በአድዋ ከተማ ባልታወቁ ሰዎች ታግታ ሦስት ሚሊየን ብር የተጠየቀባት ታዳጊ

ማኅሌት

የፎቶው ባለመብት, MILLION

የምስሉ መግለጫ, ከታገተች ሦስት ሳምንት የሆናት የ16 ዓመቷ ማኅሌት

በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን አድዋ ከተማ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ የተወሰደችው የ16 ዓመቷ ልጅ እስከ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና ቦታ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቿ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ማኅሌት ተኽላይ ከሦስት ሳምንት በፊት ከሰዓት በኋላ 10፡30 ላይ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት ብላ በወጣችበት ወቅት ነው ታፍና መወሰዷን ታላቅ እህቷ ሚሊዮን ተኽላይ የገለጸችው።

ሚሊዮን እንደምትለው አጋቾቹ እህቷ እነሱ ጋር እንደሆነች እና እንድትለቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ ግለሰቦች እስከ አሁን ሁለት ጊዜ ወደ አባቷ ስልክ ደውለዋል።

“ድምጿን አልሰማንም፤ ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ ጊዜ ደውለው ነበር። አባታችንም ‘ምን እንደሚፈልጉ እና እንዴት እንደሚሰጣቸው ጠይቋቸው ነበር። እነሱም ‘አዘጋጅ የምንልህን ታዘጋጃለህ’ ብለው ስልካቸውን እየጠበቅን ነው” ብላለች።

ተማሪ ማህሌት በአድዋ ከተማ አዲ ማሕለኻ ተብሎ በሚጠራው አካበቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ‘ባስ ሰላም’ ተብሎ ወደ ሚጠራው የቋንቋ ትምህርት ቤት ብላ ወጥታ ሳትመለስ ቀርታለች።

“ረፍዶባት ስለነበረ ተጣድፋ ነው ከቤት የወጣችው። … ነገር ግን ወዳሰበችበት አልደረሰችም፤ ያገቷት ሰዎችም ወደ ቤት ተመልሳ በምትመጣበት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ነበር ወደ ባባ የደወሉት” ስትል እህቷ ታስረዳለች።

የታገተችው ተማሪ ማኅሌት 16 ዓመት ከሆነች ሁለት ወር አልሞላትም።

በዚህ ዓመት ወደ ሁለተኛ ደረጃ የሚያሸጋግራትን የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመፈተን እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ከትምህርቷ ጎን ለጎን ሌሎች ማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመውሰድና ቋንቋ በመማር ዝግጅት ታደርግ ነበር።

ቤተሰቦቿ ማኅሌትን “ሥነ ምግባር ያላት የቤት ልጅ ናት” ይላሉ። በተጨማሪም ወደ ትምህርት ቤት በባጃጅ ስትሄድ አግተው የወሰዷትን ሰዎች ማንነት ቤተሰቧ አስካሁን አላወቀም።

አጋቾቹ በማኅሌት ስልክ ወደ አባቷ በመደወል ልጃቸውን ማገታቸው እና “በሕይወት እንድታያት የምትፈልግ ከሆነ ሦስት ሚሊዮን ብር አዘጋጅ” ብለው ስልኩን እንደዘጉት ሚሊዮን ለቢቢሲ ተናግራለች።

እናት እና ልጅ

የፎቶው ባለመብት, MILLION

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ መደወላቸው እና የጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ቤተሰቡ እየተዘጋጀ እንደሆነ ጠይቀው ነበረ።

አጋቾቹም የማኅሌትን አባት “ከጠየቅነው በላይ ልትሰጠን እንደምትችል እናውቃለን፤ የጠየቅንህን ገንዘብ እኛ ባልነው ታቀርባለህ” ብለው መልዕክት ምልዕክት አስተላልፈው ስልኩን ዘጉት።

የታጋቿ እህት እንደምትለው ማኅሌት ከታገተችበት ቀን ቀደም ብሎ በቤታቸው አካባቢ ያልተለመዱ ሰዎችን ማየቷን ለአባቷ ተናግራ፤ አባትም ወጥተው ምንም ነገር እንዳላዩ እና እድትረጋጋ መክረዋት ነበር።

ማኅሌት ከታገተች በኋላ በነበሩት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ልጃቸው ያለችበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት ቢያደርጉም ምንም ፍንጭ ሳያገኙ እስካሁን ቆይተዋል።

ቤተሰብ ስለእገታው ለፖሊስ ያሳወቀ ቢሆንም፣ የአካባቢው ፖሊስ “እንደምንጠብቀው እየተባበረን አይደለም” የምትለው ሚሊዮን፤ ከእገታው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችም ቢሆኑ ያለችበትን ሁኔታም ሆነ አድራሻን የሚጠቁም ነገር ሊገኝባቸው አለመቻሉን ገልጻለች።

የታገተችውን ልጃቸውን ድምጽ ከሰሙ ወር ሊሆናቸው የተቃረቡት ቤተሰቦች “ድምጿ እንኳን ብንሰማ ትልቅ ተስፋ ይሆነን ነበር። በር ላይ አፍጥጦ መጠባበቅ በጣም ከባድ ነው” ይላሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በታዳጊዎች ላይ የሚፈጸም እገታ እየተበራከተ ይገኛል። ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ህጻናት ላይ ያነጣጠረ እገታ መታየቱን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ድርጊቱን የሚፈጽሙ ግለሰቦች ደግሞ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ ባለ ሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎችን እንደሚጠቀሙ ይገለጻል።

ቀደም ብሎ በመቀለ ከተማ በሚገኙ የተለዩ ክፍለ ከተማዎች ከትምህርት ቤት ልጆች አግተው ሲወስዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ባለፈው ወር መጋቢት አቶ መሃሪ ከበደ የተባሉ ግለሰብ ልጅ የሆነ ህጻን ታግቶ ተወስዶ ቤተሰቦች አራት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር።

ህጻኑ ከአንድ ሳምንት በላይ በእገታ ላይ የቆየ ሲሆን፣ ቤተሰቦች ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥረት ህጻኑ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. ተለቆ ከቤተሰቡ ጋር መቀላለቁን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

“ይህ የእገታ ወንጀል በክልሉ የተለመደ አይደለም” የሚለው የክልሉ ፖሊስ “ክስተቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተበት ያለበት ምክንያት ግን ጥናት ያስፈልገዋል” ብለው ነበር።

በትግራይ ክልል የተካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ የፀጥታ እና ደኅንነት ስጋት መፈጠሩ የሚገለጽ ሲሆን፣ በርካታ የክልሉ ከተሞች ውስጥም የተደራጁ እና በትጥቅ የተጋዙ ወንጀሎች መከሰታቸውን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።