‘የምጽአት ቀንን ሽሽት’ ኢትዮጵያ ገብተው የነበሩት ኡጋንዳውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

ጸሎት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምጽአት ቀንን በመሸሽ ከኡጋንዳ ተነስተው ደቡብ ኢትዮጵያ ኛንጋቶም አካባቢ ቆይተው ነበር የተባሉ የአንድ ቤተክርስቲያን አባላት ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረገ።

በቁጥር 80 ናቸው የተባሉት የአንድ ቤተክርስቲያን አባላት፣ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው እራሳቸውን በጾም እንዲያስርቡ ፓስተራቸው እንዳሳመናቸው የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የግለሰቦቹ ፓስተር 40 ቀናትን ከጾሙ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ትገናኛላችሁ” እንዳላቸው የእምነቱ ተከታዮች ገልጸዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት የዩጋንዳ የፖሊስ ኃይል ሳይመን ኦፖሎት የተባለውን ይህንን ግለሰብ ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው።

በኡጋንዳ ምሥራቃዊ ክፍል ከምትገኘው ሴሬሬ ወረዳ ተነስተው ረዥም ርቀት አቆራርጠው ደቡብ ኢትዮጵያ ስለደረሱት ግለሰቦች ከብዛታቸው ጀምሮ እስከ ጉዟቸው ዓላማ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።

ግለሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ ነው የሚሉ ያሉ ሲሆን፣ ጉዞው ከምጽአት ቀን ሽሽት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉም አልጠፉም።

በሌላ በኩል ደግሞ የሰዎቹ ድንገት ከኡጋንዳዋ መንደር መሰወር በሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ወድቀዋል የሚል ስጋትንም ፈጥሮ ነበር።

‘የምጽአት ቀን ሽሽት’

የግለሰቦቹን ጉዞ በተመለከተ ቀደም ብለው ሲወጡ የነበሩ ሪፖርቶች የሚጠቁሙት በቁጥር እስከ 250 የሚደርሱ ኡጋንዳውያን የምጽአት ቀንን ሽሽት ኢትዮጵያ መግባታቸውን ነበር።

የኢኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን “የምጽአት ቀንን በመሸሽ” በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኩል ወደ አገሪቱ ገብተዋል ገብተው ኛንጋቶም በሚባለው አካባቢ ይገኛሉ ብለው ነበር።

ከአምባሳደሩ በተጨማሪ የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁ የግለሰቦቹ ጉዞ ከምጽአት ቀን የተያያዘ ስለመሆኑ በስፋት ሲዘግቡ ነበር።

የጉዞው ተልዕኮ ሃይኖታዊ ነው

በሌላ በኩል ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ ኢትዮጵያ የገቡት ኡጋንዳውያን በቁጥር 277 መሆናቸውን በመግለጽ፣ ግለሰቦቹ ወደ አካባቢው የመጡት ለጸሎት እንጂ የምጽአት ቀንን በመሸሽ አይደለም በማለት ለቢቢሲ ተናግረው የነበሩት የኛንጋቶም ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሎኪኛኒጋ ሙርሌ ናቸው።

ኡጋንዳውያኑ በወቅቱ በቤተክርስቲያን የእንግዳ መቀበያ እና በግለሰቦች መኖሪያ ማረፋቸውን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደምም ከኬንያ ቱርካና፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኡጋንዳ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መጥተው እንደነበር ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህ የደረሱበት አልታወቀም ተብለው የነበሩት የክርስትና እምነት ምዕመናን የሚገኙበት አካባቢ ጎሳዎች የባህል የጋራ ማኅበር የሆነው ኢቴሶ ካልቸራል ዩኒየን ከ270 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።

የማኅበሩ ቃል አቀባይ ጋብርኤል ኦፖሎት እንዳሉት ተሰወሩ የተባሉት 273 ሰዎች ዝምድና እንዳላቸው ወደሚያምኑበት የኢትዮጵያ እና የኬንያ ማኅበረሰቦች ለሰላም እና ለክርስቲያናዊ ተልዕኮ መጓዛቸውን አመልክተዋል።

ካርታ

‘40 ቀን ጹሙ’

ከየካቲት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኡጋንዳውያኑ ጉዞ ብዙ ሲያነጋግር ቆይቶ አሁን ላይ 80 የክራይስ ዲሲፕልስ ቸርች (ሲዲሲ) ቤተ-ክርስቲያን አባላት ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል።

ከምሥራቅ ኡጋንዳ ገጠራማ አካባቢ ተነስተው 500 ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ደቡብ ኢትዮጵያ የደረሱት ግለሰቦች ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ገጥሞናል ያሉትን ለኡጋንዳ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ግለሰቦች ኦፖሎት የተባለው ፓስተራቸው “ሳያቋርጡ ለ40 ቀናት ከጾሙ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በ41 ቀን ትገናኛላችሁ ሲል ነግሯቸዋል” ሲሉ የኡጋንዳ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ቃል አቀባይ ሳይመን ሙንዴኒ “መስፈርቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ነው፤ ያ እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያ መገኘት ነበረባቸው። እንደ እርሱ ከሆነ [እንደ ፓስተሩ] ዓለም ወዲያው ትጠፋለች” ስለማለታቸው ዴይሊ ሞኒተር ዘግቧል።

ኡጋንዳውያኑ ኅዳር ወር ላይ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከተረዱ በኋላ ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እስኪመቻች ድረስ ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኡጋንዳ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ያሉበት ቡድን ያለ በቂ ምግብ ወደ ኢትዮጵያ ረዥም ጉዞ ማድረጉን ተከትሎ በጣም ተዳክመው ነበር ብሏል።

ግለሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደገቡም ሆነ ወደ ኡጋንዳ በምን አይነት የትራንስፖርት አማራጭ እንደተመለሱ የተባለ ነገር የለም።