገር ስትሆን፣ ብዙዎች ግዴታ በሆነው ብሔራዊ አገልግሎት ላለመሳተፍ ጥረት ያደርጋሉ ከአገራቸውም ይሰደዳሉ።

ደቡብ ሱዳን ውስጥ ወደሚገኘው ፓሎይች አየር ማረፊያ ከአምስት ቀናት በፊት የደረሰው ተስፊት ግርማይ ግን ከቢቢሲ ዘጋቢ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነው።

በዙሪያው ያሉትን ድንኳኖች እየተመለከተ “እዚህ ያለንበት ሁኔታ እንኳን ለሰው ለእንስሳት እንኳን የማይሆን ነው” ሲል አስቸጋሪውን ሁኔታ ይገልጸዋል።

ተስፊት ብቻውን ስለሆነ በቦታው ካሉ ከአንዳንዶች በተሻለ ዕድለኛ መሆኑን ይናገራል።

“እኔ ውጪ መተኛትን እና በቀን አንድ ጊዜ መመገብን ልቋቋመው እችላሉሁ። ትልቁ ችግር ግን ከህጻናት ጋር ላሉት ሰዎች ነው። አራት እና አምስት ልጆችን ይዘው የመጡ ሰዎች አሉ” ብሏል ተስፊት።

በኤርትራ እየተዳከመ ባለው ምጣኔ ሀብት ምክንያት፣ ሥራ ለማግኘት ከተቻለም ወደ ሌላ አገር ለመሻገር ከወራት በፊት ነበር ከአገሩ ተሰዶ ወደ ሱዳን የገባው።

ነገር ግን ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ግጭት ሸሽተው ወደ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ኤርትራውያን ወደ የትም ለመሄድ በማይችሉበት ሁኔታ እየተጉላሉ ነው።

ከ700 በላይ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን ገብተዋል።

ስደተኞች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሱዳንን ጦርነት ሸሽተው ወደ ደቡብ ሱዳን የገቡ ኬንያን፣ ኡጋንዳን እና ሶማሊያን የመሳሰሉ አገራት ዜጎች በመንግሥታቶቻቸው አማካይነት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በርካታ ኤርትራውያን ግን መንግሥታቸውን ስለመፈሩ ወይም ምንም ተስፋ ስለማይታያቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ አይፈልጉም።

ተስፊት እንደሚለው በፓሎይች አየር ማረፊያ የሚገኙ ኤርትራውያን ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በሚጓዙ በረራዎች ላይ እንዳይሳፈሩ ተከልክለዋል። እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች ለመግባት አይፈልጉም።

ከአየር ማረፊያው በስተሰሜን ሦስት ሰዓት በሚያስጉዘው እና ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው ጊዜያዊ የስደተኞች ካምፕ በበርካታ ሰዎች እየተጨናነቀ ነው።

ሬንክ በሚባለው ቦታ የሚገኘው እና ተዘግቶ የቆየው የቀድሞው አፐር ናይል ዩኒቨርስቲ ግቢ አሁን ከ6,000 በላይ ሰዎች ተጠልለውበታል። በአቅራቢያው ያለው ቁጥቋጦም ሳይቀር እየመጡ ያሉ በርካታ ስደተኞችን ለማስተናገድ እየተመነጠረ ነው።

እዚህም ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገች ኤርትራዊት ከአንድ የመማሪያ ክፍል ደረጃ ላይ ከሦስት ልጆቿ ጋር ተቀምጣለች። ባሏም ለቤተሰቡ የሚሆን ምግብ ፍለጋ ወደ ከተማ ወጥቷል።

እሷም “እግዚአብሔርን በምፈልገው መንገድ ማምለክ ስላልተፈቀደልኝ በአገሬ ለመኖር አልቻልኩም” ትላለች ከኤርትራ እንድትወጣ ያስገደዳትን ምክንያት ስትናገር።

የወንጌላዊ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆነችው ይህች ሴት በአገሯ ችግር ይገጥማት እንደነበር ትናገራለች። በኤርትራ በሃይማኖቶች ላይ ቁጥጥር የሚደረግ ሲሆን፣ በመንግሥት ከተፈቀዱት ውጪ የሆኑ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎች ለእስር ይዳረጋሉ።

ከካርቱም ሸሽተው ከወጡ በኋላ፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ለማቅናት ተስፋ አድርጋ ነበር። ነገር ግን ያ የሚቻል ነገር እንዳልሆነ ተረድታለች።

