ትራምፕ ከሚስጥራዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካን ብሔራዊ ሚስጥራዊ ሰነዶች አግባብ ካልሆነ አያያዝ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ።
ትራምፕ ጥቁር ሙሉ ልብስ በቀይ ከረቫት አድርገው እና እጃቸውን አጣምረው ኮስተር ብለው የፍርድ ቤቱን ውሎ ሲከታተሉ ታይተዋል።
በአገሪቱ ታሪክ በሥልጣን ላይ ያለም ይሁን የቀድሞ ፕሬዝዳንት በፌደራል ወንጀል ክስ ሲመሰረትበት ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።
ማያሚ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የፌደራል የደህንነት ሰነዶችን ባልተገባ ሁኔታ በመያዝ እንዲሁም መንግሥት ሰነዶቹን መልሶ በእጁ ለማስገባት ያደረገው ጥረት ላይ እክል መፍጠር በሚል ለቀረቡባቸው 37 ክሶች ነው በጠበቃቸው በኩል ጥፋተኛ አይደለሁም ያሉት።
በዚህ ዓመት በወንጀል ሲከሰሱ ለሁለተኛ ጊዜያቸው የሆነው ትራምፕ፤ ከኒውክሌር ጋር የተያያዙ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ጨምሮ በርካታ ሚስጥራዊ ሰነዶችን እጃቸው ላይ በማቆየት ነው ክስ የተመሰረተባቸው።
ሪፓብሊካኑ ትራምፕ ከፍርድ ቤት ውሏቸው በኋላ ወደ ኒው ጀርሲ በማቅናት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል።
ትራምፕ የፌደራል መንግሥቱን ሚስጥራዊ ሰነዶች ከዋይት ሃውስ ይዞ የመውጣት መብት እንዳላቸው ለደጋፊዎቻቸው ተናግረው እያንዳንዱ ሚስጥራዊ ሰነድ ምን እንደያዘ ግን ለመመልከት ዕድሉን አላገኘሁም ብለዋል።
ትራምፕ ላይ ከቀረቡት ክሶች ጋር በተያያዘ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አማካሪ ዋልት ኖውታ ስድስት ክሶች ቀርበውባቸው በማያሚው ፍርድ ቤት ከትራምፕ ጋር በአንድ ጠረቤዛ ላይ ተቀምጠው ነበር።
ዛሬ 77 ዓመት የሚደፍኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ምንም አይነት እግድ ሳይተላልፍባቸው ፍርድ ቤቱን ጥለው ወጥተዋል።
ከወራት በፊት ፍሎሪዳ ከሚገኘው የትራምፕ ሪዞርት ውስጥ ከ100 በላይ ሚስጥራዊ ሰነዶች መገኘታቸው ይታወሳል።
ባልተገባ ሁኔታ ከዋይት ሃውስ ወጥተዋል የተባሉት ሰነዶች አሜሪካም ሆነ ሌሎች ሀገራት ያላቸው የመከላከያና የጦር መሳሪያ አቅም እንዲሁም የውጪ ጥቃትን ተከትሎ አጻፋዊ ምላሸን መስጠት እንደሚቻል የሚያሳዩ ሰነዶች ይገኙባቸዋል።
የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ትራምፕ በቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ የሚባሉ ከሆነ እስር ሊጠብቃቸው ይችላል ይላሉ።
ትራምፕ ግን የክሱ መጨረሻ ምንም ይሁን ምን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ እንደማያቆሙ ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተዋል።












