በየመን የበርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስክሬኖች ማግኘታቸውን ስደተኞች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, IOM
በሳዑዲ አቅራቢያ በሚገኝ የየመን ግዛት ውስጥ ባለስፍራ በጉዞ ላይ ሳሉ በተለያዩ ምክንያቶች የሞቱ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወረው አስከሬን የኢትዮጵያውያን መሆኑ ተነገረ።
በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ በድካም እና በረሃብ የሞቱት የሴት ስደተኞች አስከሬን የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪድዮዎች የበርካቶችን ልብ ነክቷል።
ምስሉ ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ያጡበትን ሁኔታ የሚያሳይ ሲሆን፣ ቢያንስ 20 የሚሆኑ ሴቶች እና ወንዶች መሬት ላይ ወድቀው ያሳያል።
እጅግ አሰቃቂ ምስል የያዘውን ቪዲዮ መቼ እና የት ቦታ ላይ እንደተቀረጸ ቢቢሲ እስካሁን ማረጋገጥ አልቻለም።
ነገር ግን በምስሉ ላይ የሚታዩት ሴት ስደተኞች በጦርነት ውስጥ ካለችው የመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ በእግር ጉዞ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ቢቢሲ ትግርኛ ከስፍራው ካነጋገራቸው ስደተኞች መረዳት ችሏል።
አደጋው የደረሰው በየመን እና ሳዑዲ መካከል የሚገኘው ራጎ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተናግረዋል።
አንድ አስከሬኖቹ ያሉበት ቦታ ድረስ ሄዶ መመልከቱን የሚናገረው ስሙ እንዲገለጽ ፍቃደኛ ያልሆነው ስደተኛ እንዳለው ሟቾቹ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም. ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጉዞ መጀመራቸው እና “በአስቸጋሪ የእግር ጉዞ ምክንያት ለድካም እና ለሞት የተዳረጉ ናቸው” ብሏል።
“[አስክሬናቸውን] አይተነዋል፤ ምንም ማድረግ ስለማንችል እየቀበርን ነው። የመቃብር ቦታ የለም፤ አካባቢው እየሸተተ ነው። አብዛኛው አስክሬን አልተቀበረም” በማለት ሁኔታውን ገልጿል።
በጉዞው ላይ የተዳከሙ ሴቶች እና ወንዶች ስደተኞች ሞት ለሞት መዳረጋቸውን ለቢቢሲ የገለጸው ስደተኛው፤ ጉዞው ውጣ ውረድ የሞላበት በመሆኑ ብዙ ስደተኞች ደክመው መንገድ ላይ እንደሚቀሩ ይናገራል።
“በረሃውን በእግር ነው የሚያቋርጡት፤ የደከማቸው በአዘዋዋሪዎች ይደበደባሉ። ሴቶቹ ውሃ ሲጠማቸው፣ ሲርባቸው፣ እና ሲደክማቸው። የሚሸከማት ወይም የሚያግዛት ከሌለ መንገድ ላይ ለሞት ትተዋቸው ይሄዳሉ።”
ስፍራውን የተመለከተ ቢቢሲ ያናገረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ እንደሚለው ከሆነ “በአካባቢው የሞቱት ወደ 20 የሚጠጉ ስደተኞች ናቸው” ብሏል።
ወዲ ራያ በሚል ስም እንዲጠቀስ የጠየቀው ሌላ ቢቢሲ ያነጋገረው ስደተኛ ደግሞ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የተለያየ እንግልት እንደሚገጥማቸው ገልጿል።
ስደተኞቹ “ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየሄዱ ነበር። ይህ መንገድ በጣም ረጅም ነው፤ በአቅራቢያው ምንም ምግብ ወይም ውሃ የለም። በረሃብ፣ በፀሐይ፣ በድካም ተጎዱ። መንገድ መሪዎቹ የደከሙትን ይደበድባሉ። ለሰው ሕይወት ግድ ስለሌላቸው፣ ያልቻሉትን መንገድ ላይ ጥለዋቸው ይሄዳሉ” ብሏል።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት እጅግ አደገኛ የሆኑ የስደት መንገዶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል፣ አብዛኛዎቹ በባሕር በኩል በመሻገር ወደ የመን ለመግባት ሲሞክሩ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
ቢቢሲ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ በሰራቸው ዘገባዎች ስደተኞቹ በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ የተፈጥሮ ሁኔታ በድካም እና በውሃ ጥም እንደሚሰቃዩ ያሳያሉ። ተሳክቶላቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡትም ከዚህ የተለየ ሁኔታ እንደማይገጥማቸው ይናገራሉ።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች እጃቸው በካቴና ታስሮ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ባወጧቸው ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች እንዳሉት በእንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ እህት ወንድሞቻቸውን ከኢትዮጵያ በተለይም ከትግራይ በሕገ ወጥ መንገድ ለማስጣት እንደሚጥሩ ገልጸዋል።
“በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ ስደት በተለይም ወደ ሳዑዲ አረቢያ መምጣት በአንገት ላይ ገመድ እንደማስገባት ያህል ነው” ሲል ስሙን መግለጽ ያልፈለገው ስደተኛ ለቢቢሲ የሁኔታውን አደገኝነት ተናግሯል።
‘የምሥራቅ መንገድ’ በመባል የሚታወቀው ሕገወጥ የስደት መንገድ በአፍሪካ እና በዓለም ካሉት እጅግ አደገኛ እና ውስብስብ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገዶች አንዱ ነው።
በባሕረ ሰላጤው አገራት ሥራ እና ተሻለ ሕይወት ፍለጋ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በተለይም ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የሚወጡ ስደተኞች በየዓመቱ ይህንን አደገኛ መንገድ ይከተላሉ።
እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ዘገባ ከሆነ ስደተኞቹ ረሃብ፣ የውሃ ጥም እና ድካምን ጨምሮ ለሕይወት አስጊ የሆኑ አደጋዎች ይገጥሟቸዋል።
ስደተኞቹ ብዙውን ጊዜ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ኢላማ የሚደረጉ ሲሆን፣ በተለይም በየመን አፈና፣ የዘፈቀደ እስራት፣ በታጣቂ ቡድኖች በግዳጅ መመልመል እንደሚገጥማቸው ተቋሙ ገልጿል።