“ማንም ወደ ጁባ ለማለፍ አይችልም። ለኤርትራውያን ብቻ መንገዱ ዝግ ነው። ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል አላውቅም።”

የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ መሥሪያ ቤታቸው አገራት ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው እንዲመልሱ ለማድረግ የኤርትራን ጨምሮ የሁሉንም ኤምባሲዎች ጠይቆ ነበር።

ነገር ግን ወደ አገራቸው መመለስ የማይፈልጉ እና ከኤምባሲያቸው ጋር ግንኙነት መፍጠር የማይሹ በመኖራቸው የኤርትራውያኑ ጉዳይ የተወሳሰበ እንደሆነ መረዳታቸውን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም ተጠባባቂ ሚኒስትሩ ወደ ጁባ የደረሱ ኤርትራውያን በግድ ወደ መጡበት ፓሎይች እንዲመለሱ ተደርገዋል መባሉን አላስተባበሉም።

ለዚህም ምክንያቱ የኤርትራ ኤምባሲ ዜጎቹን በአውሮፕላን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስለማያደርጋቸው እና ጁባ ውስጥ የስደተኞች ካምፕ ባለመኖሩ ወደ ሌላ ቦታ መወሰድ አለባቸው ይላሉ ሚኒስትሩ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በቅርቡ እንዳሉት በጎረቤት አገር ሱዳን ያለውን ግጭት ሸሽተው ወደ አገራቸው ለሚገቡ ሁሉ በራቸው ክፍት እንደሆነ ገልጸዋል።

“ኤርትራ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሚመጡ ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን በሯ ክፍት ነው። ያለምንም ሽርጉድ የሚሰደዱትን መቀበሏን ትቀጥላለች፣ ያላትንም ታካፍላለች” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ሳንዲ ማኒጄል ከልጆቿ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ሳንዲ ማኒጄል ከልጆቿ ጋር

በአንድ ወር ውስጥ 60,000 የሚደርሱ ሰዎች የደቡብ ሱዳንን ድንበር ተሻግረው አገሪቱ ስደተኞችን ለማስተናገድ የምትችልበትን አቅሟን አጨናንቀውታል።

በፓሎይች አየር ማረፊያ አንዳንድ ደቡብ ሱዳናውያን ሳይቀሩ ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል ለመሸጋገር ጥረት እያደረጉ ነው።

ከእነዚህም መካከል አንዷ የሆነችው ሳንዲ ማኒጄል ከአምስት ልጆቿ ጋር ወደየትም መሄድ ሳትችል እየተጉላላች ነው።

ለመጓዝ የአየር ትኬት ብታገኝም እየጠበቀች ጉዞው ለሌላ ጊዜ እንደተሸጋገረ እንደሚነገራት እና እንዲሁ በጥበቃ ላይ መሆኗን ተስፋ በመቁረጥ ስሜት “ሁሉም ነገር በዕድል የሚሆን ነው” ትላለች።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከፓሎይች በጭነት አውሮፕላኖች አማካይነት ነጻ በረራዎችን እያቀረበ ሲሆን፣ አስካሁን ከ7,000 በላይ ሰዎችን አጓጉዟል። ነገር ግን ይህ ለመጓጓዝ ከሚፈልጉት መካከል በጣም ትንሹ ቁጥር ነው።

የመንግሥት ዕቅድ ሁሉንም ከሬንክ እና ከፓሎይች በማስወጣት ምግብ እና መድኃኒት ወደሚያገኙበት ቦታ አዘዋውሮ ኑሯቸውን መልሰው እንዲጀምሩ ማስቻል ነው።

ነገር ግን ደቡብ ሱዳን ይህ ነው የሚባል የአስፓልት መንገድ የሌላት ከመሆኑም በላይ፣ የአገር ውጥ በረራዎችም ጥቂት ናቸው። ከፊሉ የአገሪቱ ክፍልም ከአውሮፓውያኑ 2013 አስከ 2018 ከተካሄደው ጦርነት አላገገመም።

በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት በቀጠለበት እና እየጨመረ የሚሄድ የራሷ እና የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ ግዛቷ መግባታቸው በቀጠለበት ሁኔታ ደቡብ ሱዳን ፈታኝ ሁኔታ እየገጠማት ነው።