ዊል ስሚዝ በጥፊ ከመታው ክሪስ ሮክ ጋር ለማውራት ዝግጁ እንደሆነ ተናገረ

ዊል ክሪስን በጥፊ ሲመታው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዊል ስሚዝ በኦስካር ሽልማት ላይ በጥፊ ከመታው ኮሜዲያን ክሪስ ሮክ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆነ ተናገረ።

“ክሪስ ይቅርታ። ድርጊቴ ተቀባይነት የለውም። ለማውራት ዝግጁ ስትሆን አሳውቀኝ” ሲል ዊል በለቀቀው ቪድዮ ተናግሯል።

ክሪስ ሮክ በበኩሉ ከዊል ጋር አሁን ላይ ለማውራት ዝግጁ እንዳልሆነ መልሷል።

በኦስካር የሽልማት መሰናዶ ላይ ክሪስ ሮክ በዊል ባለቤት ጄዳ ፒንኬት የጤና ሁኔታ ዙሪያ በሰነዘው ቀልድ ነበር ዊል ስሚዝ በጥፊ የመታው።

ከዚህ ክስተት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ትላንት ቪድዮ የለቀቀው ዊል፣ ከክሪስ ጋር ማውራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

ክሪስን በጥፊ ከመታው በኋላ አንድ ጊዜ በጽሑፍ ይቅርታ ከመጠየቁ ውጪ፣ እስካሁን ዊል ስሚዝ ምንም አላለም ነበር።

ከአድናቂዎቹ የተላኩለትን ጥያቄዎች ካሜራ ፊት ይመልስ የነበረው ዊል፣ “ስለ ኦስካሩ ክስተት ባለፉት ሁለት ወራት መላልሼ ሳስብ ነበር። በዚያ ቅጽበት ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱም አሰብኩ። ድርጊቴ በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ትክክል አልነበረም” ብሏል።

ክሪስ ስለ ዊል ባለቤት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ፀጉር መላጨት ነበር የቀለደው።

ጄዳ ፀጉሯን የተላጨችው ፀጉር በሚያሳጠው አሎፒሽያ በተባለ ሕመም ምክንያት ሆኖ ሳለ እንዴት ክሪስ ይቀልድባታል? በሚል ዊል ከመቀመጫው ተነስቶ፣ ክሪስ ንግግር እያደረገ ወደነበረበት መድረክ ወጥቶ በጥፊ እንደመታው ይታወሳል።

ዊል አርብ ዕለት በለቀቀው ቪድዮ “ጄዳ በድርጊቱ ውስጥ እጇ የለበትም። አንተን እንድከላከልላትም አልጠየቀችኝም” ብሏል።

ዊል ጨምሮም “ልጆቼና ቤተሰቦቼ በእኔ ድርጊት ምክንያት መነጋገሪያ በመሆናቸው ይቅርታ ልጠይቃቸው እወዳለሁ” ብሏል።

ዊል እና ጄዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጄዳ ባለቤቷ ዊል እና ክሪስ እንዲታረቁ እንደምትሻ ባለፈው ወር ተናግራለች።

ዊል እሱ ለኦስካር በታጨበት ምድብ የነበሩ ሌሎች ተዋንያንንም ይቅርታ ጠይቋል።

“እኛኮ እንደ አንድ ማኅበረሰብ ነን። ኦስካር ያሸነፍኩት ድምጽ ስለሰጣችሁኝ ነው። ያንን ቅጽበት በማበላሸቴ ተጸጽቻለሁ” ብሏል።

የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾቹ ሴሪና እና ቬነስ ዊልያምስ አባትን ሆኖ በተወነበት ‘ኪንግ ሪቻርድ’ ፊልም ነበር ዊል ስሚዝ ኦስካርን ለማሸነፍ የበቃው።

ዊል ለቀጣይ 10 ዓመታት ከኦስካር ሽልማት እንደታገደ የኦስካር ኮሚቴ አስታውቋል።

ድርጊቱንም “ጎጂና ተቀባይነት የሌለው” ብሎታል።

በዕለቱ ዊል ክሪስን በጥፊ ከመታው በኋላ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ እየተካሄደበት ከነበረው አዳራሽ እንዲወጣ ቢጠየቅም አሻፈረኝ ብሏል።

ክሪስም ዊል ከአዳራሹ በኃይል እንዲባረር እንዳልፈለገ ገልጿል።