በአጭሩ የሙዚቃ ዓለም ቆይታው ዘመናትን የተሻገሩ ሥራዎችን ያበረከተው ሙሉቀን መለሰ

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ከሆኑት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው፣ ኋላም ዓለማዊውን ሙዚቃ በማቆም ለረጅም ዓመታት በመንፈሳዊው ሕይወት ውስጥ የቆየው ሙሉቀን መለሰ ማረፉ ተነግሯል።
ሙሉቀን መለሰ የሙዚቃ ሕይወቱን በመተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ፊቱን ካዞረ በኋላ ከአገሩ ኢትዮጵያ በመውጣት ኑሮውን በአገረ አሜሪካ አድርጎ ቆይቷል። እዚያም አርባ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ቆይቶ ነው ዜና እረፍቱ የተሰማው።
ሙሉቀን መለሰ አሁን በአማራ ክልል ውስጥ በምትገኘው በቀድሞዋ ጐጃም ክፍለ አገር፣ አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም. ነው የተወለደው።
በ1958 ዓ.ም. የእናቱን ሞት ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ሙሉቀን፣ ወደ ሙዚቃ የገባው ገና በአፍላ ጉርምስና እድሜው ወቅት ነበር።
በአጎቱ ስም የሚጠራው ሙሉቀን መለሰ፣ የተወለደው ከአቶ ታምር ጥሩነህ መሆኑን በአንድ ወቅት ሲናገር “ይህንን ስም ሳልቀይር መቅረቴ ይቆጨኛል” ብሎ ነበር።
ሙሉቀን ከእናቱ ሞት በኋላ ሊያሳድጉ ወደ አዲስ አበባ ያመጡት አጎቱ አቶ መለሰ፣ በመማሪያ ደብተሩ ላይ ሙሉቀን መለሰ ብለው ከጻፉ በኋላ ነበር በአጎቱ ስም እየተጠራ የቀጠለው።
ሙሉቀን የሙዚቃ ሥራውን የጀመረው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው እና በዘመኑ ታዋቂ በነበረው ‘ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ’ ውስጥ ነው።
ሙሉቀን እንደ በርካታ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቀኞች ሁሉ ወደ ሙዚቃው ዓለም የተሳበው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰን አይቶ መሆኑን እና ለረዥም ጊዜ እርሱን እያስመሰለ ሲሠራ መቆየቱን ይናገራል።
ሙሉ ለሙሉ በሙዚቃ ሥራ ውስጥ መሳተፍ ከጀመረበት ከፓትሪስ ሉሙምባ በኋላ በተለያዩ የአዲስ አበባ የምሽት ክቦች ሲሠራ ቆይቶ የፖሊስ ኦርኬስትራ አባልም ነበረ።
ፖሊስ ኦርኬስትራ በነበረበት ወቅትም ‘እምቧይ ሎሚ መስሎ’፣ ‘የዘላለም እንቅልፍ’፣ ‘እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረችኝ’፣ ‘ያ ልጅነት’፣ የተሰኙ እና ሌሎች በርካታ ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል።
ሙሉቀን ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ ለሦስት ዓመት ካገለገለ በኋላ እንደገና በምሽት ክበቦች መጫወት ጀመረ።
ከፖሊስ ኦርኬስትራ በተጨማሪ እስከ 1975 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት ከኢኬዌተርስ፣ ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር፣ ከሮሃ፣ ዳህላክ እና ኢትዮ ስታር ባንዶች ጋር ሰርቷል።

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
በአንድ ወቅት ከሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል የትኛውን አብልጦ እንደሚወድ የተጠየቀው ሙሉቀን ሁሉንም ሥራዎችቹን ዕኩል እንደሚያያቸው በመግለጽ በዜማ እና በዘፈን የተለዩ ናቸው የሚላቸውን ጠቅሶ ነበር።
“…በጣም የሚያረኩኝ…በዜማው እና በዘፈኑ…‘ሰውነቷ’ እና ‘ሆዴ ነው ጠላትሽ’…በሙዚቃ ጥራት እና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀነባበራቸው እና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‘ቼ በለው’ እና ‘ውቢት’” የተባሉትን ለእሱ ከሌሎቹ የተለዩ ነበር።
ሙሉቀን 17 ዓመታትን ያህል በሙዚቃው ሕይወት ውስጥ ሲቆይ ከድምጻውያን በቅድሚያ የአለማየሁ እሸቴ እና የምንሊክ ወስናቸው አድናቂ መሆኑን በአንድ ቃለመጠይቁ ላይ ተናግሮ ነበር።
ከእነርሱ ባሻገር የብዙነሽ በቀለ፣ የሒሩት በቀለ፣ የመሐሙድ አህመድ፣ የጥላሁን ገሰሰ አድናቂም መሆኑን ይናገራል።
ከ17 ዓመታት የድምጻዊነት ሕይወት በኋላ ሙሉቀን ዘፈንን ያቆመው ወደ መንፈሳዊ ሕይወት በማተኮሩ ነበር።
ሙሉቀን ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው ሙዚቃ ‘ነይ ነይ ወዳጄ’ የተሰኘውን መሆኑን የሙያ ባልደረቦቹ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረው ነበር።
ከአገር ወጥቶ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ አራት አስርት ዓመታት ያስቆጠረው ሙሉቀን መለሰ፣ አገሩ ትናፍቀው እንደሆነ ሲጠየቅ “... እኔ የሚናፍቀኝ የኢየሱስ ነገር ብቻ ነው።...” ብሎ ነበር።
ሙሉቀን ከዓለማዊው የሙዚቃ ሕይወት በመውጣት መንፈሳዊነትን አጥብቆ ኑሮውን በአሜሪካ አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ ካደረገ በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ አያውቀም።
በእነዚህ ዓመታት ሙሉቀን መለሰ ከዘፈን ሕይወት ራሱን ካገለለ በኋላ ፊቱን ወደ መንፈሳዊ ዝማሬ አዞረ። በዚህም የተለያዩ የመዝሙር ሥራዎችን ለወንጌል አማኞች አቅርቧል።
ምንም እንኳን ሙሉቀን መለሰ ሙዚቃን ከተወ አርባ ዓመታት ሊሆነው የተቃረበ ቢሆንም ከአስርታት በፊት የሠራቸው ሙዚቃዎቹ ዘመናትን በመሻገር አሁን ድረስ በተለያዩ ትውልዶች ተወዳጅ እና የሚደመጡ ናቸው።
ከዚህም የተነሳ በሸክላ እና በካሴት ዘመን የተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ እሱ መዚቃን ካቆመ በኋላ በተፈጠሩት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተቀናብረው በሲዲ እና በኢንተርኔት የሙዚቃ ማድመጫዎች በኩል እየተደመጡ ይገኛሉ።
በተጨማሪም የሙሉቀን ሙዚቃዎች በትውልዶች መካከል ካገኙት ተወዳጅነት የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት ጥቂት የማይባሉ ወጣት ድምጻውያን ደግመው ተጫውተዋቸው ለአድማጮች መቅረባቸው ይታወቃል።
የሙለቀን መለሰ ህልፈት ማክሰኞ ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም. ከተሰማ በኋላ በኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ዋነኛ መነጋሪያ ሆኖ በርካቶች ከሙዚቃዎቹ ጋር ያላቸውን ትዝታዎች እና ጥልቅ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።












