የቦይንግ የቀድሞ ሠራተኛ የደኅንነት ጥያቄዎች ካነሳ በኋላ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የቀድሞ የቦይንግ ሠራተኛ በአውሮፕላን ምርት ላይ የደኅንነት ስጋት አለኝ ካለ በኋላ በግዙፉ አውሮፕላን አምራች ላይ ምርመራ ተከፈተ።
ሳም ሳሌህፒር የቀድሞ የቦይንግ ኢንጂነር ሲሆን ኩባንያው ከደኅንነት ይልቅ ለትርፍ ቅድሚያ በመስጠት በ787 እና 777 አውሮፕላን ምርቶቹ ላይ አቋራጮችን እየተጠቀመ ነው ሲል ክስ አቅርቧል።
ሳም ስጋቱን ለኩባንያው ኃላፊዎች ሲናገር ከሥራው ሊባረር እንደሚችል ማስፈራሪያዎች እንደተሰጡት ተናግሯል።
ቦይንግ ግን የቀረበበት ክስ ትክክለኛ አለመሆኑን እና እያንዳንዱ የምርት ሂደት በአገሪቱ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ጥራት ደረጃ የሚያልፍ መሆኑን ተናግሯል።
ኩባንያው ጨምሮም ኢንጂነሩ የሚያነሳቸው ስጋቶች በአውሮፕላን ደኅንነት ላይ ምንም አይነት ችግር አያስከትሉም እንዲሁም የአውሮፕላኑን የሥራ ዘመን የሚያሳጥሩ አይደሉም ብሏል።
የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር በቦይንግ ላይ የተነሳውን የደኅንነት ጥያቄ እየመረመርኩ ነው ካለ በኋላ የቦይንግ የገበያ ድርሻ 2 በመቶ ቀንሷል።
ቦይንግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተነሱበት እና እያጋጠሙት ባሉ ከደኅንነት ጋር በተያያዙ ችግሮች ጫና ውስጥ ገብቷል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ንብረትነቱ የአሜሪካው ሳውዝዌስት አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለበረራ እየተነሳ ሳለ የሞተሩ ሽፋን ከወደቀ በኋላ ምርመራ ተከፍቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የአላስካ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች የሆኑ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ተከስክሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
ጫና ውስጥ የገባው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ ሥራቸውን እንደሚለቁ ተናግረዋል።
ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም. የሳም ጠበቆች ቦይንግ በ787 ምርት ሂደቱ ላይ በአውሮፕላኑ አካል ላይ ጫና ሊፈጥር የሚችል የምርት ሂደትን ተከትሏል ብለዋል።
ይህ የቀድሞ ሠራተኛ እንደሚለው ከሆነ ይህ አሰራር አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉ 1ሺህ አውሮፕላኖችን የአገልግሎት ዘመን ያሳጥራል ብሏል።
ጠበቆች እንደሚሉት ሠራተኛው የደኅንነት ስጋቱን ከተናገረ በኋላ በ777 አውሮፕላን ላይ እንዲሰራ ተዘዋውሯል።
በ777 አውሮፕላን ምርት ሂደት ላይም ሌላ የደኅንነት ስጋት መመልከቱን ለኃላፊዎች ከተናገረ በኋላ “ከሥራ እንደሚባረር ማስፈራሪያዎች እንደደረሱት፣ በስብሰባ እንዳይሳተፍ መደረጉን፣ ለሕክምና እረፍት መከልከሉን እና ከሙያው ውጪ የሆኑ ሥራዎች እንዲሠራ መደረጉን” ገልጿል።
የቦይንግ 787 ድሪምላይነር ግዙፍ አውሮፕላን ሲሆን አብዛኛውን ግዜ ረዥም ርቀት በሚሸፍኑ ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ ጥቅም ላይ ይውላል።
ቦይንግ ይህን አውሮፕላን እአአ 2011 ላይ ወደ ሥራ ካስገባ በኋላ ከጥራት ጋር የተያያዙ ብዙ ቅሬታዎች ሲደርሱት ቆይቷል።
በዚህም ቦይንግ ይህን አውሮፕላኑን ለአየር መንገዶች ማስተላለፍ አቁሞ ለጥቂት ዓመታት ለሚነሱበት ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጥት ሲሰራ ከቆየ በኋላ እአአ 2022 ላይ ዳግም አውሮፕላኑን ማስረከብ ጀምሯል።












