የሱዳኑ ጦር መሪ ምክትላቸውና ተፋላሚያቸውን ጄነራል ከስልጣን አሰናበቱ

የሱዳን ጦር ኣዛዥ ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃንና ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሱዳን ጦር ኣዛዥ ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ምክትላቸውና ተፋላሚያቸው የሆኑትን ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲን ከስልጣን አሰናበቱ።

ጄነራል ሄምቲ በአሁኑ ወቅት በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት ጦሩን በተቀናቃኝ ጎራ ሆነው እየተዋጉ ያሉና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ናቸው።

ሁለቱ ጄነራሎች ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ አገሪቷን እያስተዳደረ ያለው የሉዓላዊው ምክር ቤት ሊቀመንበር እና ምክትል ሆነው እያገለገሉም ይገኛሉ።

ጄነራል አል ቡርሃን አርብ እለት ባወጡት የውሳኔ አዋጅ የቀድሞ አማጺ መሪ የሆኑትን ማሊክ አጋርን ምክትላቸው አድርገው ሾመዋል። አጋር አገሪቷን እየገዛ ያለው የሉዓላዊው ምክር ቤት አባል ናቸው።

የሉዓላዊው ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት እና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አዋጁን በአስቸኳይ እንዲተገብሩም ጄነራል አል ቡርሃን መመሪያ ሰጥተዋል።

የጦር አዛዡ ባለፈው ወር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በትነው ተዋጊዎቹን በአማጽያንነት የሰየሙ ሲሆን ይህም የሆነው ከመሪው ጄነራል ሄምቲ ጋር የስልጣን ሽኩቻ መፈጠሩን ተከትሎ ነው።

በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ነበር።

ሁለቱ ጄነራሎች ለሶስት አስርት ዓመታት ሱዳንን የመሯትን ኦማር አልበሽርን በአውሮፓውያኑ 2019 ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ አገሪቷንም ሲመሯት ቆይተዋል።

በቀጣናዊ እና አለም አቀፍ አጋሮች አማካኝነት የተደረሱ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ተጥሰዋል።

በጦርነቱ ቢያንስ 676 ሰዎች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል።