የዓለም ዋንጫ፡ ሴኔጋል ስትሸነፍ የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ልጅ ለአሜሪካ ጎል አስቆጥሯል

የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ልጅ የሆነው ቲሞቲ ዊሃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባት ጎሎች ሴኔጋል የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታዋን በኔዘርላንድስ 2 ለ 0 ተሸንፋ ጀምራለች።

የመጀመሪያውን ጎል የፒኤስቪ አጥቂ ኮዲ ጋክፖ አስቆጥሯል።

ተቀይሮ የገባው ዳቪ ክላሰን ሁለተኛዋን ጎል ለብርቱካናማዎቹ ማስቆጠር ችሏል።

የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ውጤታማ ባለመሆናቸው ጨዋታው ለረዥም ደቂቃዎች ጎል ሳይቆጠርበት ቀጥሏል።

ሴኔጋሎች በጉዳት ያጡት አጥቂያቸው ሳዲዮ ማኔ ምን ያህል እንዳጎደላቸው የታየበት ጨዋታም ሆኗል።

የሴኔጋል ደጋፊዎች ስታዲሙን አድምቀውት አምሽተዋል።

የሴኔጋሉ ኢስማይላ ሳር በመጀመሪያው አጋማሽ የኔዘርላንድ ተከላካዮችን አስጨንቋል።

የኔዘርላንዱ አማካይ ዲ ዮንግ ደግሞ ጨዋታውን በመቆጣጠር ብቃቱን ያሳየበት ምሽት ነበር።

ድሉን ተከትሎ ብርቱካናማዎቹ በመክፈቻው ጨዋታ ኳታርን 2 ለ 0 ካሸነፈችው ኢኳዶር ጋር ምድቡን መምራት ችላል።

ምሽት ላይ በተካሄደ ሌላ ጨዋታ የላይቤሪያው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ልጅ ለአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ኳስ እና መረብ ለማገናኘት በቅቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ልጅ የሆነው ቲሞቲ ዊሃ አሜሪካ እና ዌልስ አንድ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ነው ለአሜሪካ ጎል ማስቆጠር የቻለው።

ከክርስቲያን ፑሊሲች የተሻገረለትን ኳስ ቲም ዊሃ ድንቅ በሆነ ሁኔታ ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

በጨዋታው መገባደጃ ላይ ዌልስ አቻ ማድረግ የቻለችውን ጎል ጋሬት ቤል ከፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

ፕሬዝዳንት ዊሃ በአሜሪካ የተወለደው ልጁ የዓለም ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ ለመመልከት ዘጠኝ ቀናትን በኳታር አሳልፏል።

የፕሬዝዳንቱ ጉዞ በሃገር ቤት ውዝግብ አስነስቷል።

የሃገሪቱ የፋይናንስ ሚንስትር ፕሬዝዳንቱ 2ሺህ ዶላር ቀን አበል አለው ማለቱ ነው የውዝግቡ መነሻ።

ተቺዎችም ፕሬዝዳንቱ ቃል የገባለትን “ደሃን የሚያቅፍ አጀንዳውን” የሚቃረን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዓለም ዋንጫው ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች እንግሊዝ ከኢራን ባደረጉት ጨዋታ ነው የተጀመረው።

ጨዋታውን እንግሊዝ 6 ለ 2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።

እንግሊዝ የጎል ካዝናዋን የከፈተችው በጁድ ቤሊንግሃም የጭንቅላት ጎል ነው።

ቡካዮ ሳካ እና ራሂም ስተርሊንግ ከእረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው ጎሎች እንግሊዝ 3 ለ 0 መምራት ችላለች።

ከእረፍት መልስ ሳካ ለራሱ ሁለተኛዋን ለቡድኑ ደግሞ አራተኛው ጎል አስቆጥሯል።

መህዲ ታሬሚ ለኢራን የመጀመሪያዋን ጎል በ65ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ማርከስ ራሽፎርድ እና ጃክ ግሪሊሽ ቀሪዎቹን ጎሎች ተቀይረው ገብተው አስቆጥረዋል።

ታሬሚ ሁለተኛዋን የኢራን ጎል ከፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

የኳታር የዓለም ዋንጫ ሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ይካሄዳሉ።

ሊዮኔል ሜሲን የያያዘችው አርጀንቲና ቀን ሰባት ሰዓት ላይ በሉሳይል ስታዲየም ሳዑዲ አረቢያን ይገጥማሉ።

በሜድቡ ሌላኛ ጨዋታ ሜክሲኮ እና ፖላንድ ስታዲየም 974 ላይ ይገናኛሉ።

ኤጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም ላይ ቱኒዝያ እና ዴንማርክ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ፈረንሳይ ደግሞ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ከአውስትራሊያ ጋር ትጫወታለች።